መግቢያ
ወደላይ ያረገውና የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች ፊት ቃሉን የሚያጸኑ ምልክቶች እንዲሆኑና በአጥቢያ ቤተክርስቲያንም ለማነጽ የሚሆን ቃል የሚተላለፍባቸው መንገዶች እንዲሆኑ ከሰጣቸው ስጦታዎች አንዱ በልሳኖች መናገር ነበር። ይህንንም በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል የሚናገረውን እውነት ማወቅ በዘመናችን የብዙዎች ጥያቄና ፍላጎት ሆኗል። የዚህም ምክንያቱ በልሳኖች መናገርን በተመለከተ በየስፍራው የተፈጠረው መደነጋገርና ግራ መጋባት ነው።
በልሳኖች መናገር በ1ቆሮ.12፡8-10 ውስጥ ከተዘረዘሩት ዘጠኝ የጸጋ ስጦታዎች አንዱ ሆኖ ሳለ ከሌሎቹ የጸጋ ስጦታዎች ይልቅ ሁሉ እንዲፈልገው በሚደረግባቸው ስፍራዎች ግራ መጋባቱ ጎልቶ ይታያል። አንዳንድ ጊዜ በልኖች መናገር «የመዳን ምልክት ነው» ሲባል ሌላ ጊዜ ደግሞ «የመዳን ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ምልክት ነው» ሲባል ይሰማል። ከዚህም የተነሣ «በልሳኖች ካልተናገርኩ አልዳንኩም ወይም በመንፈስ ቅዱስ አልተጠመቅሁም ማለት ነው?» በማለት ሁልጊዜም በኅሊናቸው የሚከሰሱ ብዙዎች ናቸው፤ ይህንንም ክስ ከኅሊናቸው ለማጥፋት ወይ ፈጥረው ወይ ኰርጀው ከአፋቸው አንድ ነገር ወደ ማውጣት የሄዱም ጥቂቶች አይደሉም። ሌሎች ደግሞ በልሳኖች ለመናገር ካላቸው ከፍተኛ መጠማት የተነሣ «በታዋቂ አገልጋዮች እጅ ተጭኖ የሚጸለይበት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ፕሮግራም አለ» ወደተባለበት ሁሉ ሲንከራተቱ ማየት በዘመናችን የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። ይህም መታወክና መደነጋገር የክርስቶስ ልብ ላላቸው ሁሉ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።
ለመሆኑ በልሳኖች መናገር እንደምን ያለ ስጦታ ነው? የተሰጠበትስ ዓላማ ምንድር ነው? በሐዋርያት ዘመን ይህ ስጦታና አጠቃቀሙ ምን ይመስል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በልሳኖች መናገርን በተመለከተ በአጠቃላይ ምን ያስተምረናል? በዘመናችን «በልሳኖች መናገር ነው» እየተባለ በየስፍራው የሚሰማውና የሚታየው ልምምድስ ምንድር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በልሳኖች የመናገር ስጦታን አስመልክቶ ከሚያስተምረው እውነት ጋር ሲነጻጸር እንዴት ይታያል? በዚህ ዘመን ያለን አማኞች በልሳኖች መናገርን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት ምንድር ነው? የእነዚህንና በልሳኖች መናገርን በተመለከተ የሚነሱ የሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኝ ሲሆን ልበ-ሰፊዎች ለሆኑና «መጽሐፍስ ምን አለ?» ለሚሉ ሁሉ ከዚሁ የከበረ መጽሐፍ የተገኙ እውነቶችን በዚህች መጽሐፍ ውስጥ እናቀርባለን።
በልሳኖች መናገርን በተመለከተ ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል የሚናገሩት መጻሕፍት ሦስት ሲሆኑ እነርሱም የማርቆስ ወንጌል፣ የሐዋርያት ሥራ እና የመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት ናቸው። በመሆኑም በልሳኖች መናገርን በተመለከተ ትክክለኛ መረዳትን ለማግኘት በእነዚህ መጻሕፍት ርእሱ የተነሣባቸውን ጥቅሶች በጥልቀት ማጥናት እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል፤ በዚህች አነስተኛ መጽሐፍም የምናደርገው ይህንኑ ነው። ይህች መጽሐፍ ስትነበብ በቅዱሳት መጻሕፍት የተነገሩ እውነቶችን በመረዳት ማረፍ ለሚፈልጉና ለእውነት የሚሸነፍ ልብ ላላቸው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በልሳኖች መናገርን በተመለከተ ያለን የራሱን ሐሳብ ግልጽ ያደርግላቸዋል ብለን እናምናለን።
ልሳኖች (በአዲስ ቋንቋ) መናገር በማርቆስ ወንጌል
ማር.16፡17
«ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፤ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በድውዮች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይድናሉ።»
ይህ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለአሥራ አንዱ በተገለጠ ጊዜ የተናገረው ቃል ነው። በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው ጌታችን የዘረዘራቸው ምልክቶች አምስት ሲሆኑ ከአምስቱ ምልክቶችም አንዱ በአዲስ ቋንቋ መናገር ነው።
«ያመኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል» በሚለው ቃል ውስጥ «ያመኑት» የተባሉት የተሰበከላቸውን ወንጌል ተቀብለው በጌታ በኢየሱስ ያመኑትን ሰዎች ያመለክታል አንዱ ከአማኞች መካከል እነዚህን በዚህ ክፍል የተዘረዘሩትን ምልክቶችን ለማድረግ የሚያስችል የተለየ እምነት ያላቸውን ለይቶ የሚያመለክት አይደለም። ቀደም ባሉት ቁጥሮች እንደምንረዳው ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለ11ዱ በተገለጠ ጊዜ ያዩትን ስላላመኗቸው ጌታ አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቅፏል (ከቍ.9-14 ተመልከት)፤ ከዚያም በኋላ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ በማለት የወንጌል ተልእኮን ሲሰጣቸው እንመለከታለን። በመቀጠልም ባመኑትና ባላመኑት መካከል ግልጽ ልዩነት በማድረግ «ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል» ሲላቸው እናያለን (ቍ.15-16)፤ «ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል» ያለው ከዚህ በኋላ ነው። ስለሆነም «ያመኑት» የተባሉት በኢየሱስ ያመኑት መሆናቸውን በዚህ እንገነዘባለን።
«ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል» ማለትም ያመኑት ሁሉ እነዚህን ምልክቶች ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ሆኖም ምልክቶቹ ካመኑት መካከል በአንዳንዶች ሲደረጉ በጌታ ያመኑትን ሰዎች መከተላቸውን የሚያሳይ ነው። ንባቡም «ይከተሉአቸዋል» ይላል እንጂ «ያደርጋሉ» አይልም። ይህም በጌታ ያመኑት ሰዎች እምነታቸው ከእግዚአብሔር መሆኑን ለመመስከር ምልክቶቹ በመካከላቸው መደረጋቸውን ያሳያል እንጂ ያመኑት ሁሉ እያንዳንዳቸው ምልክትን እንደሚያደርጉ አያሳይም። ይህንን ለይቶ ማስተዋል መሠረታዊውን ሐሳብ ማለትም ትክክለኛውን እውነት ለመረዳት ያስችላል።
አይሁድ የኢየሱስን ትንሣኤ ለማስተባበል የቻሉትን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። በጌታ ያመኑት በአንድ ልብ አብረው ሆነው ይጸልዩና ወጥተውም በየስፍራው ይሰብኩ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስም ካረገ በኋላ ከእነርሱ ጋር በመሥራት ምልክቶችን አያደረገ ቃሉን ያጸና ነበር፤ ይህንንም በተመለከተ በቍ.20 ላይ «እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር» ተብሎ የተጻፈውን ቃል እናገኛለን። ስለሆነም ምልክቶቹ የመደረጋቸው ዓላማ በዚያ የቤተክርስቲያን የምሥረታ ዘመን የተገለጠውን ቃል ለማጽናት ነበር።
ቃሉን ለማጽናት ያመኑትን እንደሚከተሏቸው ከተነገሩት ምልክቶች አንዱ አዲስ ቋንቋ መናገር መሆኑ ተገልጧል። በአዲስ ቋንቋ መናገርና መሆኑ ተገልጧል። በአዲስ ቋንቋ መናገርና በልሳን መናገር ምንም ልዩነት እንደሌላቸውም ሊታወቅ ይገባል። ልሳን ማለት ቋንቋ ማለት ነውና። በዚህ ክፍል ቋንቋው አዲስ መባሉም በተአምር የሚነገረው ቋንቋ ከዚያ በፊት ለተናጋሪውም ሆነ ያን ቋንቋ ለማያውቁት ሰሚዎች ሁሉ አዲስ በመሆኑ ነው።
ጌታ ኢየሱስ «በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ» ብሎ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በኋላ በተግባር የሆነውን ስንመለከት እርሱ ካረገ በኋላ በኢየሩሳሌም በተከበረው በበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ በአንድ ልብ ሆነው የነበሩት የመጀመሪያዎቹ አማኞች በሌላ ልሳኖች እንደተናገሩ ተጽፏል፤ ይህም ምልክት ከታየ በኋላ በሐዋርያው ጴጥሮስ አማካኝነት ስለክርስቶስ የተሰበከው የእግዚአብሔር ቃል ሲነገር ልባቸው የተነካ 3 ሺህ ሰዎች ቃሉን የተቀበሉ መሆናቸውን እናነባለን (ሐ.ሥ.2፡1-41)፤ ሆኖም እነዚህ 3 ሺህ ሰዎች በልሳኖች እንደተናገሩ አናነብም፤ እንደዚሁም በሐዋ.ሥ.4፡4 ላይ 5 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች እንዳመኑ የተገለጸ ሲሆን እነርሱም በልሳኖች እንደተናገሩ አናነብም፤ በሌሎችም ስፍራዎች ወንጌል እየተሰበከ ከአይሁድም ከግሪክ ሰዎችም በዙዎች እንዳመኑ የተነገረ ቢሆንም ሁለም በልሳኖች እንደተናገሩ አልተገለጸም (የሐ.ሥ.2፡47፤ 5፡14፤ 8፡12፤ 14፡1፤ 17፡4 ተመልከት)። ደግሞም ከ1ቆሮ.12፡30 እንደምንረዳው ሁሉም በልሳኖች ሊናገሩ አይችሉም። ስለዚህ «በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ» የሚለው ቃል ያመኑትን ሁሉንም የሚመለከት እንዳልነበረ እንገነዘባለን።
በሐ.ሥ.2፡43 እና ምዕ. 5፡12 ላይ በሐዋርያት እጅ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ እንደነበረ ሲገለጽ በሐ.ሥ.6፡8 ላይ ደግሞ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያርግ እንደነበር ተነግሮናል። የሚደረጉት ምልክቶችም ዓላማቸው ቃሉን ማጽናት ስለሆነ ከምልክቶቹ ጋር የእግዚአብሔር ቃል አብሮ ይነገራል። ለምሳሌ በሐ.ሥ.4፡30 ላይ ያለውን የአማኞች ጸሎት ስንመለከት «... ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው» ይላል። እንዲሁም ፊልጶስ በሰማርያ ወንጌልን ሲሰብክ ምልክቶች ይደረጉ ነበር፤ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃል «ሕዝቡም ፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ»ይላል (የሐ.ሥ.8፡6)። እንዲሁም ጳውሎስ በእርሱ በኩል ይደረጉ ስለነበሩ ምልክቶች ሲጽፍ «አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፣ በምልክትና በድንቅ ነገር ኃይል በመንፈስ ቅዱስም ኃይል በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም» ይላል (ሮሜ.15፡18)፤ በሌላ ስፍራ ደግሞ ምልክቶችና ተአምራት የሐዋርያነት ምልክት እንደሆኑ ሲጽፍ «በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግስት ተደረገ» ብሏል 2ቆሮ.12፡12)። ስለሆነም በአዲስ ቋንቋ መናገርም ሆነ ሌሎች ምልክቶች ይደረጉ የነበሩት በሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር አብረው በሠሩ በተወሰኑ የቃሉ አገልጋዮች እንጂ ባመኑት ሁሉ አልነበረም። እግዚአብሔር እነዚህን ምልክቶች የሰጠውም በመልእክተኞቹ የላከው ቃል የእርሱ ቃል መሆኑን ለመመስከር ነበር። በዕብ.2፡3-4 ላይም «... ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፤ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት» የሚለው ቃል ይህንኑ ያረጋግጣል።
በልሳኖች መናገር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑትን እንደሚከተሉ ከተናገራቸውና ቃሉን ካጸናባቸው ምልክቶች አንዱ «በአዲስ ቋንቋ መናገር» እንደሆነ ባለፈው ክፍል ተመልክተናል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተገለጠውን የዚህን ተግባራዊ ገጽታ ደግሞ በዚህ ክፍል እንመለከታለን፤ በአዲስ ቋንቋ መናገር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ «በልሳኖች መናገር» ተብሎ የተገለጠ ሲሆን በሁለቱ አገላለጾች መካከል ግን ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፤ ከጌታ ዕርገት በኋላ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከምድር ዳር ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሠራውን የወንጌል ሥራ በሚናገርው በዚህ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በልሳኖች መናገር በሦስት ስፍራዎች ተጠቅሶ እናገኛለን፤
እነርሱም፡-- 1. ሐ.ሥ.2፡-13፣ 2.
- ሐዋ.ሥ.10፡44-472፣ 3.
- ሐዋ.ሥ.19፡1-7 ናቸው።
በእነዚህ ክፍሎች መናገርን በተመለከተ የተጻፈውን እውነት ቀጥሎ እንመለከታለን።
1. የሐ.ሥ.2፡1-13ይህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ በወረደበት «በዓለ ሃምሳ» በተባለው ቀን ስለተነገሩት ልሳኖች የሚናገር ነው። በዓለ ሃምሳ በዘሌ.23 ላይ ከተዘረዘሩት እና እስራኤላውያን እንዲያከብሯቸው ከታዘዙአቸው ከሰባቱ የእግዚአብሔር በዓላት ሦስተኛው በዓል ነው። ቃሉ ከግሪክኛ ተወስዶ በእኛ አነጋገር ጰንጠቆስጤ ተብሏል። ትርጉሙም ያው በዓለ ሃምሳ ማለት ነው። ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣና ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በኢየሩሳሌም በተከበረው በበዓለ ሃምሳ ዕለት ሁሉም በአንድ ልብ አብረው በነበሩ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ እጅግ የሚያስደንቁ ተአምራዊ ክስተቶች ተከሠቱ፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስ ራሱን የገለጠባቸው ክርስተቶች ነበሩ። ከሰማይ ድምጽ መጣ፤ ይህም የመጣው ድምጽ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ እንደነበረ ተነግሮናል። ይህም ድምጽ በቤቱ ውስጥ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን ከቤቱ ውጪ በርቀት ላሉት ሁሉ የሚሰማ ነበር። በቍ.6 ላይ «ይህም ድምጽ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰባሰቡ» የሚለው ቃል ይህንኑ ያስረዳል። ይህ ድምጽ በአንድ ልብ አብረው የነበሩ እነዚያ ደቀመዛሙርት ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንደሞላው ስናነብ መንፈስ ቅዱስ የወረደው በዚያ ቤት ውስጥ ተለይተው ለነበሩት አማኞች እንደሆነ እንገነዘባለን። ከዚያ ወዲህም መንፈስ ቅዱስ የሚኖረው ከአይሁድና ከአሕዛብ ተለይታ ባለችው በቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነው። ድምፁ ቤቱን መሙላቱም መንፈስ ቅዱሰ በቤተክርስቲያን (በጉባኤ) ለመኖር መውረዱን የሚያመለክት ነው። በዕለቱ የተከሠተው ነገር የሚሰማ ብቻ ሳይሆን የሚታይ ክስተትም ነበር። «እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው» የሚለው ቃል ይህን ያስረዳል። እዚህ ላይ እንደ እሳት የታዩት የተከፋፈሉት ልሳኖች እንጂ ራሱ መንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ይህንን ንባብ መጥምቁ ዮሐንስ «...እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል (ማቴ.3፡11) ወይም «...እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳትም የጠምቃችኋል (ሉቃ.3፡16) ብሎ ከተናገረው ጋር በማያያዝ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅና በእሳት መጠመቅ አንድ እንደሆኑ ሲነገር ይሰማል። «መጥምቁ ዮሐንስ ግን «በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም» ሁለቱን ለይቶ መናገሩን ማስተዋል ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ ስለመጠመቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ሲናገር «ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» ብሎ ነበር (የሐ.ሥ.1፡5)። በዚህም መሠረት በበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ተከናውኗል ማለት ነው። በእሳት መጠመቅ ግን ፍርድን የሚያመለክት ነው፤ ስለዚህ ነገር በተነገረበት በዚያው በማቴ.3 በቍ.12 ላይ «መንሹ በእጁ ነው አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራ» ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል» የሚለውን እናነባለን። ስለሆነም በእሳት መጠመቅ ገለባው በማይጠፋ እሳት ከመቃጠሉ ጋር የሚነጻጸር ነው። ወደፊት የማያምኑ ሰዎች ሲፈረድባቸው ወደ እሳት ባሕር እንደሚጣሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ተነግሮናል (ራእ.20፡14፤ 21፡8 ተመልከት)፤ ስለዚህ ኢየሱስ በእሳት የሚያጠምቀው የማያምኑትን ነው። በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ግን ያመኑትን እንጂ ያላመኑትን የሚመለከት አይደለም፤ ስለሆነም በበዓለ ሃምሳ (በጰንጠቆስጤ) ዕለት በአንድ ልብ አብረው የነበሩት አማኞች የተጠመቁት በመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ በእሳት አይደለም። «እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዮአቸው» በሚለው ንባብ ውስጥ የምንረዳውም የተከፋፈሉት ልሳኖች በወቅቱ በቤቱ ውስጥ ለነበሩት አማኞች በዐይን የታዩበትን ቅርጽ ነው። እሳት በሚንበለበልበት ጊዜ የተከፋፈሉ ነበልባሎች ይታዩበታል። በአንድ ልብ የተሰበሰቡት እነዚያ አማኞች ከሰማይ የመጣውን ድምጽ ተከትሎ የተከፋፈሉ ልሳኖችን (መላሳችን) በዚህ አይነት መልክ በዓይናቸው አይተዋል፤ ስለዚህ በሐ.ሥ. ምዕ.2 «እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው» በሚለው ንባብ ውስጥ እሳት የተከፋፈለ ልሳኖች (ቋንቋዎች) ምሳሌ መኾኑን እንገነዘባለን። በዚህ መልክ የዚህን ንባብ ትክክለኛ ሐሳብ በጥንቃቄ ያስተዋለ አማኝ በዕለቱ የተከናወነው ክስተት በእሳት መጠመቅ ነው ሊል አይችልም። እንደ እሳት ተከፋፍለው የታዩት ልሳኖች ልክ ከሰማይ እንደመጣውና እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ሆኖ እንደተሰማው ድምፅ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የሚገልጥ ሌላው ክስተት ነበር። ስለዚህም የወረደው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እሳት አይደለም፤ በዚህ ዕለት የተከናወነው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ እንደሆነ ከመውረዱ በፊት በዮሐ.7፡39 «ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና» ተብሎ በተነገረው ቃል እንዲሁም ከወረደ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለመንፈስ ቅዱስ መውረድ ሲናገር «ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደወረደ..» ብሎ በገለጸው ቃል መረዳት ይቻላል። ስለዚህ እነዚያ አማኞች ጌታችን «ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» (የሐ.ሥ.1፡5) ባላቸው መሠረት በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቁ እንጂ በእሳት አልተጠመቁም፤ «በእሳት መጠመቅ» ፍርድን የሚያሳይ ስለሆነ ቀደም ሲል እንደተገለጠው የሚያመለክተው የማያምኑ ሰዎች ወደ እሳት ባሕር መጣላቸውን ነው። ስለሆነም ባለማወቅ «በእሳት አጥምቀን» ብለው ሲጸልዩ የነበሩ አማኞች ይህን እውነት ከተረዱ በኋላ በጸጋው ብዛት እንደ ጸሎታቸው በእሳት ያላጠመቃቸውን አምላክ በማመስገን ይህን ጸሎታቸውን ሊያርሙ ይገባቸዋል።
«እንደ አሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው» ካለ በኋላ «በያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጡባቸው» የሚል እናነባለን። የተከፋፈሉት ልሳኖች በዓለም ላይ የሚገኙት የተለያዩ ቋንቋዎች ናቸው። በዘፍ.11፡1 «ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች፤» የሚል ካነበብን በኋላ የሰው ልጆች አንድ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ በማመጻቸው ምክንያት እግዚአብሔር «እነሆ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፤ በሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ማድረግ ጀመረ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። ኑ እንውረድ፤ አንዱ ያንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው» በማለት የተናገረውን እናነባለን (ቍ.6 እና7)። በታሪክ ቅደም ተከተሉ በዘፍ.11 ከተገለጸው ቀጥሎ የሚታየው በዘፍ.10፡5፣20፣31 ላይ የተገለጸው ንባብም የሰው ልጆች በየምድራቸው በየቋንቋቸው በየነገዳቸው በየሕዝባቸው እንደተከፋፈሉ በግልጽ ይነግረናል። ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም ላይ የተከፋፈሉ ልሳኖች ሊኖሩ እንደቻሉ እንረዳለን። በበዓለ ሃምሳ ዕለትም እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች በታዩ ጊዜ በእያንዳንዳቸው ላይ መቀመጣቸው በዚያ ለነበሩት ለእያንዳንዳቸው የተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች እንደተሰጧቸው የሚገልጥ ነው። በዕለቱ በአንድ ልብ ሆነው አብረው የተሰበሰቡት እነዚያ አማኞች በተለያሉ (በተከፋፈሉት) ልሳኖች ተናግረውል። ይህም የሆነው በዚያን ዕለት በወረደው በመንፈስ ቅዱስ ስለተሞሉ ነው። የመንፈስ ቅዱስ መውረድ መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ሊኖር መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ደግሞ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ሆኖ አንድ ሥራ ለመሥራት ወይም አንዳች አገልግሎትን ለማከናወን በወቅቱ በኃይል ወይም በሙላት መገለጡን የሚያሳይ ነው። መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በወረደ ጊዜ በአንድ ልብ የተሰበሰቡት አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ልሳኖች መናገራቸውን «በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር» በሚለው ቃል እንረዳለን። በዚህ ንባብ ውስጥ «በሌላ ልሳኖች» የሚለው ሐረግ በምድር ላይ ከሚነገሩት ቋንቒዎች ሌላ ማለት አይደለም። ልሳኖቹ ለተናጋሪዎቹና በመንፈስ ቅዱስ የተገለጡትን ቋንቋዎች ለማያውቋቸው ሁሉ ሌላ ልሳኖች መሆናቸውን የሚያስረዳ ብቻ ነው። በተለይም በዚህ ንባብ «ልሳኖች» የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር የተነገረ በመሆኑ በዕለቱ አንድ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቋንቋዎች በተአምር እንደነገሩ ይገልጻል። ይህም የሆነውን መንፈስ ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው (እንደወሰነላቸው) ነው።
«ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምጽ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፡- እነሆ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በሁለት ወንዝም መካከል፣ በይሁዳም፣ በቀጰዶቅያም፣ በጳንጦስም በእስያም፣ በፍርግያም፣ በጵንፍልያም፣ በግብፅም፣ በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፣ በሮሜም የምንቀመጥ አይሁድም ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በእርሳቸው ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።» (ከቍ.5-13)በዚህ ክፍል ንባብ ልሳኖች በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የተለያዩ ሰዎች የሚናገሯቸው ቋንቋዎች እንደሆኑ በስፋት ተገልጧል። የበዓለ ሃምሳ ዕለት ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ(ይገኙ) ነበር። «ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ» ሲል በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን በአጠቃላይ ይመለከታል። አይሁድ ከሰማይ በታች ወዳሉ ሕዝብ ተበትነው ይኖሩ እንደ ነበር የታወቀ ነው። ከ70ው ዓመት የባቢሎን ምርኮ በኋላም ወደ አገራቸው የተመለሱት ከይሁዳ ነገድና ከብንያም ነገድ፣ ሌዋውያንንም ጨምሮ፣ በቍጥር 42360 የበሩ ጥቂት ቅሬታዎች ብቻ ነበሩ (ዕዝ.2፡65)። ስለሆነም ብዙዎች አይሁድ በአሕዛብ አገሮች እንደተበተኑ ይኖሩ ነበር ማለት ነው። ከጌታችን ዕርገት በኋላ በተከበረው የበህለ ሃምሳ ዕለት ከዚያው ከይሁዳ የመጡትን ጨምሮ ባጠቃላይ ከ15 አገሮች የተሰባሰቡ አይሁድ በኢየሩሳሌም ተገኝተው እንደነበር ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው ክፍል እንረዳለን። በዚህም በአሕዛብ አገሮች ተበትነው ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ብዙዎች እንደነበሩና በዓሉን ለማክበር ከያለበት ተሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ እንደነበር እንገነዘባለን። በዓለ ሃምሳ እስራኤላውያን በጠቅላላ ከያለበት እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ በመረጠው ስፍራ (በኢየሩሳሌም) ተሰብስበው ከሚያከብሯቸው ከ3ቱ ዐበይት በዓላት ማለትም «የቂጣ በዓል፣ የሰባቱ ሱባኤ በዓልና የዳስ በዓል» ተብለው ከሚጠሩት በዓላት «የሰባቱ ሱባኤ በዓል» የሚባለው ነው (ዘዳግ.16፡16)። «በጸሎት የተጉ አይሁድ» ተብለው የተገለጡት እነዚህ አይሁድ በሕጉ መጽሐፍ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደሚያውቁና ምንም እንኳ በአሕዛብ አገሮች ተበትነው ያለ ቢሆኑም እምነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ እንደነበሩ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ የተወለዱትም ሆነ የሚኖሩት በአሕዛብ አገሮች በመሆኑ የሚናገሩትም ቋንቋ ያው የተወለዱበትንና የሚኖሩበትን አገር ቋንቋ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ለአይሁድ በራሳቸው ቋንቋ ሲናገር የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በአይሁድ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በተከፋፈሉ ልሳኖች ማለትም በተለያዩ ቋንቋዎች መናገሩን እናስተውላለን። ይህም እግዚአብሔር ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸጋ በር እንደከፈተና አስቀድሞ ሕዝቡ ያልነበሩትን ሕዝብ የሚያደርግበትን መንገድ እንዳዘጋጀ የሚያሳይ ነው።
በአንድ ልብ ሆነው አብረው ያሉት የጌታ ደቀመዛሙርት በተሰበሰቡበት ቤት የተሰማው ከሰማይ የመጣው ድምጽ ቀደም ሲል እንደተገለጠው በርቀት የነበሩትን እነዚህን ከየአገሩ የመጡትን አይሁድ መሰብሰብ እስኪችል ድረስ የሚሰማ ድምጽ ነበር። «ይህ ድምጽ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ» የሚለው ቃል ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ከተሰበሰቡ በኋላ ደግሞ እነዚያ በአንድ ልብ አብረው የነበሩ የገሊላ ሰዎች በየቋንቋቸው ሲናገሩ የሚሉትን እስኪያጡ ድረስ እንደተገረሙ እናያለን። «እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ» የሚሉት ዐረፍተ ነገሮች ይህን ስሜታቸውን ያሳያሉ፤ የተገረሙትና የተደነቁትም ቋንቋዎቻቸውን የማያውቁ የገሊላ ሰዎች በልምድም በትምህርትም ሳይሆን በተአምራዊ ኃይል የእያንዳንዳቸውን ቋንቋ ሲናገሩ በመስማታቸው ነው፤ «እነሆ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?» እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?» በማለት የተናገሩት ቃል ይህንኑ የሚያስረዳ ነው። ይህም ከፍ ብሎ በቍ.4 ላይ «በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር» ተብሎ የተነገረው በጊዜው በተለያዩ አገሮች ይነገሩ በነበሩ ቋንቋዎች መናገራቸውን የሚያመለክት እንደሆነ ያረጋግጣል። የዚያን ዕለት የተወለዱበት የገዛ ቋንቋቸው በተአምር ሲነገር የሰሙት ሰዎች ከ15 አገሮች የመጡ ነበሩ። እነርሱም ከቍ.9-11 በተዘረዘሩበት ቅደም ተከተል መሠረት እንደሚከተለው ቀርበዋል።
1. ጳርቴ 9. ቀጰዶቅያ 2. ሜድ 10. ጳንጦስ 3. ኢላሚጤ 11. እስያ 4. በሁለት ወንዝም መካከል (መስጴጦምያ) 12. ፍርግያ 5. ይሁዳ 11. ጵንፍልያ 13. በቀሬና በኩል ያሉት የሊቢያ ወረዳዎች 12. ግብፅ 13. ሮሜ 14. ቀርጤስ 15. ዓረብ ናቸው።
እነዚህ 15 አገሮች ተዘርዝረው የእያንዳንዳቸው ቋንቋ መነገሩ በግልጽ ስለተነገረን፣ በልሳኖች መናገር በተለያዩ አገሮች ቋንቋዎች መናገር መሆኑን ያለምንም መደነጋገር መረዳት እንችላለን። በዕለቱ የተነገሩት ልሳኖች ዋና ይዘት ምን እንደነበረም የቋንቋዎቹ (የልሳኖቹ) ባለቤቶች ሲገልጹ «የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን» (ቍ.11) ብለዋል። ስለዚህ በልሳን መናገር አንድ ትርጉምና መልእክት ያለው ነገር መናገር እንጂ ትርጉም የለሽ ድምፆችን ማውጣት ወይም አንድን ሐሳብ የሚያስተላልፉ ወደ አፍ የገቡ ፊደላትን እንዳገኙ መደርደር አይደለም። በበዓለ ሃምሳ ዕለት የተነገሩት ልሳኖች ሰሚዎቹ የተረዱትን መልእክት ያስተላለፉ ልሳኖች ነበሩ፤ መልእክቱም ወደ ሰሚዎቹ የተነገረ ነበረ፤ በመልእክቱም ሁሉም ስለ እግዚአብሔር ታላቅ ሥራ የተነገራቸውን ሰምተዋል። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻቸው ሲሰሙ የተገረሙት እነዚያ ሰዎች በሁለት ሲከፈሉ እናያለን፤ በአንድ ወገን ያሉት «እንጃ ይህ ምን ይሆን?» ሲሉ ሌሎቹ ግን እያፌዙባቸው «ጐሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል» ብለው የድፍረት ቃል መናገራቸውን እናነባለን። ብዙውን ጊዜ ምልክቶችን ያዩ ሰዎች ሁሉ ያምናሉ ማለት እንደማይቻል በወንጌላትና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናነበው እውነታ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አለማመን ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ተቃውሞና ፌዝ ስድብም የሚናገሩ እንደነበሩ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጋንንትን የሚያወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ እያለ «በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል» የሚል ከባድ የስድብ ቃልን የሚናገሩ ሰዎች ነበሩ (ማቴ.12)፤ በበዓለ ሃምሳም የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ ከሰሙ ሰዎች መካከል «ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል» ብለው የሚያፌዙ ተቃዋሚዎች ነበሩ። ለዚህ ተቃሙሞአቸው ሰበብ የሚሆን ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ጉሽ የወይን ጠጅ የጠገበ ሰው ስለሚሰክር ራሱ የሚናገረው ቋንቋ እንኳ ቢሆን ጠፍቶበት እንደሚኮለታተፍና ሐሳብን በትክክል ማስተላለፍ እንደሚያቅተው ይታወቃል። እነዚያ አማኞች ግን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በተለያዩ አገሮች ልሳኖች ሲናገሩ ተሰምተዋል። አንዳንድ ጊዜ «እነዚህ የሚያፌዙ ሰዎች ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል ለማለት ያበቃቸው ሲነገሩ የሰሟቸው ልሳኖች የማይታወቁና ተናጋሪ የሌላቸው ድምፆች ቢሆኑ ነው» የሚል ሐሳብ ሲሰነዘር ይሰማል። ይሁን እንጂ በቍ.6 ላይ «እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይስማ ስለነበር የሚሉትን አጡ፤» በቍ.8 ላይ ደግሞ «...... እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?» የሚሉት ንባቦች የተሰነዘረውን ሐሳብ ውድቅ ያደርጉታል። የሚያፌዙት ሰዎች የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በገዛ ቋንቋቸው ሲነገር ሰምተዋል፤ ነገር ግን ክፉና የማያምን ልብ በግልጽ እየታየ ያለውን እውነታ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ማፌዙ አይቀርም፤ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች የሚሉትን ቢያጡ እያፌዙ «ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል» አለ፤ ነገር ግን ለዚህ ምክንያት የለሽ ከንቱ ተቃውሞ በቂ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ምላሽ አለ፤ ይህንንም ምላሽ ሐዋርያው ጴጥሮስ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲናገር ቀጥሎ እናያለን።
«ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፣ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡- አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ቃሎቼን አድምጡ። ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደለም ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል። ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁንም ሕልም ያልማል፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነም የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል» (የሐ.ሥ.2፡14-21)።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ከየአገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የመሰከረው ይህ ቃል ከእምነት በሚነሣ መንፈሳዊ ድፍረት የተነገረ ቃል ነበረ። ጴጥሮስ ጌታ ኢየሱስ በተያዘባት በዚያች ሌሊት እየማለ «ሰውየውን አላውቀውም» ብሎ ክዶ እንደነበር ስናስታውስ (ማቴ.26፡74)፣ አሁን ምን ያህል አስደናቂ ለውጥ እንደታየበት እንረዳለን። ድምፁን ከፍ አድርጎ «ይህ በእናንተ ዘንድ የተወቀ ይሁን፤ ቃሎቼን አድምጡ።» እያለ መናገሩ ያለምንም ፍርሃት መመስከሩን የሚያሳይ ነው። የምስክርነቱም ዋና ይዘት ከላይ እንደተመለከትነው «ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል» ላሉት ሰዎች የሚሆን ምላሸ ለመስጠት ነው። ይኸውም «ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደለም ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና» በሚለው ንግግሩ ይታወቃል። በዕለቱ የተሰማውም ሆነ የታየው ነገር የተከሰተው ከቀኑ ሦስት ሰዓት በመሆኑ ስካር ነው ብሎ ለመገመትም ሆነ ለማሰብ የሚያስችል አይደለም፤ በብዛት በተለመደው የሰዎች ጠባይ ቢታይ እንኳ «የሚሰክሩ በሌሊት ይሰክራሉ» (1ተሰ.5፡7) እንጂ በቀን አይደለም። ከንቱ ጥላቻ ባይኖር ኖሮ እነዚያ ተቃዋሚዎች በአእምሮቸው እንዲህ ብለው በማሰብ በክርስቶስ ደቀመዛሙርት ላይ የተከሰተው ነገር ጉሽ የወይን ጠጅ ከመጥገብ የሚመጣ ስካር እንዳልሆነ ይገነዘቡ ነበር። ጴጥሮስ የተከሰተው ነገር ስካር እንዳልሆነ በመናገር ብቻ አላበቃም፤ ነገር ግን ክስተቱ ምን እንደሆነ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ትንቢት ኢዮኤልን በመጥቀስ አስረድቷል። «ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዮኤል የተባለው ነው» ለሚለው ተቃራኒ ሆኖ የተነገረ በመሆኑ ከትንቢተ ኢዮኤል የጠቀሰው ጥቅስ በዕለቱ በአማኞች ላይ የተሰማውና የታየው ነገር ምን እንደሆነ ለማስረዳት ብቻ የጠቀሰው እንደነበር መረዳት ይቻላል። ጥቅሱ የተጠቀሰው ከኢዮ.2፡28 ሲሆን የትንቢቱ ቀጥተኛ ፍጻሜው ወደፊት በጌታ ምጽአት ጊዜ መኾኑን ከንባቡ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ጴጥሮስ ክፍሉን ሲጠቅስ «በመጨረሻው ቀን» ብሎ መጀመሩ ትንቢቱ በዋናነት የሚፈጸመው በጌታ ምጽአት መኾኑን ያመለክታል፤ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች «የመጨረሻ ቀን (ሰዓት፣ ዘመን)» የሚው ቃል አሁን ያለንበትን የቤተክርስትያን ዘመን በጠቅላላ የሚያሳይ ቢሆንም (ዕብ.1፡2፤1ዮሐ.2፡18)፣ ጴጥሮስ «የመጨረሻው ቀን» ያለው ግን ወደፊት የሚመጣውን የጌታን የምጽአት ጊዜ ነው፤ ይህም ከኢዮኤል በጠቀሰው በዚያው ክፍል «ድንቆችን በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም፣ እሳትም፣ የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅም የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ባይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ» ተብሎ በተነገረው ቃል ይረጋገጣል፤ በዚህ ክፍል በኢዮኤል የተነገሩት ክስተቶች ደም፣ የጢስ ጭጋግ በበዓለሃምሳ ዕለት እንዳልተከናወኑ፣ ከዚያ ቀድሞም ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም እንዳልተለወጡ ግልጽ ነው። ስለዚህ በኢዮኤል የተነገረው ይህ ትንቢት ወደፊት «በጌታ ቀን» ማለትም በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ የሚፈጸም መሆኑን እንገነዘባለን፤ ስለሆነም «ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ» የሚለው የትንቢት ቃል ፊደል በፊደል የሚፈጸምበት ጊዜ ጌታችን ይህ የአሁኑ ጸጋ ዘመን አብቅቶ የእርሱ የሆኑትን ወደራሱ ለመውሰድ ከመጣ በኋላ ነው። ከኢዮኤል ሌላ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር መንፈሱን እንደሚያፈስ የተናገሩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አሉ(ኢሳ.32፡15፤ 44፡3-4፤ 29፡19-21፤ ሕዝ.36፡27-28፤ 37፡14፤ 39፡29 ተመልከት)። በኢዮ. ምዕ.2፡28 «ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ጎበዞቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቼ» የተባሉት ከእስራኤል የሆኑት ቅዱሳን እንደሆኑ ከንባቡ ይዘት በግልጽ መረዳት ይቻላል። እነርሱም መካከል ወደፊት እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ሲያድስ የሚኖሩና በመሢሑ የሚያምኑ የእስራኤል ቅዱስን ናቸው፤ እነርሱም ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን በሚሰብኩት የመንግሥት ወንጌል ብዙዎች አሕዛብ በመሢሑ በሚያምኑት ላይ የሚፈስ መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ የማያምኑት ግን በፍርድ ስለሚወገዱ ከዚያ በኋላ የሚኖሩት ሥጋ ለባሾች መንፈሱ የሚፈስባቸው ብቻ ናቸው ለማለት ይቻላል።
የኢዮኤል ትንቢት በቀጥታ የሚመለከተው ይህንን ሲሆን፣ የበዓለ ሃምሳ ዕለት የወረደውና በአማኞች ላይ የፈሰሰው መንፈስ ወደፊት በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሹ ሁሉ ላይ የሚፈሰው ያው መንፈስ መሆኑን ለማስረዳት ብቻ በጴጥሮስ ሊጠቀስ ችሏል። በዚህ በኢዮኤል ትንቢት የተነገሩት መንፈስ ቅዱስ ራሱን የሚገልጥባቸው መንገዶች ማለትም የወንዶችና ሴቶች ልጆች ትንቢት መናገር፣ የጎበዞች ራእይ ማየት፣ የሽማግሌዎች ህልም ማለም፣ የሚፈጸሙት ወደፊት ነው። ቤተክርስቲያን በተወለደችበት በበዓለ ሃምሳ ደግሞ እነዚህን ነገሮች ሳይሆን የተለያዩ ልሳኖችን በመናገር ተገልጧል። ይሁን እንጂ የፈሰሰው መንፈስ ወደ ፊት የሚፈሰው ያው መንፈስ ነው፤ ይህም መንፈስ የእግዚአብሔር «መንፈሴ» ብሎ የጠራው ያው መንፈስ ነው። ስለዚህ የበዓለ ሃምሳ ዕለት «ጉሽ የወይን ጠጁ ጠግበዋል» ብለው ያፌዙ አይሁዳውያን ቢኖሩም እውነታው ግን በነቢዩ በኢዩኤል «ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ.... በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ» የተባለው ነው፤ ማለትም በዕለቱ የሆነው ነገር የእግዚአብሔር መንፈስ ስለፈሰሰ ነው እንጂ ስለሰከሩ አይደለም የሚል ምስክርነት ነው።
በበዓለ ሃምሳ የወረደው መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ መኾኑን ለማስረዳት በጴጥሮስ የተጠቀሰው ይህ የኢዩኤል ትንቢት በዘመናችን በአንዳንድ ክርስትና ክፍሎች ዘንድ እየታየ ያለውን ስሜታዊነትና የሌላ መንፈስ አሠራር ለማስረዳት ሊጠቀስ አይችልም። እግዚአብሔር የበዓለ ሃምሳ ዕለት አማኞችን በተለያዩ አገሮች ልሳኖች ያናገረ ሲሆን አሁን በአንዳንድ ስፍራ የሚታዩትና የሚሰሙት ትርጉም የለሽ ድምፆችና ፊደላት ግን ልሳኖች ሊባሉ አይችሉም። እንዲሁም በበዓለ ሃምሳ ዕለት ያልታዩ የመውደቅና የመንዘፍዘፍ ትእይንቶች በበዙባቸው ቦታዎች ያለው መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይህን መንፈስ የእግዚአብሔር ነው ለማለት የኢዮኤል ትንቢት የሚጠቀስበት አጋጣሚ ቢኖርም ይህ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሊሠራ የፈለገ የሌላ መንፈስ አሠራር እንደሆነ ሊስተዋል ይገባል። የበዓለ ሃምሳው ክስተት ከዚያ በኋላ በዚያው በሐዋርያት ዘመን እንኳ በተደጋጋሚ ሲታይ አንመለከትም። መንፈስ ቅዱስ በሌሎች ወገኖች ላይ በተገለጠ ጊዜም ቢሆን በበዓለ ሃምሳ እንደሆነ፣ ከሰማይ የመጣ ድምጽ እየተሰማና እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች እየታዩ አለመሆኑን ሁል ጊዜም ማስተዋል ጠቃሚ ነው።
2. የሐዋ.ሥ.10፡44-48«ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።»በሐዋ.ሥ.2 ላይ የተመለከትነው መንፈስ ቅዱስ ከአይሁድ ወይም ከተገረዙት ወገን ለነበሩት 120 ሰዎች እንደወረደ ነበር። ከላይ በተጠቀሰው በሐዋ.ሥ.10፡44-48 ላይ ደግሞ ለእነዚያ ከአይሁድ ለነበሩ አማኞች እንደ ወረደ ሁሉ ከአሕዛብ ለነበሩትም እንደወረደ እንመለከታለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ በራእይ ተረድቶና በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ከኢዮጴ ወደ ቂሣርያ ከሄደ በኋላ ከአሕዛብ ወገን ለነበሩት ለመቶ አለቃው ለቆርኔሌዎስና ለዘመዶቹ እንዲሁም በቅርብ ወዳጆቹ(የሐዋ.ሥ.10፡24) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለ ፈራጅነቱና ስለ አዳኝነቱ ወንጌልን ሰበከላቸው። በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ከአሕዛብ ለስሙ የሚሆንን ወገን እንደሚወስድ ያረጋገጠ ክሥተት ተከሠተ።
ጌታ ኢየሱስ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ወደ አሕዛብ ሄደው እንዲያስተምሩ ንስሐና የኃጢአትንም ስርየት እንዲሰብኩ አዝዞ ነበር (ማቴ.28፡19፤ ሉቃ.24፡47፤ የሐዋ.ሥ.1፡8)፤ ስለሆነም ወንጌል ወደ አሕዛብ እንዲደርስ ከቀድሞ ጀምሮ የእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ ነበረ። የበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የወረደው ከአይሁድ ላመኑት ቢሆንም በዕለቱ የተከፋፈሉ የአሕዛብ ልሳኖች (ቋንቋዎች) ሲናገሩ መስማታቸው እግዚአብሔር ወደ አሕዛብ የተከፈተ የጸጋ በር እንዳለው የሚያመለክት ነበር። በዚህም መሠረት ቆርኔሌዎስና ዘመዶቹ እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹ ከጴጥሮስ አንደበት የእግዚአብሔርን ቃል በሚሰሙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው፤ «ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ» የሚለውም ቃል ይህንን የሚያመለክት ነው (ቍ.44)።
ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆኑ የሚታወቁት አይሁድ ብቻ ነበሩ። ሆኖም መንፈስ ቅዱስ በእነርሱም ላይ በመውረዱ በኢየሱስ ያመኑ እስከሆኑ ድረስ አሕዛብ ቢሆኑም የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆኑ ተረጋገጠ። አሕዛብን (ያልተገረዙትን) በተመለከተ በተደረገው የኢየሩሳሌም ስብሰባ (ጉባኤ) ላይ ጴጥሮስ ይህን ሲገልጥ «ወንድሞች ሆይ አሕዛብ ከአፌ ወንጌልን ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደመረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፣ ልባቸውንም በእምነት ሲያንጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለይም» ብሏል (የሐዋ.ሥ.15፡7-9)።
የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም በኢየሱስ ያመኑ ሰዎች ብልቶች የሆኑባት አንድ አካል ናት። ይህቺም አንድ አካል የተመሠረተችው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። በ1ቆሮ.12፡13 ላይ «አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፤ ሁላችን አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።» ተብሎ የተጻፈው ቃል አይሁድንም ሆነ የግሪክ ሰዎችን (አሕዛብን) አንድ አካል ያደረጋቸው በአንድ መንፈስ መጠመቃቸውና አንድን መንፈስ መጠጣታቸው እንደሆነ የሚያስረዳ ነው። ስለሆነም በቂሣርያ በቆርኔሌዎስ ቤት መንፈስ ቅዱስ ለአሕዛበ መውረዱ ቀደም ሲል ከነበሩት አማኞች ጋር እነርሱን አንድ አካል ለማድረገ መሆኑን በግልጽ እንረዳለን። ይህንንም እውነታ ጴጥሮስ በይሁዳ ለነበሩ ወንድሞች ሲገልጥ «... ለመናገር በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው። ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለው የጌታ ቃል ትዝ አለኝ» በማለት ተናግሯል (የሐዋ.ሥ.11፡5-16)። «እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ለነጴጥሮስ (ከአይሁድ ለነበሩ) የወረደ ዕለት የተፈጸመ ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ በቂሣርያ ከአሕዛብ ለነበሩም መውረዱን ለማስረዳት ተጠቅሷል። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ የተጠመቁት በአንድ መንፈስ መሆኑ ከሁለቱ አንድ አዲስ አካል መመሥረቱን የሚያሳይ ነው፤ በኤፌ.2፡14-18 ላይ «እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም» ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና» ይላል። በዚህ ንባብ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ከሁለታቸው (ከአይሁድ እና ከአሕዛብ) አንድን አዲስ ሰው ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጧል፤ እንዲሁም ከሁለታቸው የተፈጠርነውና አዲስ ሰው የተባልነው አማኞች ወደ አብ የምንገባው በአንድ መንፈስ መሆኑም ተነግሯል። የክርስቶስ የመሞቱ ዓላማ የሆነው የዚህ እውነት ተግባሪዊ ገጽታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተፈጽሟል። ከአይሁድ ያመኑት በተጠመቁበት በዚያው በአንድ መንፈስ ከአሕዛብ ያመኑት ሲጠመቁ ይህ አንድ አዲስን ሰው ለመፍጠር የነበረው የክርስቶስ የሞቱ ዓላማ በተግባር ተከናውኗል።
ከተገረዙት ወገን የነበሩት (አይሁድ የነበሩት) አማኞች እግዚአብሔር አሕዛብን ከእነርሱ ጋር አብረው አንድ አካል እንዲሆኑ ማድረጉን መረዳት ስለነበረባቸው ከጴጥሮስ ጋር አብረው ወደ ቂሣርያ መሄዳቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር ለማለት እንችላለን። በመሄዳቸውም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብ ላይ መፍሰሱን ተጨባጭ በሆነ መንገድ ሊያረጋግጡ ችለዋል። በበዓለ ሃምሳ እንደሆነው ሁሉ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለአሕዛብ ማፍሰሱን ያረጋገጠው እነዚያን አሕዛብ በልሳኖች በማናገር ነበር። እነርሱ በልሳኖች ሲናገር መስማት ደግሞ በትክክል የእግዚአብሔር መንፈስ ልክ እንደ በዓለ ሃምሳው የወረደላቸው መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ስለሆነም ከተገረዙት ወገን የነበሩት ምዕመናን በአካል ተገኝተው ይህን ማረጋገጣቸው እግዚአብሔር የተቀበላቸውን አሕዛብ እነሱም ከልባቸው እንዲቀበላቸው ያደርጋቸዋል፤ በቍ.45 ላይ «ጴጥሮስ ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና» የሚለው ቃል እንደሚያስረዳው ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች ባዩት ነገር ስለተገረሙ ክስተቱ አሕዛብን ከልባቸው ለመቀበል ያስችላቸዋል ማለት ነው።
በቂሣርያ መንፈስ ቅዱስ የወረደላቸው አማኞች ሲናገሩዋቸው እግዚአብሔርን ሲያከብሩባቸው የተሰሙት ልሳኖች በጠባያቸው በበዓለ ሃምሳ ሲነገሩ ከተሰሙት የተለየ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም፤ «ልሳኖች» የሚለው በብዙ ቍጥር የተነገረ ቃል ሲሆን የተሰሙ ነገሮች የተለያዩ (የተከፋፈለ) ቋንቋዎች እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። እንዲሁም በልሳኖቹ የሚያስተላልፉት አንዳች መልእክተኛ የራሳቸው የሆነ የቋንቋ ይዘት እንደነበራቸውም «በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና» የሚለው ቃል በግልጽ ያሳያል። «በልሳኖች ሲናገሩ» ስለሚል ልሳኖቹ ንግግር (መናገር) መሆናቸው እንጂ ምላስና ከንፈርን እንደፈለጉ በማርገብገብ የሚፈጠሩ ትርጉም የለሽ ድምፆች አለመሆናቸው በግልጽ ይታያል። እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ እንደነበር መስማታቸው በልሳኖች ከመናገራቸው ጋር ተያይዞ መገለጡ ደግሞ በእነዚያ ልሳኖች የተነገረው ዋና ይዘት እግዚአብሔርን ማክበር (ማመስገን) እንደነበር የሚያስረዳ ነው። በበዓለ ሃምሳ «የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን» ተብሎ የተነገረው ቃል ልሳኖቹ የቋንቋ ይዘት ያላቸው መሆኑን እንዳመለከተ ሁሉ በዚህ ክፍልም «በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና» የሚለው አገላለጽ የተነገሩት ልሳኖች መልእክት የሚያስተላልፉ ቋንቋዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በበዓለ ሃምሳ ቀን የኢየሩሳሌም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከተከሰተው ነገር በቂሣርያ ያልታየው «ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ» ሆኖ ከሰማይ የመጣው ድምጽ እና የልሳኖቹ እንደ እሳት ተከፋፍሎ መታየት ነው። በበዓለ ሃምሳ ይህ የሚሰማና የሚታይ ነገር ሊከሰት የቻለው መንፈስ ቅዱስ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ መውረዱ ስለነበረ ያንን የእርሱን መምጣት ለማብሰር ነው። በቂሣርያ ግን በኢየሩሳሌም የበዓለ ሃምሳ ዕለት ከሰማይ የወረደው ያው መንፈስ የወረደ በመሆኑና ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰማይ መምጣቱ ባለመሆኑ እነዚህ ክርስተቶች ያላስፈለጉ መሆናቸውን እንገነዘባለን። በኢየሩሳሌም፣ በቂሣርያም ሆነ በሌሎች ቦታዎች መንፈስ ቅዱስ ወረደ ሲባል እንደገና ወደ ሰማይ ወጥቶ፣ ወረደ ማለት ሳይሆን በዚያ ስፍራ ባሉ አማኞችም ውስጥ ገባ በመካከላቸውም አደረ ማለት ነው።
በበዓለ ሃምሳ በኢየረሳሌም ከአይሁድ ለነበሩት አማኞች መንፈስ ቅዱስ የወረደው ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ላይ እያለ ነበር፤ በዚህ በቂሣርያ ለነበሩት ግን የወረደው ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ቃል ገና ሲናገር ነበር። ይህም መንፈስ ቅዱስ የወረደው በአንድ ዓይነት መንገድና ባንድ ዓይነት ጊዜ እንዳልነበረ የሚያሳይ ነው። ከዚህም ሌላ በቂሣርያ የአሕዛብ የሆኑትና ወንጌልን የሰሙት ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በውኃ ከመጠመቃቸው በፊት እንደሆነም በግልጽ ተነግሮናል። «በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፡- እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማነው?» የሚለው ቃል ይህንኑ ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች በውኃ የተጠመቁት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነበር። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከውኃ ጥምቀት የበለጠ መለኮታዊ ክስተት ነው፤ ከዚህም አንጻር ጴጥሮስ ትልቁን ነገር ያገኙትን እነዚህን ሰዎች ከዚያ ያነሰውን የውኃ ጥምቀት ሊከለክላቸው የሚችል እንደሌለ በመናገር «በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው» (ቍ.48)፤ የውኃ ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ተከትሎ የሚከናወን ሥርዓት መሆኑ የታወቀ ነው (ማር.16፡16፤ ሐዋ.ሥ.8፡36-38)፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከውኃ ጥምቀት በበለጠው በመንፈስ ቅዱስ ስለተጠመቁ በውኃም እንዲጠመቁ ታዘዋል። በመሆኑም አስቀድሞ በቆርኔሌዎስ ቤት ጴጥሮስ የሰበከላቸውን ወንጌል በሰሙ ጊዜ ልባቸው መለወጡንና በኢየሱስ ማመናቸውን እግዚአብሔር እንዳየ እንገነዘባለን፤ መንፈሱን በእነርሱ ላይ በማውረድ ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው።
በዘመናችን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አብዝቶ መጸለይ ወይም የውኃ ጥምቀት ወይም ልዩ የሆነ መጠማት አስቀድሞ እንደሚያስፈልግ በየስፍራው የሚነገሩት የስህተት ትምህርቶች በቅዱሳት መጻሕፍት የሚታየውን የመንፈስ ቅዱስ አሠራር በውል ባለመረዳት ወይም ባለመቀበል የሚመጡት ናቸው። መንፈስ ቅዱስ ወደ አንድ ሰው የሚገባው ያ ሰው በክርስቶስ ስላመነ ነው እንጂ ሰው ስለተጠመቀ ወይም ልዩ የሆነ ጾምና ጸሎት ስለያዘ ወይም ታዋቂ ሰዎች ስለ ጸለዩለት አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ በበዓለ ሃምሳ ቀን በኢየሩሳሌም፣ እንዲሁም በቂሣርያ መንፈስ ቅዱስ ለመውረዱ ምልክት የነበረው በልሳኖች የመናገር ስጦታ በሁሉም ቦታ ለሁሉም አማኞች የግድ እንዳልነበረ ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ በሰማርያ የነበሩ አማኞች መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ጊዜ አንዳች የታየ ምልክት ስለመኖሩ የምናነበው ቃል የለም (ሐ.ሥ.8፡14-17)፤ እኛም መንፈስ ቅዱስን ስንቀበል እነዚያ ምልክቶች ባይታዩም በኢየሱስ ባመንን ጊዜ መንፈስ ቅዱስን መቀበላችንን ልናውቅ ይገባል።
3. የሐዋ.ሥ.19፡1-7«አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ አንዳንድ ደቀመዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም አልተቀልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው እነርሱም በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በልሳኖችም ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር።»በልሳኖች ስለመናገር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ለመጨረሻ ጊዜ የምናነበው በዚህ ክፍል ነው፤ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን አገልግሎቱን ገና እንደጀመረ የታየውን በልሳን የመናገር ምልክት በተመለከተ የሚናገር ንባብ ነው። ጳውሎስ በ2ኛው የስበከት ጉዞ ማብቂያ ላይ ወደ ኤፌሶን ቢደርስም ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ስለነበረበት በዚያ ያገኛቸውን ሰዎች «እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደ እናንተ እመለሳለሁ» ብሎአቸው ነበረ (የሐ.ሥ.18፡21)። እግዚአብሔርም ፈቅዶ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን በተመለሰ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛቸው በመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት ብቻ የተጠመቁ 12 ደቀመዛሙርትን ነበር። ጳውሎስ እነዚህን ደቀመዛሙርት «ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?» የሚል ጥያቄን አቀረበላቸው፤ ይህን ጥያቄ ልብ ብለን ስንመለከት ሰው መንፈስ ቅዱስን የሚቀበለው ኢየሱስን በትክክል ባመነ ጊዜ እንደሆነ ጠያቂው ጳውሎስ ማረጋገጡን እንረዳለን። በእርግጥ እነዚያ ጥያቄው የቀረበላቸው ደቀመዛሙርት እምነታቸው የተሟላ አልነበረም፤ መጥምቁ ዮሐንስ ስለኢየሱስ የመሰከረውን ያመኑ ቢሆኑም ኢየሱስ ስለበደላችን እንደሞተና እኛን ስለማጽደቅ እንደተነሣ የሚያምኑ አልነበሩም። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስን ሊቀበሉ አልቻሉም፤ እንዲያውም ራሳቸው እንደገለጹት መንፈስ ቅዱስ እንዳለ እንኳ አልሰሙም። ይህም ሁኔታ እነርሱ ገና አይሁዳውያን የሆኑ የመጥምቁ ዮሐንሰ ደቀመዛሙርት ብቻ እንጂ ክርስቲያኖች እንዳልነበሩ በግልጽ የሚያሳይ ነው፤ ጳውሎስም በመረገም «እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ?» የሚል ቀጣይ ጥያቄ ያቀረበላቸውም በጥምቀታቸው የመሰከሩት እምነት የትኛው እምነት መሆኑ እንዲታወቅ ነበር። የመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር እንጂ በኢየሱስ ማመንን የሚያመለክት አልነበረም። ስለዚህም እነዚያ ደቀመዛሙርት በጌታ በኢየሱስ ስም መጠመቅ ነበረባቸው። በኢየሱስ ስም መጠመቅም ስለኢየሱስ የተሰበከውነ ወንጌል ተቀብለው በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሙለውን እምነት እንደያዙና የእርሱም ደቀመዛሙርት እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ይህን እምነት ያመኑት ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ባገኛቸው ጊዜ ስለ ነበር መንፈስ ቅዱስ የወረደላቸው እርሱ እጁን በጫነባቸው ጊዜ ነበር። ጳውሎስ እጅን እስኪጭንባቸው ድረስ መንፈስ ቅዱስ ያልወረደላቸው የጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣኑ በእነርሱ ፊት እንዲረጋገጥ ነው፤ «ጳውሎስም እጅን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው» የሚለው አገላለጽ በወቅቱ የተከናወነው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የጳውሎስን ማንነት ማለትም በእግዚአብሔር የተላከ ሐዋርያ መሆኑን የማረጋገጥ ዓላማ እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሐ.ሥ.8፡14-20 ያለውን ክፍል ስናነብ በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ ሲሰጥ እናያለን። የሰማርያ ሰዎች ወንጌላዊው ፊልጶስ የሰበከላቸውን ወንጌል ተቀብለው በጌታ በኢየሱስ አምነው ቢጠመቁም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደዚያ እስኪሄዱ ድረስ መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበር፤ ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ከጸለዩላቸው በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ ሲሞን የተባለው ሰው ይህን የሐዋርያነትን ሥልጣን በገንዘብ ሊገዛ መሞከሩን ሲገልጥ «ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ» ብሏል። በዚህ አነጋገር ውስጥ ጸሐፊው «በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ» ብሎ የገለጸውን ስንመለከት መንፈስ ቅዱስ የተሰጠው እጅ የጫኑት ሐዋርያት በመሆናቸው መኾኑን እንረዳለን። ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌሶን ባገኛቸው 12 ደቀመዛሙርት ላይ እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የወረደው ጳውሎስ ከእግዚአብሔር የተላከ ሐዋርያ እንደሆነ ለእነዚያ ደቀመዛሙርት ለማረጋገጥ መሆኑን በዚህ እንገነዘባለን። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲሁም ጳውሎስ እጅ በጫኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ በዚህ ዘመን በየስፍራው እጅ በመጫንና ሰዎችን በመጣል ከእግዚአብሔር ያልሆነውን መንፈስ በሰዎች ውስጥ ለሚሞሉ አገልግሎቶች በማስረጃነት ሊጠቀስ አይችልም፤ ምክንያቱም በዘመናችን እጅ የሚጭኑት ሰዎች ሐዋርያት አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም፤ ምክንያቱም ሐዋርያት አሁን የሚገኙት በላይ በሰማያት ከክርስቶስ ጋር እንጂ በዚህ ምድር ላይ አይደለም። እግዚአብሔር ከ12ቱ ሐዋርያትና ከጳውሎስ በቀር ለቤተክርስቲያን ሌላ ሐዋርያ አልሰጠምና፤ በሐዋርያት ስም የሚመጡ ውሸተኞች ሐዋርያት በየጊዜው ቢነሱም እውነተኞቹ ሐዋርያት ግን እነዚያው የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ብቻ ናቸው።
ጳውሎስ ግን ሐዋርያ ስለነበረ እነዚያ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት የነበሩ ሰዎች የተሰጠውን የሐዋርያነት ሥልጣን ቅዱስን ሊቀበሉ ችለዋል። ይህም የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በእነርሱ ላይ በታዩት የልሳንና የትንቢት ተአምራዊ ምልክቶች ተገልጧል። «በልሳኖችም ተናገሩ ትንቢትም ተናገሩ» የሚለው ቃል «ጳውሎስ እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው» የሚለውን ዓረፍተ ነገር ተከትሎ መነገሩ እነዚህ ተአምራዊ ምልክቶች መንፈስ ቅዱስ ራሱን የገለጠባቸውና የጳውሎስን ሐዋርያነት ያረጋገጠባቸው ምልክቶች መሆናቸውን የሚያመለክት ነው (2ቆሮ.12፡12፤ ማር.16፡17-20)። ሆኖም ከዚያ በኋላ ጳውሎስ በኤፌሶን በቆየባቸው 3 ዓመታት እያንዳንዱ አማኝ መንፈስ ቅዱስን እርሱ እጁን ይጭንበት ነበር ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል።
በልሳኖች መናገር በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት
በቆሮንቶስ ላለች የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከተጻፉት ሁለት የጳውሎስ መልእክታት መካከል የመጀመሪያቱ የቆሮንቶስ መልእክት በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የታዩት ስህተቶች እና ውድቀቶች እንዲታረሙ ለማድረግ የተጻፈች መልእክት ናት። በተለይም በማኅበር ደረጃ ሁሉም ተጠያቂ በሆኑባቸው የተለያዩ ውድቀቶች እንዲገሠጹና እንዲታረሙ የተጻፈች ናት። አያንዳንዳቸው «እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፣ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፣ እኔስ የክርስቶስ ነኝ» የሚል ክርክር በመካከላቸው ነበር (1፡12)፤ እንዲሁም በመካከላቸው ዝሙት ነበር(5፡1)፤ በመካከላቸው ልዩነት እያለ እንጀራ ይቈርሱ ነበር (10፡21፤ 11፡17) የእግዚአብሔርን ማኅበር በመናቅ አንድ ሲራብ ሌላው እየሰከረ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላ ነበር (11፡21)፤ ሲሰበሰቡም ለማኅበሩ መታነጽ የተሰጡትን በልሳኖች የመናገርና ትንቢት የመናገር ስጦታዎችን በአገባብና በሥርዓት አይጠቀሙባቸውም ነበር (14፡39-40)።
ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ ውድቀቶች እያነሣ ከገሠጻቸው በኋላ መፍትሔውን በማስቀመጥ እያስተማረ ጽፎላቸዋል፤ ይህም በቤተክርስቲያን ዘመን ሁሉ በየስፍራው ለምትገኝ ለእያንዳንዷ ቤተክርስቲያን (ማኅበር) በመመሪያነት የሚያገለግል ነው፤ በተለይም በዘመናችን በክርስትናው ዓለም ውስጥ እነዚህን ሁሉ ውድቀቶች የምናገኝ ሲሆን በይበልጥ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ ከያዝነው ርዕስ አኳያ በልሳኖች መናገርን በተመለከተ የተጻፈልንን ትምህርት በዝርዝር እንመለከታለን።
በዚህች መልእከት ውስጥ ልዩ ልዩ የጸጋ ስጦታዎችን በተመለከተ ተጽፎ የምናገኘው ከምዕ.12 እስከ ምዕ.14 ድረስ ነው፤ ሆኖም አሁን እኛ እያጠናን ያለነው በልሳኖች መናገርን በተመለከተ የተነገረውን ብቻ ስለሆነ በእነዚሁ ምዕራፎች ውስጥ ስለዚሁ ስጦታ ብቻ የተነገረባቸውን ንባቦች እያነሣን፣ ቃሉ በትክክል የሚለውንና በዘመናችን የሚታየውን እያነጻጸርን እንመለከታለን።
1. 1ቆሮ.12፡4-11ሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፣ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፣ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፣ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፣ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፣ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፣ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል»
ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል መሆንዋ በዚሁ በ1ኛይቱ የቆሮንቶስ መልእክትም ይሁን በሌሎች የጳውሎስ መልእክታት በግልጽ ተጽፏል (ሮሜ.12፡4-5፤ 1ቆሮ.12፡12-27፤ ኤፌ.1፡22-23፤ ቈላ.1፡18ና24)። አካል አንድ ሆኖ ሳለ ብዙ ብልቶች አሉት፤ የብልቶቹም ሥራ አንድ አይደለም። በ1ቆሮ.12፡27 ላይ «እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።» ተብሎ እንደተጻፈ አማኞች እያንዳንዳቸው በክርስቶስ አካል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብልቶች ናቸው። የብልቶቹ ሥራ አንድ እንዳይደል ሁሉ አማኞች እያንዳንዳቸው ያላቸው አገልግሎት (ሥራ) የተለያየ ነው። በክርስቶስ አካል ውስጥ አገልግሎት የሚከናወነው ደግሞ ለእያንዳንዱ አማኝ በተሰጠው ጸጋ መሠረት ነው፤ ስለዚህ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጠው የጸጋ ስጦታም ልዩ ልዩ ነው። «የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው» የተባለውም ለዚህ ነው። በሮሜ.12፡6 ላይም «እንደተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን» ተብሎ ተነግሯል። የጸጋ ስጦታዎቹ የተለያዩ ይሁኑ እንጂ እነርሱን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው። መንፈስ ቅዱስ ልዩ ልዩ የጸጋ ስጦታዎችን ለእያንዳንዱ አማኝ እንደሚሰጥ ማመን፣ በሰዎች ስለተሾሙ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶች ስለሠለጠኑ ብቻ እንዲህ ያለ ጸጋና አገልግሎት አለኝ እያሉ ከመሳሳት ያድናል። የጸጋ ስጦታዎቹ ልዩ ልዩ ቢሆኑም ዓላማቸው ግን አንድ ነው፤ ያም መላውን የክርስቶስን አካል መጥቀም ነው፤ እንዲሁም ስጦታዎቹ በአገልግሎት ላይ /pሲውሉ መንፈስ ቅዱስን ይገልጡታል፤ «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል» የሚለው ቃል ይህን የሚያስረዳ ነው።
- 1.
- ጥበብን መናገር 2.
- እውቀትን መናገር 3.
- እምነት 4.
- የመፈወስ ስጦታ 5.
- ተአምራትን ማድረግ 6.
- ትንቢትን መናገር 7.
- መናፍስትን መለየት 8.
- በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር 9.
- በልሳኖች የተነገረውን
ከእነዚህ ስጦታዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ተአምራዊ ያልሆኑ ስጦታዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 6ቱ ግን ተአምራዊ ስጦታዎች ናቸው። ከስጦታዎቹ ሁሉ በመጨረሻ የተዘረዘሩት ደግሞ «በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር እና «በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም» ናቸው። እንደዚሁም የጸጋ ስጦታዎች ቅደም ተከተል በይበልጥ በግልጽ በሚታይበት በ1ቆሮ.12፡28 ላይም በልሳኖች መናገር እና መተርጐም በመጨረሻ ተቀምጠዋል። ይህም አቀማመጥ ተአምራዊ ስጦታዎችን በተለይም የልሳን ስጦታን ሁልጊዜ ከሌሎች ይልቅ አስቀድመውና አስበልጠው ለሚመለከቱ ሁሉ ትምህርት የሚሰጥ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ያስቀመጠውን ወደ መጨረሻ ወስዶ መጨረሻ ያስቀመጠውን ወደ መጀመሪያ ማምጣት የመንፈስ ቅዱስን ትኩረትና አሠራሩን አለመረዳትን ነው። ስለሆነም በልሳኖች የመናገርና በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታን መንፈስ ቅዱስ በመጨረሻ ላይ ያስቀመጠው በመሆኑ በመጀመሪያ ከተቀመጡትና ተአምራዊ ካልሆኑት ከሌሎች ስጦታዎች ማለትም ጥበብን ከመናገር፣ እውቀትን ከመናገርና ከእምነት ይልቅ የአማኞችን ትኩረት ሊስብ አይገባም፤ አንዳንድ ጊዜ አማኙ መንፈስ ቅዱስ መሞላቱን ለማረጋገጥ ከሚል የተሳሳተ መነሻ በመነሣት «በልሳን ትጸልያለህን?» ተብሎ ሲጠየቅ የምንሰማው ከሌሎች ስጦታዎች ይልቅ በልሳኖች ለመናገር የቅድሚያ ትኩረት በሚሰጥበት ጊዜ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። የጸጋ ስጦታ ማለት በልሳኖች መናገር ብቻ እስኪመስል ድረስ በዘመናችን የብዙዎች አማኞች ትኩረት በልሳኖች የመናገር ስጦታ ላይ ለዚያውም እውነተኛ ባልሆኑና ልሳኖች ተብለው ሊጠሩ በማይችሉ የሐሰት ልሳኖች ላይ መሆኑ የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ ስጦታ ዝርዝር ቅደም ተከተል ለተረዱ ሁሉ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።
በዚህ በያዝነው ንባብ ውስጥ ልሳኖችን የሚመለከቱ ሁለት ዓይነት ስጦታዎች እንዳሉ እናያለን፤ እነርሱም «በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር» እና «በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም» ናቸው። ይህም የሆነው በ1ኛ የቆሮንቶስ መልእክት ውስጥ የተገለጠው በልሳኖች የመናገር ስጦታ በጉባኤ በመካከል የሚነገሩና ሰሚዎቹ የማያውቋቸውን የባዕድ ልሳኖችን የሚመለከት በመሆኑ ነው። ይህንንም በ1ቆሮ.14፡22 ላይ የምንረዳ ሲሆን እግዚአብሔር በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የባዕድ ልሳኖች እንዲነገሩ ያደረገ ለምን እንደሆነ ወደፊት በንባቡ ላይ ስንደርስ እንመለከተዋለን። በሐዋ.ሥ.ምዕ2. ላይ የምንመለከተው በልሳኖች መናገር ተናጋሪዎቹ ከዚያ በፊት የማያውቋቸው ነገር ግን የሰሚዎቹ ቋንቋዎች የሆኑ ልሳኖች የተነገሩበት ነው፤ በሐዋ.ሥ. ምዕ.10፡46 እና ምዕ.19፡6 ላይ ደግሞ በልሳኖች የተናገሩት የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙትና በኢየሱስ ያመኑት ሰዎች በመሆናቸው ለተናጋሪዎቹ ባዕድ የሆኑ ልሳኖችን እንደተናገሩ መረዳት ብንችልም ለሰሚዎቹ ግን ባዕድ ይሁን ወይም አይሁን ማወቅ አንችልም፤ ልሳኖቹ የተነገሩት አማኞች በጉባኤ (በቤተክርስቲያን) ለመተናነጽ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳይሆን ሰዎቹ ገና እንዳመኑ መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ የተናገሩአቸው ልሳኖች በመናገራቸው ዋና ዓላማቸው ቃሉን ለማጽናትና የሐዋርያትን ሥልጣን ለማስረገጥ በምልክትነት ማገልገል ነበር። በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት ውስጥ የምናነበው ግን ጉባኤውን ለማነጽ ስለተሰጡ ልሳኖች ነው። ልሳኖቹ ለማኀበሩ (ለሰሚዎቹ) ባዕዳን በመሆናቸው ማኀበሩ እንዲታነጽ በልሳኖች የተነገረው መተርጐም አለበት፤ ስለሆነም ስጦታው በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር ብቻ ሳይሆን በልሳኖች የተነገረውን መተርጐምም ሊሆን ቻለ።
«በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር» ሲል በምድር ላይ የሌለና የሚናገሩበት ሰዎች የሌሉት ቋንቋ ማለት አይደለም፤ በልሳኑ ለሚናገረውም ሆነ ልሳኑን ለሚሰሙት ሰዎች እንግዳ ወይም ሌላ ልሳን (ቋንቋ) እስከሆነ ድረስ ልዩ ዓይነት ልሳን ነው፤ ልሳኑ ግን በምድር ካሉት ቋንቋዎች አንዱ ነው። በሐዋርያት ሥራ ውስጥም ሆነ በ1ኛ የቆሮንቶስ መልእክት ውስጥ የተነገረለት በልሳኖች የመናገር ስጦታ ተናጋሪዎች ባላቸውና በምድር ላይ ባሉ በሌሎች ቋንቋዎች መናገርን የሚያመለክት መሆኑ ምንጊዜም መዘንጋት የለበትም፤ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በልሳኖች ስለመናገር የተጻፈው ሁሉ የሰዎች ቋንቋን የሚያመለክት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።
በልሳኖች መናገርና በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች ሆነው መገለጻቸው በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በልሳኖች የመናገር ስጦታ ኖሯቸው የመተርጐም ስጦታ የሌላቸው ሰዎች እንደ ነበሩ ያሳያል፤ ይህም ማለት እግዚአብሔር በልሳኖች የመናገር ስጦታውን ሰጥቶ የመተርጐም ስጦታውን ያልሰጠበት ሁኔታ ነበረ ማለት ነው። በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ በልሳኖች ለሚናገረው ሰው ለራሱ ወይም ለሌላ አማኝ ሊሰጥ ይችላል። በ1ቆሮ.14፡13 «ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጐም ይጸልይ» ሲል በልሳን የመናገር ስጦታ የተሰጠው ራሱ መተርጐሙም ሊሰጠው ይችል እንደነበር ሲያመለክት በ1ቆሮ.14፡27 «በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ፤ አንዱም ይተርጉም» በሚለው ቃል ውስጥ «አንዱም ይተርጐም» ሲል ከተናጋሪው ሌላ የሆነ ሌላ ሰው የመተርጐም ስጦታ ይሰጠው እንደነበር የሚያመለክት ነው። በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታም ያስፈለገበት ምክንያት በአማኞች ማኅበር (በቤተክርስቲያን) መካከል በተአምራዊ መንገድ ይነገሩ የነበሩ የውጭ (የባዕድ) ቋንቋዎች የሚያስተላልፉት መልእክት በሰሚዎቹ ቋንቋ ተነግሮ ሰሚዎቹ እንዲያውቁትና እንዲታነጹ ለማድረግ ነበር፤ ይህም 1ቆሮ.ምዕ.14ን ስናጠና የምንመለስበት ይሆናል።
2. 2ቆሮ.12፡27-31«እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፣ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፣ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል። ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጐማሉን? ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።»
በቆሮንቶስ የነበረች የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በመላይቱ አንዲት አካል ውስጥ የምትገኝ የክርስቶስ አካል ስትሆን በጊዜው የነበሩት እያንዳንዳቸው አማኞችም ብልቶች ናቸው፤ ይህ እውነታ በዘመናት ሁሉ እና በስፍራ ሁሉ የምትገኘውን እያንዳንዷን አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚመለከት እውነታ ነው። «ብልቶች» ተብለው የተገለጡት እያንዳንዳቸው አማኞች ሲሆኑ በአንድነት ሆነው የክርስቶስን አካል የሚገልጹት በየስፍራቸው በጌታ በኢየሱስ ስም ሲሰበሰቡ ነው። እነዚያም በየስፍራው የተሰበሰቡበት ጉባኤያት በመላይቱ አንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመላይቱ ቤተክርስቲያን የተሰጡትና የሚሰጡት ስጦታዎች ለእነርሱም የተሰጡ ስጦታዎች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በቍጥር 28 ላይ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ያደረጋቸው (ያኖራቸው) ስጦታዎች በቅደም ተከተል ተዘርዝረውልናል። በዚህም ቍጥር ላይ «በቤተክርስቲያን» ሲል ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ጌታችን ለቅዱሳኑ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ በየስፍራው የሚኖሩ እውነተኛ አማኞችን ብቻ በብልትነት የያዘችውን መላዋን አንዲት ቤተክርስቲያን የሚያመለክት ነው። በእርስዋም ውስጥ እግዚአብሔር ያደረጋቸው (ያኖራቸው) ስጦታዎች ለሁሉም ጉባኤዎች የተሰጡ ሲሆኑ እነርሱም አስቀድሞ ሐዋርያት፣ ሁለተኛም ነቢያት፣ ሦስተኛም አስተማሪዎች፣ እርዳታም፣ አገዛዝም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችም ናቸው። እዚህ ላይ በቅደም ተከተል ከተቀመጡት ስምንት ስጦታዎች መካከል በመጀመሪያ የተገለጹት «ሐዋርያት» ሲሆኑ በመጨረሻ የተገለጹት ደግሞ «የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖች» ናቸው። በጸጋ ስጦታዎች ዝርዝር ውስጥ ሐዋርያት በመጀመሪያ መጠቀሳቸው የተለመደ እንደሆነ ሁሉ (ኤፌ.4፡11)፣ በልሳኖች መናገርም በመጨረሻ መቀመጣቸው የተለመደ ነው (1ቆሮ.12፡10 እና ቍ.30)። መንፈስ ቅዱስ ይህን ማድረጉ ሊሰጠን የሚችለውን ትምህርት አስቀድመን ስለተመለከትን እዚህ ላይ መድገሙ አስፈላጊ አይደለም።
በዚህ ክፍል እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ያደረጋቸው (ያኖራቸው) ልሳኖች «ልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖች» ተብለው ተገልጠዋል። ይህም አገላለጽ ስጦታው በነበራቸው የተለያዩ አማኞች ይነገሩ የነበሩት ልሳኖች ዓይነታቸው ልዩ ልዩ እንደነበር ያስረዳል። የሐዋ.ሥ.2ን ስናጠና እንደተመለከትነው በበዓለ ሃምሳ ዕለት የ15 አገሮች ቋንቋዎች (ልሳኖች) ተነግረው ነበር። ልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖች ቢባልም የተለያዩ አገሮች እና ሕዝቦች የሚናገሯቸው የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚያመለክት ነው። በቆሮንቶስ በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥም ይነገሩ የነበሩት ለስሚዎቹ ባዕድ የሆኑ ነገር ግን ተናጋሪ ያላቸው የተለያዩ ቋንቋዎች መሆናቸውን ከዚህ እንረዳለን፤ በዘመናችን የሚሰሙት ግን አንዳንዶች ሦስት ወይም አራት የፈጠራ ቃላትን እየደጋገሙ እና የተወሰኑ ፊደሎችን ብቻ እየቀያየሩ የሚያሰሟቸው፣ ወይም ከሰው ወደ ሰው በኩረጃ የሚተላለፉ፣ ወይም አእምሮን በመሳት የተፈጠረ ሥርዓት አልባና ትርጉም የለሽ ድምፆች በመሆናቸው ልዩ ልዩ ልሳኖች እንዳልሆኑ ማወቅ ይቻል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጥራዝ ነጠቅ የሚታወቁ እንደ እግዚአብሔር ስም ያሉ አንዳንድ የሌሎች ቋንቋዎች ቃላትን ሆን ብሎ በማስገባት እውነተኛ ልሳኖች ለማስመሰል ቢሞከርም በተናጋሪዎቹ በራሳቸው ቋንቋና በሃሌ ሉያ እየታገዙ የሚነገሩ የተቈራረጡና የሚደጋገሙ እንዲሁም ሙሉ ሐሳብንና መልእክትን መግለጽ የማይችሉ ስለሆኑ «ልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖች» ሊባሉ አይችሉም፤ አይደሉምም።
«ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጐማሉን?» የሚለው ቃልም በአንዳንዶች ዘንድ አማኞች ዘንድ አማኞች መዳናቸው
የሚታወቀው፣ በሌሎች ዘንድ ደግሞ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ መጠመቃቸው የሚታወቀው «በልሳኖች ሲናገሩ ነው» ተብሎ የሚታመነውን የሐሰት ትምህርት ከሥሩ የሚነቅል ከመሠረቱ የሚንድ ነው። ምክንያቱም «ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን?» ለሚለው ጥያቄ መልሱ «አይደሉም» የሚል ከሆነ «ሁሉ በልሳኖች ይናገራሉን? የሚል መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ነው። በ1ቆሮ.12፡11 ላይ «ይህን ሁሉ ግን አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል» ተብሎ የተጻፈው ቃልም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው። ስለሆነም በልሳኖች መናገር ለሁሉ ስለማይሰጥ የመዳንም ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምልክት አይደለም።
- 3. 1ቆሮ.13፡1
«በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽው ጸናጽል ሆኜአለሁ።»
በቀደመው ምዕራፍ ማለትም በምዕ.12 መጨረሻ ላይ እንደምናነበው ሐዋርያው ጳውሎስ «ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ» ብሎ ነበር(ቍ.31)። በዚህም መሠረት በ1ቆሮ.13 ከጸጋ ስጦታዎች ሁሉ ስለሚበልጠው ስለፍቅር ጽፎላቸዋል፤ ከቍ.1-3 ያለውን ስናነብ 4 የጸጋ ስጦታዎች ማለትም በልሳን የመናገር፣ የትንቢት፣ የእውቀት፣ የእምነት ስጦታዎች ከፍቅር ጋር ተነጻጽረው የቀረቡ ሲሆኑ እነዚህ ሁሉ የጸጋ ስጦታዎች ፍቅር ከሌለ ከንቱ መሆናቸው ተገልጿል። እዚህ ላይ በተለይ የምንመለከተው ግን የሰዎችና የመላእክት ልሳንን በተመለከተ ይሆናል።
«በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር» የሚለው አገላለጽ ከማንም በበለጠ በልሳን የመናገር ስጦታ ቢኖረን ከሰዎችም አልፈን የመላእክትን ቋንቋ እንኳ መናገር ብንችል ለማለት የቀረበ ግነታዊ አገላለጽ ነው። እንደዚሁም ይህ ንባብ በቆሮንቶስ አማኞችም ሆነ በሐዋርያው ዘንድ የሚታወቀው ልሳን፣ ተናጋሪ ባለቤት የሌለው፣ ምላስና ከንፈር በድንገት በመርገብገብ የሚፈጥሩት ድምጽ ሳይሆን ተናጋሪ ባለቤት ያለው ልሳን(ቋንቋ) እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። በዘመናችን የሰዎችን ልሳን እንደማይናገሩ በኅሊናቸው ያለውን እውነት መካድ ባልቻሉና ለመቀበልም በተገደዱ ሰዎች «የምንናገረው ልሳን ሰዎች ባይናገሩበትም ምናልባት የመላእክት ቢሆንስ» የሚል ሐሳብ ሲሰነዘር ይሰማል፤ ይህ ሐሳብ በዘመናችን ልሳን ተብሎ ሲነገር የሚሰማውን ነገር የመላእክት መኾን አለመኾኑን ሰው ሊያረጋግጥ እንደማይችል አስቀድሞ በመገንዘብ የቀረበ የመከራከሪያ ሐሳብ ከመሆን አያልፍም። ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የመላእክትን ልሳን እናገራለሁ» ለማለት አይደለም፤ ቃሉ «ብናገር» ይላል እንጂ «እናገራለሁ» ወይም «ተናግሬአለሁ» አይልም። ስለሆነም ንባቡ ሰዎች በገዛ ስሜታቸው የፈጠሯቸው ድምፆች ምናልባት የመላእክት ሊሆኑ
«የመላእክት ልሳን» እዚህ ላይ የተነሣበት ምክንያት «ይህን ያህል ስጦታ እንኳ ቢሰጠኝ» ብሎ የልሳኑን ዓይነት አግንኖ ለማቅረብ ነው፤ በመዝ.8፡4-5 «ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው» ተብሎ እንደጻፈው ሰው ከመላእክት ያንሳል፤ መላእክት ደግሞ ከሰው ይበልጣል። ታዲያ አንድ ሰው በሰዎችና በመላእክት ልሳን ቢናገር የሰዎችን ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች የሚበልጡትን የመላእክትን ቋንቋ በመናገሩ የተሰጠው በልሳኖች የመናገር ስጦታ ከፍ ያለ ደረጃ አለው ማለት ነው፤ ፍቅር ከሌለ ግን ይህ ከፍ ባለ ደረጃ የተሰጠው በልሳኖች የመናገር ስጦታ ከንቱ ነው። አንድን ጸጋ ወይም አገልግሎት ወይም ክብር ወይም ሌላ መልካም ነገር በሰዎች ዘንድ ካለው ሁኔታ ጋር በተነጻጻሪነት ማሳየት በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው። ለምሳሌ በመዝ.77(78)፡25 ላይ «የመላእክትን እንጀራ ሰው በላ» ሲል መላእክት ከሚኖሩበት ሰማይ የወረደው መና (እንጀራ) ከእነርሱ ላነሰው ለሰው መስጠቱን ለማሳየት ነው፤ በገላ.1፡8 ላይም «ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።» የሚለው ቃል ከሰዎች የሚበልጠው መልአክ ሰብኮታል ብለው ልዩ ወንጌልን እንዳይቀበል ለማሳሰብ የተጻፈ ነው፤ በገላ.4፡4 ላይም «.... ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁን» በሚል ጊዜ መጀመሪያ ላይ የገላትያ ሰዎች ጳውሎስን ሲቀበሉት ለሰዎች ከሚሰጠው ክብር በሚበልጥ ክብር ተቀብለውት እንደነበር የሚያስታውስ ቃል ነው። የዚህ ዓይነት ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ ስለዚህ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ሲል ምንም እንኳ «የሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ፍጥረታት የሆኑትን የመላእክትን ልሳን ጭምር መናገር ብችል እንኳ» ብሎ ከፍ ያለውን የልሳን ስጦታ አግንኖ በመግለጽ ከፍቅር ጋር ለማነጻጸርና ፍቅር ከዚያ እንደሚበልጥ ለማሳየት የተጻፈ ነው።
የመላእክት ልሳን ሲባል ምናልባት ጳውሎስ ወደሰማይ ወደገነት ተነጥቆ በዚያ የሰማውን «ሰው ሊናገር የማይገባውን ቃል» ዓይነት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመት ይሆናል (2ቆሮ.12፡4)፤ ይሁን እንጂ ይህ ቃል መላእክት የተናገሩት ቃል መሆን አለመሆኑ ካለመገለጹም ሌላ ቃሉ «ሰው ሊናገረው የማይገባ፣ የማይነገር» ቃል እንደሆነ ስለተነገረን ግምቱ የሚያስኬድ እንዳልሆነ ማየት ይቻላል። ሆኖም መላእክት እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከሰው ጋር እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር በቋንቋ ሲነጋገሩ የሚያሳዩ ብዙ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦች አሉ (መሳ.13፡3-5፤ ዳን.8፡16፤ 9፡20-23፤ ማቴ.1፡20፤ 2፡13፡19፤ 28፡3፤ ሉቃ.1፡13-1-20ና26-38፤ 2፡9-14፤ ሐ.ሥ.10፡4፤ 12፡7-9፤ ራእ.7፡2-3፤ ተመልከት)። መላእክት ለሰው ሲናገሩ በሰው ቋንቋ እንደተናገሩ መረዳት ቢቻልም እርስ በእርሳቸውና ወደ እግዚአብሔር ሲናገሩ ምን ዓይነት ቋንቋ እንደሚገለገሉ ማወቅ አይቻልም። ይህ በመንፈሳዊው ዓለም ያለ ልሳን (ቋንቋ) በመሆኑ እጅግ የከበረ ነው። አማኝ ይህ የመላእክት ቋንቋ ቢሰጠው እንኳ ፍቅር ከሌለው ዋጋ ቢስና ከንቱ ነው። ሆኖም በሐዋ.ሥ.2 ላይ እንደምናነበው በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ የወረደ ዕለት የተነገሩት ልሳኖች የ15 አገሮች ሰዎች ልሳኖች ናቸው እንጂ የመላእክት ልሳን አልነበሩም፤ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያንም ይነገሩ የነበሩት ልሳኖች የዚህ ዓለም ሰዎች የሚናገሯቸው ልሳኖች እንደሆኑ በ1ቆሮ.14፡10 ላይ «በዓለም ምናልባት ቍጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል፤ ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም» የሚለው ቃልና በቍ.22 ላይ «ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ» የሚለው ቃል በግልጽ ያስረዳል። በመሆኑም እንኳን የሰዎችን ልሳን ይቅርና ከሰው የሚበልጡትን የመላእክትን ልሳን የመናገር ስጦታ ቢኖር እንኳ ፍቅር ከሌለ ከንቱ መሆኑን በንጽጽር ለማስረዳት ጳውሎስ የተጠቀመበትን ቃል በዘመናችን በልሳን ይቅርና ከሰው የሚበልጡትን የመላእክትን ልሳን የመናገር ስጦታ ቢኖር እንኳ ፍቅር ከሌለ ከንቱ መሆኑን በንጽጽር ለማስረዳት ጳውሎስ የተጠቀመበትን ቃል በዘመናችን በልሳኖች ስም የተፈጠሩ ድምፆችን የመላእክት ልሳኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ በግምት ለማስረዳት መጥቀሱ መጻሕፍትን ማጣመም ነው፤ አንድ አማኝ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ቢናገር ነገር ግን ፍቅር ባይኖረው «እንደሚጮህ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽው ጸናጽል» መኾኑ ተገልጧል። ናስ ባልታሰበ አጋጣሚ ሁሉ በድንገት ቢነካ ይጮኻል፤ ግን መጮኹ ምንም ምክንያትና ዓላማ ስለሌለው ትርጉም የለሽ ነው። ጸናጽል በሚንሸዋሸው ጊዜ አንዳች ተለይቶ የሚታወቅ ዜማ ሊሰጥ አይችልም፤ ከሌሎች ሙዚቃዎች ጋር ሥራ ላይ የሚውል የዜማ ዕቃ ብቻ ነው። ስለዚህ ጸናጽል ቢንሸዋሸው ምንም ለማለት አይደለም፤ የሚንሸዋሸው እንዲያው በከንቱ ነው፤ እንዲሁም ሰው ፍቅር በሌለበት በሰዎች ብቻ ሳይሆን ከሰዎችም አልፎ በመላእክት ልሳን እንኳ ቢናገር በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ ቢስና ከንቱ ነው፤ የዚህ ቃል ትክክለኛ ሐሳብ ይህ ነው እንጂ ሊተረጐምና ሊታወቅ የማይችል ልሳን ተሰጥቶና ተነግሮ እንደነበር ለማስረዳት የተጻፈ አይደለም።
4. 1ቆሮ.13፡8-13«ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ክፍልን እናውቃለንና፤ ከትንቢትም ከፍለን እንገናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጐልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ።»
ሐዋርያው ጳውሎስ የጸጋ ስጦታዎችን ከፍቅር ጋር በማነጻጸር እያቀረበ ያለውን እውነታ በመቀጠል በዚህ ንባብ ውስጥ ከጊዜ አኳያ አነጻጽሯቸዋል። በዚህ ክፍል ከፍቅር ጋር የተነጻጸሩት የጸጋ ስጦታዎች ሦስት ሲሆኑ እነርሱም ትንቢት፣ ልሳኖች እና እውቀት ናቸው። «ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም» በሚል ጊዜ ፍቅር በዘመናት ሁሉ የሚኖርና አማኞችን የሚገዛ ክርስቲያናዊ ምግባር መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከፍቅር በተነጻጻሪ ከቀረቡት ከሦስቱ ስጦታዎች መካከል ትንቢትና እውቀት የሚሻሩ መሆናቸው የተገለጠ ሲሆን ልሳኖች ግን «ይቀራሉ» ተብለዋል። ለትንቢትና ለእውቀት «ይሻራል» የሚል ግስ ሲጠቀም ለልሳኖች ግን «ይቀራሉ» የሚለውን ግስ ይጠቅማል። በሁለቱ ግሶች መካከልም የትርጉም ልዩነት አለ፤ «ይሻራል» በሚለው ግስ የተገለጡት ትንቢትና እውቀት በከፊል የነበሩ እንደሆኑ ተገልጿል፤ «ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና» አልተባለም፤ ስለሆነም ተከፍሎ የነበረው ትንቢትና ተከፍሎ የነበረው እውቀት የሚሻሩት ፍጹም የሆነ ሁኔታ ሲመጣ ነው፤ ፍጹም የሆነ ሁኔታ በሚመጣ ጊዜ አስቀድሞ በከፊል ሲነገርና ሲታወቅ የበረውን ወደሚሽር ፍጹም የተሟላ መገለጥ ውስጥ ስለምንገባ ተከፍሎ የነበረው ያን ጊዜ አስፈላጊ አየሆንም፤ በሙላት ባለው ተተክቷልና። ስለዚህ «ይሻራል» ሲባል ሙላትና ፍጹምነት ባለው (ፍጹም በሆነ) ነገረ ሲተካ የሚተው መሆኑን የሚያመለክት ነው። ይህንንም ለማብራራት ሐዋርያው ሁለት ምሳሌዎችን አቅርቧል፤ የመጀመሪያው የልጅነት ጠባይንና የጐልማሳነትን ጠባይ በማነጻጸር የቀረበ ምሳሌ ነው። «ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር እንደ ልጅም እቈጥር ነበር» ሲል ተከፍሎ የነበረውን ትንቢትና እውቀት በምሳሌነት ሲያሳይ «ጐልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ» ሲል ደግሞ ወደፊት የምንደርስበትን ፍጹም ወይም ሙሉ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ያመለክታል። ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ የመስታወት ምሳሌ ነው። በጥንት ጊዜ የነበረው መስታወት የናስ መስታወት ነበር (ዘጸ.38፡8)። ይህ መስታወት ምስሎችን የሚያሳየው እንዳሁኖቹ በጥራት ሳይሆነ በድንግዝግዝ ነበር፤ ስለሆነም «ዛሬም በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን» ተበሎ ሊገለጽ ቻለ። ወደፊት በሚኖረው ፍጹም የሆነ ሁኔታ የምናውቀው በሙላት እንደሆነ ለማሳየት ደግሞ «በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን» ተባለ። አንድን ነገር በመስታወት በድንግዝግዝ ከማየት ይልቅ ፊት ለፊት ማየት ስለዘያ ነገር የተጣለና የተሟላ እውቀት እንዲኖር ያደርጋል። ሐዋርያው ምሳሌውን ራሱ ሲተረጐም «ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ፤ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ» ብሏል። «ፊት ለፊት እናያለን» የሚለው አገላለጽ «እኔ ደግሞ አንደታወቅሁ አውቃለሁ» በሚለው ቃል ተብራርቷል። ይህም ማለት እኔ በእግዚአብሔር የምታውቀውን ያህል ሁሉን ነገር አውቃለሁ ማለት ነው፤ በሌላ አገላለጽ ሙሉውን የእግዚአብሔርን እውቀት ወደሚገኝበት ፍጹም ሁኔታ ውስጥ እገባለሁ ማለት ነው። በ1ዮሐ.3፡2 ላይ «ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን ምንም እንምንሆን ገና አልተገለጠም ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህ «ዛሬ» የሚለው እዚህ ምድር ላይ ጌታ ከመምጣቱ በፊት አማኞች የሚኖሩበትን ጊዜ የሚያሳይ ሲሆን «በዚያን ጊዜ» የሚለው ደግሞ በነፍስ ወደ ጌታ ሄደን በሰማይ በእርሱ ዘንድ የምናርፍበትንና ወደፊት ጌታ ለቅዱሳኑ ሲመጣ ከሙታን ተነስተን በከበረ አካል ወደ እርሱ ተወስደን ለዘላለም ከእርሱ ጋር የምንኖርበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ፍጹም የሆነ ሁኔታ የሚመጣውም በዚያን ጊዜ ነው። በኤፌ.3፡19 «እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ በሚለው ቃል ውስጥ የተገለጠው ፍጹም ሙላትም ይህ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ተከፍለው የነበሩትን ትንቢትና እውቀትን የሚሽራቸው እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ስንደርስ የምንገኝበት ፍጹም ሁኔታ ነው፤ ይህም በሰማይ ባለ መንፈሳዊ ዓለም የምንገኘበት የከበረ ባሕርይ ነው። ዛሬ ለእኛ ያልተነገሩን፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የተያዙ፣ እንድናውቃቸውም ያልተደረጉ እውነታዎች መኖራቸውን ከቃሉ እንረዳለን፤ ለዚህም በዘዳ.29፡29፣ ማቴ.24፡36፣ ሐዋ.ሥ.1፡6-7፣ ፊልጵ.3፡12-15 ያሉትን ንባቦች ተመልከት። ወደ ክብር የምንወሰድበት ጊዜ ሲመጣ ግን ያን ጊዜ በእኛ ዘንድ ከፊል የሆነ ነገር አይኖርም። ተከፍሎ የነበረው ሁሉ እዚያ ፍጹም በሆነው ነገር ያሻራል።»
«ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» ሲል ግን ልሳኖቹን የሚተካቸው ሌላ ፍጹም ነገር ሲመጣ ልሳኖቹ መሻራቸውን የሚያሳይ ሳይሆን ልሳኖቹ የተሰጡበትን ዓላማ ፈጽመው ከጨረሱ በኋላ የሚያቆሙ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነው። በሌላ አገላለጽ ይህ ቃል በልሳኖች የመናገር ስጦታ ከመጀመሪያውኑ የተሰጠው በጊዜያዊነት መሆኑን ያመለክታል።
በማር.16፡17 የተጻፈውን ስናጠና እንደተመለከትነው በአዲስ ቋንቋ መናገር ቃሉን ለማጽናት የተሰጠ ምልክት ነው፤ በጠባዩም ተአምራዊ የሆነ ስጦታ ነው። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው ባልተጠናቀቁበት በዚያ ዘመን ጌታን ባመኑ ሰዎች ማለትም በክርስቲያኖች እየተነገረ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ለአይሁድና ለአሕዛብ አዲስ በመሆኑ በምልክቶች መጽናት ነበረበት። ስለሆነም በማር.16፡20 ላይ እንደተገለጠው ጌታ ካመኑት ጋር እየሠራ ቃሉን በምልክቶች የጸና ነበር። የማርቆስ ወንጌል በሚጻፍ ጊዜ እንኳ «ያጸና ነበር» በሚል በኃላፊ ግስ የተነገረ ክስተት ሆኖ እናገኛለን፤ ሌሎችም ቆየት ብለው በተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በዚያ ጊዜ ቃል በምልክቶች መጽናቱ በግልጽ ተነግሮናል። ለምሳሌ በዕብ.2፡4 ላይ «.. ይህ በመጀመሪያ በጌታ የተነገረ ነበረና፤ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት» ይላል። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን በጌታ የተነገረውና ቃሉን ከእርሱ በሰሙት ሰዎች የተላለፈው ቃል እግዚአብሔር እርሱ ራሱ በምልክትና በድንቅ ነገር፣ በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማደል እንደመሰከረለት (እንዳጸናው) ከዚህ እንገነዘባለን። እንደዚሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ በ2ኛው መልእክቱ እርሱና በጊዜው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሐዋርያት በቅዱሱ ተራራ ሳሉ የእርሱን የኢየሱስን ግርማ እንዳዩ፣ ስለእርሱም የተነገረውን የአብ ድምጽ ከሰማይ ሲወርድ እንደሰሙ ከገለጸ በኋላ «ከእርሱም ይልቅ የጸና የትንቢት ቃል አለን» ብሏል። (2ጴጥ.1፡16-18)፤ ይህም የጸናው የትንቢት ቃል በዚሁ ምዕራፍ በቍ.20 ላይ «በመጽሐፍ ያለው ትንቢት» እንደሆነ ተገልጧል። በዚያን ጊዜ የነበረው መጽሐፍ ደግሞ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው። ስለዚህ ጴጥሮስ በዚህ ክፍል «የጸና የትንቢት ቃል» ብሎ የሚገልጸው በጊዜው በነበረው መጽሐፍ ቅዱስ የነበረውን ቃል ነው። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፈው ቃል ግን በምልክቶችና በድንቆች ገና እያጸና ነበር፤ በኋላ ግን በዕብ.2፡4 ላይ እንደተጻፈው እግዚአብሔር እርሱ ራሱ በምልክቶችና በድንቆች በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማደል አጽንቶታል።
ይሁን እንጂ ይህንን ካለመገንዘብ የተነሣ የጸናው የእግዚአብሔር ቃል ከሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰበክበት በዚያ ዘመን በአንዳንድ ስፍራ በልሳኖች መናገር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ምልክቶች እንዲታዩ ሲፈለግና አልፎ አልፎም እንደሚደረጉ ሲነገር ይሰማል። ይሁንና እግዚአብሔር በምልክቶችና በድንቅ ነገር ቃሉን የማጽናት ሥራውን በክርስትና ዘመን መጀመሪያ ላይ ያጠናቀቀ በመሆኑ እነዚህ ሲደረጉ ይታያሉ የሚባሉ ምልክቶች ከእግዚአብሔር አለመሆናቸውን መረዳት ይገባል። በሰይጣን አሠራር የሚከናወኑ ሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆች ተአምራትም ስለመኖራቸው አስቀድሞ በግልጽ መነገሩን ማወቅ ያስፈልጋል (ማቴ.7፡21-23፤ 24፡24፤ 2ተሰ.2፡9-12)። ምልክቶችን በማየት ለማመን መፈለግም በጌታ በኢየሱስ በጥብቅ ተነቀፏል። ይህንንም አይሁድ ምልክትን እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም» በማለቱ ገልጧል (ማቴ.12፡38-40፤ ማቴ.16፡4)። ጌታ እንዲህ ያላቸው አይሁድ ነቢዩ ዮናስንም ሆነ ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ውስጥ 3 ቀን 3 ሌሊት ማደሩን በዐይናቸው አላዩም፤ ሆኖም በትንቢት ዮናስ የተጻፈውን ስለሚያውቁ ይህንን ሊላቸው ችሏል። የዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ 3 ቀን 3 ሌሊት ማደር የጌታን በምድር ልብ ውስጥ 3 ቀን 3 ሌሊት ማደር እንደሚያመለክት ተናግሯል (ማቴ.12፡40)። ዮናስ ከዓሣ ሆድ ውስጥ ከ3 ቀንና ከ3 ሌሊት በኋላ እንደወጣ ጌታም ከ3 ቀንና ከ3 ሌሊት በኋላ ከሙታን ተነሥቷል። ይህ ለእምነታችን ትልቁ ምልክት ወይም ማስረጃ ነው። ጌታ «ከነቢዩ ከዮናስ በቀር ሌላ ምልከት አይሰጠውም» ባለው መሠረት ምልክትን ለሚሻ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ከዮናስ ከሚበልጠው ከእርሱ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ክርስቶስ ከ3 ቀንና ከ3 ሌሊት በኋላ ከሙታን መነሣቱን በዓይናችን ባናይም በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎልናል። ስለዚህ ምንም ባናይም ልናምን ይገባል። ጌታ ኢየሱስ ከተነሣ በኋላ ለቶማስ «ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው» ብሎ የተናገረው ቃል ለዚህ ጉልህ ማስረጃ ነው (ዮሐ.20፡29)። ስለዚህ ክርስቶስ ሞቶ መነሣቱን ሳያዩ ያመኑ ሰዎች በልሳን (በአዲስ ቋንቋ) ከመናገርም ሆነ ከሌሎቹ ምልክቶች የበለጠ ዘላለማዊ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው እነዚህ ምልክቶች መቅረታቸውን ይረዳሉ።
ስለሆነም «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» የሚለው ቃል ሁሉ ቃልን የማጽናት ዓላማውን ከፈፀመ በኋላ የሚያቆም ወይም ለዘለቄታው የማይቀጥል መሆኑን ያስፈርዳል። ቃሉ «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» ይላል እንጂ «ቀርተዋል» ስለማይል ልሳኖች የሚቀሩበት ጊዜ መቼ እንደ ሆነ ለማወቅ እንድንጠየቅ ያደርግናል። ልብ ብለን ካስተዋልን «መቅረት» አንድ ነገር መጀመሩን፣ ነገር ግን አለመቀጠሉን የሚያሳይ ቃል ነው። የመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት በተጻፈችበት ጊዜ ገና የእግዚአብሔር ቃል ጸንቶ ባለመጠናቀቁ በልሳኖች መናገር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተአምራዊ ምልክቶች ሁሉ አልቀሩም ነበር፤ ስለዚህ በዚያን ጊዜ ሲጻፍ ሊባል የሚችለው «ልሳኖችም ቢሆኑ የቀራሉ» ተብሎ ነው እንጂ «ቀርተዋል» ተብሎ ሊሆን አይችልም፤ እልከኛ ባልሆነና ቅንነት በተሞላ ልብ ሆኖ ያስተዋለ ሰው «ይቀራሉ» የሚለው ቃል «ጌታ እስኪመጣ እስከ ፍጻሜው ይቀጥላሉ» ማለት እንዳልሆነ መረዳት ይችላል፤ እንዲያውም መቅረት ብዙ ጊዜ በመነሻው ወይም በጅማሬው ላይ ዓላማውን አከናውኖ ማቆሙንና ከዚያ በኋላ ወደፊት አለመቀጠሉን የሚያስገነዝብ ቃል ነው። በመሆኑም «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» ሲል «በልሳኖች የመናገር ስጦታ» በቤተክርስቲያን የመጀመሪያ ዘመን መሥራት የነበረበትን ሥራ ሠርቶ የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ሲያበቃ ከሌሎቹ ተአምራዊ ስጦታዎች ጋር ሊቀር ወይም ሊቆም እንደነበረው በእርግጠኝነት የሚያስረዳ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ዘመን ላይ ሆነን ስንናገር ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ማለትም ከ2ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አሁን እስካለንበት እስከ 21ኛው ክ/ዘመን ብሎም እስከ ጌታ መምጣት ድረስ በልሳኖች የመናገር ስጦታ «ቀርቷል» ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።
አንዳንድ ጊዜ «እንዲህ ማለት መንፈስ ቅዱስ አይሠራም ማለት ይሆናል» በሚል ስጋት በልሳኖች የመናገር ስጦታ መቅረትን ለመቀበል የሚከብዳቸው ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ካለማወቅ የሚመጣ ድፍረት ማጣት ነው። መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን በምድር ላይ ባለችበት ዘመን ሁሉ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥና በጉባኤ መካከል እየኖረ አለ፤ ስለሆነም እርሱ በዘመናት ሁሉ ሥራውን ባለማቋረጥ ይሠራል። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሲባል ግን አማኞችን በልሳኖች ማናገርና የተለያዩ ታምራትን ማሠራት ብቻ አልነበረም፣ አይለምም፤ ስለጌታ መመስከር (ዮሐ.15፡26) ወንጌል ለማያምኑ እንዲደርስ ማድረግ (1ተሰ.1፡5፤ 1ጴጥ.1፡12)፣ የማያምኑትን መውቀስ (ዮሐ.16፡8)፣ እያንዳንዱን አማኝ ማተምና መቀባት (2ቆሮ.1፡21-22፤ ኤፌ.1፡13)፣ በነገር ሁሉ አማኞችን መምራትና ማገዝ (ሮሜ.8፡14፣26)፣ የተለያዩ የጸጋ ስጦታዎችን በቤተክርስቲያን መካከል መግለጥ እነዚህንም ስጦታዎች እንደፈቃዱ ለእያንዳንዱ እያካፈለ መስጠት (1ቆሮ.12፡4-11)፤ .... ወዘተ፤ እነዚህ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ናቸው፤ መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ሥራዎቹን የሚሠራው ደግሞ በራሱ ዕቅድና መንገድ ነው። «ይቀራል» ያላቸውን ማስቀረትም የራሱ ዕቅድ ነበር። እርሱ አንዳንድ ስጦታዎችን እስከ ጌታ መምጣት ሊሠራባቸው አንዳንዶቹን ደግሞ በጊዜው ዓላማቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ሠርቶባቸው ሊያስቀራቸው የሚቻለው መለኮት የሆነ ማንነት ነው። መንፈስ ቅዱስ ራሱ ካስጻፈው ቃል በተቃረነ መልኩ የሚሠራ አይደለም፤ ስለዚህ «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» ብሎ ያስጻፈው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያመነ ሰው በልሳኖች መናገርን ያስቀረውም ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው ብሎ በእርግጠኝነት ለማመንና ለመናገርም ድፍረት አያጣም።
5. 1ቆሮ. ምዕ.14 (ቍ.1)በ1ቆሮ. 12 መጨረሻ ላይ «ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ» ተብሎ የተጠቀሰው እና በ1ቆሮ.13 መጨረሻ ላይ ደግሞ ከእምነትና ከተስፋ እንደሚበልጥ የተነገረለት «ፍቅር» በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ቍጥር ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፤ መንፈሳዊ ስጦታዎች በቤተክርስቲያን ሥራ ላይ በሚውሉ ጊዜ ፍቅር ትልቁን ስፍራ ሊይዝ ይገባል። «ፍቅርን ተከታተሉ» የሚለው ቃል ማናቸውም የጸጋ ስጦታ በጥቅም ላይ በሚውል ጊዜ ፍቅርን መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባው የሚያስረዳ ነው። በ1ቆሮ.13፡1 ላይ አንድ ሰው በሰዎችና በመላእክት ልሳን ቢናገር፣ ትንቢት ቢኖረው፣ ምሥጢርን ሁሉና እውቀትን ሁሉ ቢያውቅ፣ ተራሮችን እስኪያፈርስ ድረስ እምነት ቢኖረው ፍቅር ከሌለው ከንቱ መሆኑ ተነግሮአል። ስለዚህ የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ በፍቅር ሥራ ላይ የሚውሉ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ከመንፈሳዊ ስጦታዎች መካከልም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ» ተብሏል። ይህ ማለት አንድ ሰው ትንቢት የመናገር ስጦታ እንዲሰጠው ይፈልግ ማለት ሳይሆን በአማኞች መካከል «ትንቢት መናገር» እንዲኖር ፈልጉ ማለት ነው። ስለዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች በልሳኖች ከመናገር ሆነ ከሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች ይልቅ «ትንቢት መናገር» በማኀበራቸው መካከል እንዲኖር በብርቱ ይፈልጉ ዘንድ መመከራቸውን እናስተውላለን።
(ቍ.2፡3) «በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና በመንፈስ ግን ምስጢርን ይናገራል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል»
በልሳን መናገር እና በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች መሆናቸውን አስቀድመን ተመልክተናል። በዚህ ንባብ ውስጥ ከሁለቱ ስጦታዎች የተጠቀሰው «በልሳን መናገር» ብቻ እንደሆነና በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ አብሮት እንደሌለ ማስተዋል ይገባል፤ ይህም የንባቡን ትክክለኛ ሐሳብ ለመረዳት ያስችላል። ስለሆነም «በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሐር እንጂ ለሰው አይናገርም» ሲል አንድ በልሳን የመናገር ስጦታ የተሰጠው አማኝ ወደ ሰው ሳይተረጐም በልሳን ቢናገር የሚናገረው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይደለም ማለት ነው። በመሠረቱ ልሳኖችን መተርጐም የሚያስፈልገው ለሰው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። እግዚአብሔር ልሳኖቹን የሰጠ እርሱ በመሆኑ ለእርሱ አይተረጐምለትም፤ በልሳን የሚነገረው ነገር አድራሻው ወደ እርሱ ባይሆን እንኳ የሚነገሩት ልሳኖች ሁሉ በእርሱ የሚታወቁ ናቸው። ስለዚህ ባልተተረጐመ ልሳን የሚናገር ሰው፣ የሚናገረው፣ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይሆንም፤ የተነገረውን የሚሰማው ወይም የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ልሳን ከመጀመሪያውኑ የተሰጠው ወደ እግዚአብሔር ለመናገር እንጂ ወደ ሰው መናገር አይደለም ተደርጐ በስህተት ሲብራራ እንሰማለን፤ ሆኖም «በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም» ማለት ተተርጐሞ ሰው እንዲሰማው እስካልተደረገ ድረስ የሚነገረው ለእግዚአብሔር ነው፤ ወይም የሚሰማው እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አይደለም ማለት ነው። ይህም የሚታወቀው ከዚህ ንባብ ቀጥሎ በምክንያትነት በተቀመጠው «የሚያስተውለው የለምና» በሚለው ቃል ነው። ማንም የሚያስተውለው ሰው በሌለበት የሚነገር ልሳን የተነገረው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይደለም፤ ከእርሱ በቀር የሚያውቀው ወይም የሚያስተውለው ማንም ሰው የለምና።
ይሁንና ሳይተረጐሙ የሚነገሩ ልሳኖች አንዳች ምስጢርን የሚናገሩ የሌሎች ሰዎች ቋንቋዎች ናቸው እንጂ እንዲሁ በምላስና በከንፈር መነቃነቅ (መርገብገብ) የሚፈጠሩ ትርጉም የለሽ ፊደላት አይደሉም፤ «በመንፈስ ግን ምስጢርን ይናገራል» በሚለው ቃል እንደምንረዳው ልሳኑ አንዳች «ምስጢር» የሚነገርበት ቋንቋ መሆኑን በግልጽ የሚያመለክት ነው። እዚህ ላይ «ምስጢር» ሲባል አንዳንዶች በስህተት እንደሚያስቡት ለሰዎች ሲነገር ሰይጣን እንዳይሰማ ተብሎ በልሳን የተነገረ ማለት አይደለም4 ነገር ግን ምስጡር የተባለው አስቀድሞ ተሰውሮ የነበረና ለሚያሰተውሉ ሁሉ ሊገለጥ የሚችል ሐሳብ ነው። እንዲህ ያለው ምስጢር ቢተረጐም ኖሮ ሰዎች ሰምተውት ይጠቀሙበት ወይም አሜን ይሉ ነበር። ባለመተርጐሙ ግን የሚያስተውለው አይኖርም። ይሁንና ችግሩ አለመተርጐሙ ነው እንጂ ልሳኑ ግን ይዘትና መልእክት ያለው ንግግር (ቋንቋ) መሆኑ ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም።
በልሳን ከሚናገር ሰው ጋር በተቃራኒ የተነጻጸረው ትንቢትን የሚናገር ሰው ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው እንደሚናገር ተገልጧል። ትንቢት በዘመናችን ሲነገር እንደሚሰማው የአማኞች የግል ኑሮን፣ የወደፊት ዕድልን፣ ትደርን፣ ሥራን፣ ትምህርትን፣ ወደ ውጭ አገር መሄድ አለመሄድን፣ ጤናን፣.... ወዘተ የሚያመለክት አይደለም ነገር ግን ትንቢት እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ አልፎ አልፎ በተአምራዊ መገለጥ ሲነገሩ የነበሩ የወደፊት ክስተቶችንና በዘወትር የቤተክርስቲያን አገልግሎት ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ለማኀበረ የሚልከውን የሚያንጽ የሚመክርና የሚያጽናና ቃልን ያመለክታል። በዚህ በምናጠናው ክፍል የገለጠው ዘወትር በመደበኛ አገልግሎት ጊዜ የሚነገረው የሚያንጽ የሚመክርና የሚያጽናና ቃል ሆኖ ነው። ሳይተርጐሙ ከሚነገሩ ልሳኖች ይልቅ ማኀበሩን የሚጠቅመው የዚህ ዓይነት የትንቢት አገልገሎት ነው። ምክንያቱም ትንቢት የሚነገረው በሰሚዎቹ ቋንቋ በመሆኑ ነው። በልሳኖችና በትንቢት መካከል የተደረገው ይህ ንጽጽር በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን መካከል በማኅበር ሲነገር የነበረው ልሳን የሰሚዎቹ ቋንቋ ሳይሆን የሌሎች ሰዎች ቋንቋ መሆኑን ሊያመለክት የሚችል ንጽጽር ነው።
(ቍ. 4) «በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኀበሩን ያንጻል።»
«በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል» የሚለው ቃል በአሉታዊ መንገድ የተነገረ መኾኑን ማስተዋል የንባቡን ትክክለኛ ሐሳብ ለማግኘት ይረዳል። ይህ ማለት ከማኀበሩ ይልቅ የራስን መታነጽ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፤ ምክንያቱም «በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል» የሚለው ቃል የተነጻጸረው «ትንቢትን የሚናገር ግን ማኀበሩን ያንጻል» ተብሎ ከተነገረው ቃል ጋር ነው። በዚህ ቍጥር ላይም የተገለጸው «በልሳን መናገር» ሳይተረጐም የተነገረውን ልሳን (ቋንቋ) የሚያመለክት ነው። ላይተረጐም የቻለው ተናጋሪው «በልሳን የመናገር ስጦታ» እንጂ «በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ» ስላልተሰጠው ነበረ። ይህንንም የምናውቀው በዚሁ ምዕራፍ በቍ.13 ላይ «ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጐም ይጸልይ» በሚለውቃለ ነው። «እንዲተረጐም ይጸልይ» ከተባለ የተሰጠው ጸጋ «በልሳን መናገሩ» ብቻ ነው እንጂ «መተርጐሙም» ጭምር አልነበረም ማለት ነው። ይሁንና ይህን «በልሳን የመናገር ስጦታ» «የመተርጐሙ ስጦታ» በሌለበት በማኅበር መካከል መጠቀም ትልቅ ስህተት ነበረ። በልሳን የሚናገረው አማኝ የራሱን መታነጽ ብቻ በመመልከት የማኀበሩን መታነጽ ግን ችላ በማለት በማኅበር መካከል ልሳኑን ሳይተረጐም ከራስ ወዳድነት ወይም በሰዎች ለመታየት ከመፈለግ የተነሳ ያደረገው መሆኑን ያስገነዝባል፤ ይህም በዚህ ምዕራፍ በቍ.20 ላይ እንደተጠቀሰው በአእምሮ ህፃን ከመሆን የመጣ ተገቢ ያልሆነ አድራጐት ነው፤ ስለዚህ ቃሉ በቆሮንቶስ አማኞች መካከል ይህ እንዳይቀጥል የተጻፈ ቃል ነው።
ሆኖም በማህበር መካከል ባልተተረጐመ ልሳን ይናገር የነበረው የቆሮንቶስ አማኝ ራሱንስ ቢሆን ሊያንጽ የሚችለው እንዴት ነው? የህንን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ መታነጽ ራሱ ምን እንደሆነ ማየት መልቀም ነው። መታነጽ በመንፈሳዊ ሕይወት መገንባትንና ወደ እግዚአብሔር በይበልጥ መጠጋትን የሚያመለክት ቃል ነው። መታነጽ በመንፈሳዊ ሕይወት መገንባትንና ወደ እግዚአብሔር በይበልጥ መጠጋትን የሜያመለክት ቃል ነው። ልሳኑ በሚነገር ጊዜ ያሉት ሌሎች ሰዎች ሊታነጹ የሚችሉት ተተርጐሞላቸው መልእክቱን ሲረዱት ብቻ ነው። ልሳን ተናጋሪው ግን ትርጐሙን ተረድቶ መታነጽን ባያገኝም ልሳኑን በመናገሩ ብቻ ራሱን ያንጻል፤ ምክንያቱም ልሳኑን የሚናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንደመሆኑ መጠን በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ሥር ይሆናል። በውስጡ እያለፈ ያለውና በአንደበቱም እየተነገረ ያለው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልሳን ነው። በዚህን ጊዜ ያለበት ስሜት የተቀደሰና ነፍሱና መንፈሱን የሚገዛ የመንፈስ ቅዱስ ስሜት ነው፤ ስለዚህም በልሳን ተናጋሪው ትረጉሙን ባያውቀውም እንኳ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ልሳን በመናገሩ ብቻ በልቡ ደስታና ሰላም ይሞላበታል፤ ይህም መታነጽ ነው፤ * መታነጹ ከልሳኑ መልእክት የተገኘ ባይሆንም ልሳኑን በመናገር ብቻ የተገኘ መታነጽ ነው። ስለዚህ «በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል» ሲል በልሳን ተናጋሪው ከመልእክቱ የሚያገኙውን መታነጽ ሳይሆን ልሳኑን በሚናገርበት ጊዜ ካለበት የመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖና ስሜት የሚያገኘውን መታነጽ የሚመለክት እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን በቆሮንቶስ በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ ይህን በግል የመታነጽ ሁኔታ ብቻ በማየት በማኅበር መካከል ትርጉሙ በሌለበት ጊዜም በልሳን የሚናገሩ ሰዎች እንደነበሩ ንባቡ ያመለክታል። ይህም በማኀበሩ ፊት ለታይታ ወይም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ ራስን ለማክበረ የተደረገ ነው እንጂ ማኀበሩን ለማነጽ የተደረገ ባለመሆኑ አግባብ አልነበረም፤ ስለሆነም «በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል» ተብሎ የተጻፈው ቃል ሁኔታው መታረም ያለበት ስህተት መሆኑን ለማሳሰብ ነው እንጂ በማኅበር መካከል ራሱን ለማነጽ ባልተተረጐመ ልሳን መናገር ትክክል ነው ብሎ ለማበረታታት የተነገረ አለመሆኑን መረዳት ይገባል።
በልሳን ተናጋሪው ልሳኑን ሳይተረጐም ተጠቀመበት ማለት ግን ልሳኑ ሊተረጐም የማይችል እና መልእከት ያላዘለ፣ ምስጢርንም የማይናገር የፊደላት ቅጥልጥል ነውነ ማለት አይደለም። ተናጋሪው ሳይተረጐም የቻለው ተጋሪው በልሳኖች የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ ስላልተሰጠው ነው እንጂ የሚናገረው ልሳን ቋንቋ ስላልነበረ ወይም በዚህ ዘመን በስፋት እንደሚታየው ትርጐም የለሽና ስሜት የሌለው ድምጽ ሆኖ አልነበረም።
(ቍ.5) «ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፤ ትንቢት ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኀበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጉም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።»
ሐዋርያው ጳውሎስ «ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር» ሲል ሁላችሁ በልሳኖች ትናገራላችሁ ወይም «በልሳኖች መናገር» ለሁላችሁም ይሰጣል ማለቱ አይደለም፤ «እወድ ነበር» ሲል የራሱን መልካም ምኞት መግለጹ ነው። ከዚህ በመነሣት ግን ሁሉም አማኝ በልሳን መናገር ይገባዋል የሚል መረዳት መያዝ ከንባቡ ሐሳብ ብዙ ርቆ መሄድ ነው። ወይም ሐዋርያው በተናገረው ላይ የራስ ፍላጐት የወለደውን ሐሳብ መጨመር ነው። ይህንኑ ቃል የጻፈው ሐዋርያው በ1ቆሮ.12፡30 ላይ «.... ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?.....» በማለት ያነሣውን ጥያቄ ምን ጊዜም መዘንጋት የለብንም። እግዚአብሔር የጸጋ ስጦታዎችን እንደሚፈቅዱ እያካፈለ የሚሰጥ መሆኑም በግልጽ ተነግሮናል (1ቆሮ.12፡4-11)፤ በመሆኑም «ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር» የሚለው ቃል ይህን የሚያፈርስ አይደለም፤ ሐዋርያው ይወድ እንደነበር መግለጹ እግዚአብሔር የግድ ለሁሉም ልሳን ይሰጣል ማለቱ አይደለምና። በመቀጠልም «ትንቢትን ልትናገሩ ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ» ያለውም በዚሁ ዓይነት ነው እንጂ የግድ ሁሉም ትንቢት ይናገሩ ማለቱ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። ይሁንና በልሳኖች ከመናገር ይልቅ ትንቢት መናገርን አስበልጦ መመልከቱን «ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ» በሚለው አገላለጹ ልንረዳ እንችላለን። ከዚያ ቀጥሎም «ማኀበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጉም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል» ብሎ የጻፈውን ቃል ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ትንቢት የመናገር ስጦታ የሚበልጠው የመተርጐም ስጦታ አብሮት ከሌለው በልሳኖች የመናገር ስጦታ መሆኑን ነው፤ ስለዚህ ትንቢት መናገር በልሳኖች ከመናገሩ ብቻ ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ስጦታ ሆኖ ተገልጧል፤ በልሳኖች መናገር ከትንቢት መናገር ሊያንስ የሚችለውም ንግግሩ ባለመተርጐሙ ማኅበሩ ሳይታነጽ ሲቀር መሆኑ ተነግሯል፤ ለማኅበሩ መታነጽ በልሳኖች የተነገረው የግድ መተርጐም እንደነበረበት ከዚሀ እንረዳለን።
ከቍ. 6-12 «አሁን ግን ወንድሞቼ ሆይ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ? ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምጽ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምጽ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። በዓለም ምናልባት ቍጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል። ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ»
በመንፈስ ተነድቶ የሚጽፈው ሐዋርያ በዚህ ክፍል ንባብም ትኩረት የሰጠበት ነገር በልሳኖች መናገር ቤተክርስቲያንን ለማነጽ የሚያገለግል ይሆን ዘንድ በሰሚዎቹ ቋንቋ ተተርጉሞ ሊነገር የሚገባ መሆኑን ነው። በ1ቆሮ.12፡7 ላይ «መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል» የሚለውን ስናጠና በልሳኖች መናገርም ለጥቅም የተሰጠ ስጦታ መኾኑን ተመልክተናል። በዚህ ክፍልም ሐዋርያው በማኅበር መካከል በልሳኖች የሚነገረው ነገር «በመግለጥ» ወይም «በእውቀት» ወይም «በትንቢት» ወይም «በትምህርት» ካልተነገረ ምንም ጥቅም እንደሌለው የሚያሳይ ቃል ሊጽፍ ችሏል። ራሱን እንደምሳሌ ተጠቅሞ በዚህ መልክ ካልነገርኋችሁ «ምን እጠቅማችኋለሁ?» በማለት ጠይቋል። መግለጥ፣ እውቀት፣ ትንቢትና ትምህርት በማኀበሩ ቋንቋ ሁሉም ሊገባቸው በሚችልበት መንገድ የሚነገሩ ናቸው። ታዲያ በልሳኖች የሚነገረው መልእክት ከእነዚህ አራት መንገዶች ባንዱ ቢነገር ለማኀበሩ ጥቅም ይሰጣል። «መግለጥ» አዲስ የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ማምጣት ወይም የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ቃል ምስጢራት ለሰው በሚገባ መልክ ማብራራት ማለት ይሆናል በልሳኖች የተነገረው ነገረም በዚህ ዓይነት አዲሱንም የሆነ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃልን በመግለጥ ለማኀበሩ ቢነገር ጥቅም ይኖረዋል፤ «እውቀት» የእግዚአብሔር ነገሮችን በጥልቀት መረዳትና በአግባቡ መለየትን ያመለክታል። በልሳኖች የተነገረውን ሐሳብ በአእምሮ በሚገባ ተረድቶ ለማኀበሩ ቢነገር በእውቀት ተነግሯል ሊባል ይችላል፤ ጥቅምንም ያስገኛል፤ «ትንቢት» በዚህ ክፍል ላይ ማኀበሩ የሚመከርበትንና የሚጽናናበትን የጊዜውን ቃል የሚያመለክት ሲሆን በልሳኖች የተነገረው ቃል ለማኀበሩ ወቅታዊ መልእክትን በሚያስተላልፍ መልኩ ቢነገር በትንቢት ተነግሯል ማለት ይቻላል። «ትምህርት» አንድን እውነት በሚያሳምን መልክ ለሰሚዎች ማስረዳት ነው። በልሳኖች የተነገረው ቃል ሰሚዎቹ በሚገባቸው መንገድ ተብራርቶ መቅረብ የሚችል ከሆነ በትምህርት ተነግሯቸዋል ሊባል ይችላል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን በልሳኖች የተነገረው ቃል ሰሚዎቹ በሚናገሩበት ቋንቋ መተርጐም አለበት።
ሆኖም በዚህ በማኅበር መካከል በልሳኖች የተነገረው ሐሳብ በተገለጠ ቃል ካልተነገረ በሐዋርያው አገላለጽ ድምፃቸውን ልዩነት እንደማይሰጡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሆኖ ቀርቧል። ከሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ነገሩን ለማብራራት ዋሽንትና ክራር በምሳሌነት የተጠቀሱ ሲሆን የድምጽ ልዩነት የማይገልጡ ከሆነ «በዋሽነት የሚነፋው ወይም በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል?» ተብሏል። እዚህ ላይ «መዝሙር» የሚለው ቃል በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች «ዜማ» ተብሎ የተተረጐመ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። (አ.መ.ት. ተመልከት)። ማንኛውም ዜማ አስቀድሞውኑ የሚታወቅ ከሆነ በሙዚቃ በሚቃኝ ጊዜ የድምፁን ልዩነት ከሰጠ ወዲያውኑ ይታወቃል። አብሮ ማዜምም ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ዜማውን ማወቅም መለየትም አይቻልም። «መለከት» ከዜማ ጋር በተያያዘ ባይሆንም በማብራሪያነት ከቀረቡት የሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ ነው «ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምጽ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?» የሚል ጥያቄ ቀርቧል። መለከት የተለያዩ መመሪያዎችንና አዋጆችን ወደ ሕዝብ ለማድረስ የሚያገለግል የሙዚቃ መሣሪያ ነው። በጦርነት ጊዜ የሚሰማውም የመለከት ድምጽ ዓይነቱ በሠራዊቱ ዘንድ ቀድሞውኑ የሚታወቅ ነው፤ የዚያ ዓይነት ድምጽ ተለይቶ ካልተሰማ ለጦርነት የሚዘጋጅ አይኖርም። ልክ እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች የድምጽ ልዩነት ካልሰጡ ዜማቸው ወይም የሚያስተላልፉት መልእክት ተለይቶ እንደማይታወቅ ሁሉ በልሳኖች የተነገረው ምስጢርም በመግለጥ፣ በእውቀት፣ በትንቢት፣ በትምህርት ካልተነገረ ምን እንደተባለ አይታወቅም፤ ስለዚህ ሐዋርያው «እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ» በማለት ጽፏል። «የተገለጠውን ቃል» መናገር የሚቻለው ደግሞ በልሳኖች የተነገረው ቃል በሰሚዎች ቋንቋ ሲተረጐም ነው። የቋንቋው ፍቺ ካልታወቀ በተናጋሪውና በሰሚዎቹ መካከል መግባባት አይኖርም፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በልሳኖች የተነገረው ነገር ለሰሚዎቹ ምንም ጥቅም ሳያስገኝ ይቀራል። ይህም ልሳን በዓለም ካሉ ቋንቋዎች አንዱ ቋንቋ መሆኑ የሚታወቅበት አንዱ ባሕርይ ነው። በልሳኖች በመንፈስ ሲነገር የነበረው ምስጢር በተገለጠ ቃል መነገር የሚችል መሆኑ የቋንቋ ባሕርይ ነው። «በዓለም ምናልባት ቍጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል፤ ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ እንግዲህ የቋንቋውን ፍቺ ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል።» ተብሎ የተጻፈው ቃልም ልሳኖች ሌላ ምንም ሳይሆኑ በዓለም ካሉ ቋንቋዎች መካከል የሆኑ ተናጋሪ ሕዝብ ያላቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህ በተገለጠ ቃል ሊተረጐሙ ይችላሉ። ፍቺው በማይታወቅበት ሁኔታ ቢነገሩ ግን አንዱ ለሌላው እንግዳ ይሆናል። በማኅበር መካከልም ፍቺው ወይም ትርጉሙ ታውቆ በተገለጠ ቃል ማለትም በሰሚዎቹ ቋንቋ ተተርጐሞ ካልተነገረ በቀር ምንም ዓይነት ጥቅምን ማለት መታነጽን ስለማያስገኝ በልሳኖች መነገር የለበትም። ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ ሊኖረን የሚገባው ቤተክርስቲያንን ለማነጽ እንዲሆን ያስፈልጋል። በመሆኑም «እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ» የሚል መመሪያ ተጽፎአል። ስለዚህ በልሳኖች የመናገር ስጦታም በማኅበር መካከል ሥራ ላይ መዋል ያለበት ለቤተክርስቲያን መታነጽ እንጂ ለግል መታነጽ ስላልነበረ መተርጐም ነበረበት።
ከቍ.13-19 «ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጐም ይጸልይ። በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ያለፍሬ ነው። እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ ሌላው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን ሌሎችን አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።»
የቆሮንቶስ አማኞች መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የሚፈልጉ ከሆነ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላቸው ይፈልጉ ዘንድ ተነግሯቸዋል፤ በልሳን የመናገር ስጦታ ደግሞ ለማኀበሩ መታነጽን ሊያመጣ የሚችለው ለማኀበሩ ሲተረጐም ብቻ ነው። በዚህ ምክንየት በቆሮንቶስ አማኞች መካከል በልሳን የሚናገር ሰው «ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጐም ይጸልይ» የሚል መመሪያ ተሰጥቶታል፤ ተብሎ፤ «ስለዚህ» የሚለው አያያዥ ቃል ከላይ ባሉት ቁጥሮች ለተገለጸው ችግር መፍትሔውን የሚጠቁም ሐሳብ ቀጥሎ እንደማነገር የሚያሳይ ቃል ነው፤ በልሳን የሚናገር ሰው በድፍረት የመሰለውን ሊተረጐም አይችልም፤ ወይም ሳይተረጐም በማኅበር መካከል በልሳን መናገር አልነበረበትም፤ በምትኩ ግን እንዲተረጐም መጸለይ ይገባው ነበር። «እንዲተረጐም» በሚልበት ጊዜ ራሱ በልሳን የመናገር ስጦታ የነበረው አማኝ ካለ ሊተረጐም ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን በልሳን የሚናገረው አማኝ ራሱ መተርጐም እንዲችል ሊጸልይ ይገባል።
በልሳን መናገር ስንል «በመግለጥ፣ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት» መልክ ብቻ ሳይሆን በጸሎት መልክም ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ከቃሉ እንረዳለን፤ «በልሳን ብጸልይ» የሚለው አገላለጽ ይህን የሚያስረዳ ነው። ይሁን እንጂ የተናጋሪው አእምሮ ትርጉሙን ሳይረዳ በመንፈስ ብቻ ልሳኑን የሚናገረ ከሆነ ምንም እንኳ ልሳኑ በመንፈስ ቅዱስ ሙላት እየተነገረ ቢሆንም የሰውየው አእምሮ ግን ያለ ፍሬ ነው። «በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው» የተባለውም ለዚህ ነው። እዚህ ላይ «ያለፍሬ ነው» የተባለው «አእምሮዬ» ነው። ያለፍሬ ማለት ምን ማለት ነው? በአእምሮዬ የምረዳው ነገር የለም፤ ወይም አእምሮዬ የተረዳው ፍሬ ነገር የለም ማለት ነው፤ ይህ ግን ትክክለኛ ሁኔታ ነውን? በፍጹም አይደለም፤ «በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው» የሚለው ቃል የሚገልጸው አንድን ችግር ወይም ትክክለኛ ያልሆነ የልሳን ተናጋሪውን ሁኔታ ነው እንጂ መሆን ያለበትን በልሳን የመናገር ዓይነት የሚገልጽ አይደለም። ሐዋርያው ችግሩን አስቀድሞ ከገለጸ በኋላ መፍትሔውን በማስከተል የተናገረው፤ ይህም የሚታወቀው ከዚያ በመቀጠል «እንግዲህ ምንድነው?» ብሎ ባቀረበው ጥያቄ ነው፤ «መሆን ያለበት ነገር ምንድር ነው?» ማለት ነው ከዚህ ጥያቄ በኋላ ያቀረበው መልስም «በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ» የሚል ሲሆን ይህም ጸሎትም ሆነ መዝሙር በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአእምሮም መሆን እንዳለበት የሚናገር መርህ ነው። ሳይረዱና ሳይተረጐሙ በልሳን መጸለይ በመንፈስ ብቻ መጸለይ ነው፤ እንዲህ የሚያደርግ ሰው አእምሮው ያለ ፍሬ ከመሆኑም ሌላ ወደ ሌሎች መተርጐም ባለመቻሉም ማኀበሩ «አሜን» ማለትም መታነጽም አይችልም። በቍ.16 ላይ «እንዲያማ ካልሆነ» የሚለው ሐረግ በመንፈስም በአእምሮም ካልሆነ ማለት ነው፤ በልሳን የሚናገረው በመንፈስም በአእምሮም ሆኖ ካልጸለየና ካልዘመረ ለሰሚዎቹ ምንም ጥቅም አያስገኝም፤ «እንዲያማ ካልሆነ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል?» የተባለው በዚህ ምክንያት ነው። በዚህ ንባብ «ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው» የሚለው አዲሶችን ጨምሮ ለነገሩ እንግዳ ሆነው ተቀምጠው የሚናገረውን የሚሰሙ አማኞችን ያመለክታል። በልሳን የሚናገረው አማኝ በመንፈስ ሊባርክ ወይም ሊያመሰግን ይችላል፤ «አንተማ መልካም ታመሰግናለህ» ስለተባለ ምስጋናው ትክክለኛና መልካም የሆነ ነው። ሆኖም የሚያመሰግነው በመንፈስ ብቻ እንጂ በአእምሮም ባለመሆኑ ሊተረጐመው አይችልም፤ ስለዚህ «ሌላው ግን አይታነጽበትም» ተባለ። በጸሎትና በምስጋና ጊዜ መታነጽ ሊገኝ የሚችለው ወደ እግዚአብሔር የሚናገሩት ቃላት የሰሚውን ልብ በመንካት በሚፈጥሩት አድናቆትና ተመስጦ መሆኑን መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም ጸሎትና ምስጋና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ እንጂ ወደ ሰው የሚተላለፍ መልእክት አይደሉምና።
ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ በልሳኖች የመናገር ስጦታ እንደ ነበረው ሊገልጥ «ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ» ይላል፤ ነገር ግን በማኅበር በመንፈስ ብቻ ሆኖ ልሳኖችን መናገር ተገቢ አለመሆኑን ለተናገረው መርህ ራሱም ይገዛ ነበር። ይህንንም ሲገልጽ «ነገር ግን ሌሎችን አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላትን በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ» ብሏል። በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ በልሳን መናገር በአእምሮ ከመናገር ጋር በተቃራኒ ተነጻጽሯል። እዚህ ላይ «በልሳን መናገር» ሲባል የመተርጐም ስጦታ አብሮ የሌለበትን በልሳን የመናገር ስጦታ እንደሚያመለክት መዘንጋት የለብንም፤ ልሳን በዚህ መልክ ሊነገር የሚችለው ተናጋሪው በመንፈስ ብቻ ሆኖ ሲናገር ነው። በአእምሮ መናገር ግን ተናጋሪው በራሱ መደበኛ ቋንቋና በሕዝቡ ቋንቋ መናገሩን የሚያመለክት ነው፤ ስለሆነም በመንፈስ ብቻ ሆኖ ሐሳቡን ሳይተረጉሙ እልፍ (10 ሺህ) ቃላትን ከመናገር ይልቅ 5 ቃላትን በአእምሮ ሆኖ መናገር ሌላውን ያስተምራል፤ ማኀበሩን ያንጻል።
ቍ. 20-26 «ወንድሞች ሆይ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎች እና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፏል። እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ አብደዋል አይሉምን? ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፤ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።»
በልሳኖች መናገርን በተመለከተ የቆሮንቶስ አማኞች የነበራቸው መረዳትና የአጠቃቀም ሥርዓት እንደ ሕፃናት መሆን እንደሌለበት ሐዋርያው ይመክራል ለክፋት ነገር ካልሆነ መቀር በአእምሮ ሕፃናት መሆን አይገባም ሳይተረጉሙ በማኅበር መካከል በልሳኖች መናገር በአእምሮ አለመብሰልን ወይም ሕፃንነትን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ «በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ» «በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ» የሚሉ መመሪያዎች ተሰጡ። በዚህ ዓለም እውቀት በእጅጉ መማር ቢቻል እንዲሁም በዕድሜ መግፋት ቢኖር እንኳ መንፈሳዊ ስጦታን በአገባብና በሥርዓት መጠቀም ካልተቻለ በአእምሮ ሕፃናት መሆን ነው። እስኪ ረጋ ብለን እናስተውለው በማኅበር መካከል ትርጉሙን ማንም ሰው እንደማይረዳው እየታወቀ በሌላ ቋንቋ መናገር የአእምሮ ሕፃንነት ከሚባል በቀር ምን ሊባል ይችላል? በዘመናችንም እንዲህ ያለ የአእምሮ ሕፃንነት በክርስትናው ዓለም በስፋት ይታያል፤ ለዚያውም ተናጋሪ ሕዝብ ያለውን ሌላ ቋንቋ ሳይሆን በምላስና በአንደበት ላይ በድንገት የሚመጡ ትርጉም አልባ የፊደላት ቅጥልጥሎሾችን እያሰሙ በማኅበር መካከል ሲንዘፈዘፉ መታየት የተለመደ የአእምሮ ሕፃንነት ሆኗል። እግዚአብሔር ግን ሕዝቡ ወደ ማስተዋል ተመልሶ ከዚህ የአእምሮ ሕፃንነት እንዲመለስና በአእምሮ እንዲበስል በቃሉ ይናገራል።
እስከ አሁን እንደተመለከትነው በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ይነገሩ የነበሩ ልሳኖች የሰዎች መነጋገሪያ ቋንቋዎች ናቸው። ይህም በይበልጥ ግልጽ የሚሆነው ደግሞ በቍ.22 ላይ ከኢሳ.28፡11-12 ላይ በተጠቀሰልን ክፍል ነው። በዚህም ንባብ እግዚአብሔር ሕዝቡን «ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎች እና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ» እንዲህ ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ» ብሎ የተናገረው ተጠቅሷል። በኢሳ.28፡11 ላይ ይኸው ቃል «በባዕድ አፍ በልዩ ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል» ተብሎ ተገልጿል። ቃሉ የተነገረውም በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ማለትም «ኤፍሬም» ተብለው የተጠቀሱ 10ሩ ነገድና ቀሪዎቹ ሁለቱ ነገድ በእግዚአብሔር ላይ ስላመጹና ለፍርድ አልፈው ስለተሰጡ ነበር። በገዛ ቋንቋቸው የተነገራቸውን ምክርና ተግሣጽ ሰምተው ከዓመፃቸው አልመለስ ሲሉ እግዚአብሔር በባዕድ አፍ በልዩ ልሳን እንደሚናገራቸው ገለጸ። እነዚህ እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብለው የተጠሩ ናቸው፤ ሆኖም ይህ ቃል በሚነገር ጊዜ እስራኤላውያን ወደ አለማመንና ወደ አለመታዘዝ ገብተው ነበር። እንዲመለሱ እግዚአብሔር የተለያዩ ነቢያትን እየላከ በቋንቋቸው ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን «አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም» (2ነገሥ.17፡7-14 ተመልከት)። ስለሆነም በሁለተኛ ደረጃ እግዚአብሔር ያደረገው «በባዕድ አፍ በልዩ ልሳን» መናገር ነበር። የሚናገረውም መልእክት «ዕረፍት ይህቺ ናት፤ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህቺም ማረፊያ ናት» የሚል ነበር (ኢሳ.28፡12)፤ ይህም ቃል መልእክቱ በተለይ ለገዢዎች እንደነበር የሚያሳይ ነው። «እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ» የሚል ቃል በዚሁ ቍጥር ላይ ስናነብ በጊዜው የነበረው ደንዳናነት ምን ያህል ከፍ ያለ እንደ ነበር እንረዳለን። እግዚአብሔር በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን የሚናገርበት ዓላማ ግን እንዲሰሙትና ካለማመንና ካለመታዘዝ እንዲመለሱ ነበር ይሁን እንጂ መስማትን እንቢ ባሉ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ይፈርድባቸው ዘንድ ለዓመፃቸው አሳልፎ ሲሰጣቸው እንመለከታለን፤ በኢሳ.28፡13 ላይ «ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ሥርዓት በሥርዓት ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል» ይላል። ይህ በሦስተኛውኛ ደረጃ እግዚአብሔር የሚያደርገው ሲሆን የመጨረሻ ፍርድ እንዲፈጸምባቸው ዓመፃቸው ጫፍ ይደርስ ዘንድ መፈጸም ለማይችሉት ትእዛዝና ሥርዓት እንደሚተዋቸው የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ትእዛዝ በትአዛዝ ሥርዓት በሥርዓት ሥርዓት በሥርዓት፣ በሚሆንባቸው ጊዜ መጠበቅ ስለማይችሉ ሄደው ወደኋላ ይወድቃሉ፣ ይሰበራሉ፣ ተጠምደውም ይያዛሉ። እግዚአብሔር ለዚህ ውድቀት አሳልፎ መስጠቱም እርሱ ለመጨረሻ ጊዜ ለሚፈርደው ፍርድ ሕዝቡን እንደተዋቸው የሚያሳይ ነው። በሌላ አንደበት ለሕዝቡ መናገሩ ግን ከዚህ አስቀድሞ በሕዝቡ መካከል ባለው አለማመን ላይ ይፈርድ ዘንድ ሕዝቡን ለራሳቸው ከመተው በፊት ከደነደነው ልባቸው እንዲመለሱ ለማስጠንቀቅ ነበር።
በሐ.ሥ.2 ላይ የተመለከትነው ልሳን የሰሚዎቹ ቋንቋ ነበር።
በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ግን ይነገር የነበረው ልሳን የራሳቸው የቆሮንቶስ ሰዎች ቋንቋ ሳይሆን የሌሎች ሰዎች ልሳን ነበር። ሆኖም በሁለቱም ስፍራዎች የሚታየው ልሳን የሰዎች መነጋገሪያ ቋንቋ ነበር። በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሌሎች ሰዎች ቋንቋ እንዲነገር ያደረገበት ምክንያት እንደ እስራኤል ሁሉ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ብዙ አለማመንና አለመታዘዝ ስለነበረ እግዚአብሔር እነርሱን ለፍርድ ከመተው አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ ሊናገራቸው ስለፈለገ ነበር፡ የቆሮንቶስ አማኞች «እኔ የጰውሎስ ነኝ፤ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፣ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፣ እኔስ የክርስቶስ ነኝ» እያሉ መለያየት (መከፋፈል) እና ሌላም ብዙ ዓይነት ሥጋዊነት ያሳዩ ነበር (1ቆሮ.1፡12፤ 3፡1-4)፣ ዝሙት (1ቆሮ.5፡1)፣ ለጣዖት የተሠዋውን መብላት(1ቆሮ.8፡7፤)፣ የጳውሎስን ሐዋርያነት አለመቀበል (1ቆሮ.9፡1)፣ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል (1ቆሮ.10፡20)፣ በጌታ እራት ጊዜ መስከር (1ቆሮ.11፡21)፣ የጸጋ ስጦታዎችን ያለፍቅር መገልገል (1ቆሮ.13፡1) በመካከላቸው በስፋት ይታይ ነበር። እነዚህ ሁሉ በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የነበረውን አለማመንና አለመታዘዝ የሚገልጹ ናቸው። በመሆኑም እግዚአብሔር በዚህ አለመታዘዝ ላይ ሊፈርድ የሌሎች ሰዎች ልሳኖች በመካከላቸው በተአምር እንዲነገሩ አደረገ። ስለዚህ የሌሎች ሰዎች ልሳኖች በአማኞች ማኅበር መካከል መከሠታቸው እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ባለማመን የሚመላለሱ አማኞች እንዳሉ ከማየቱ የተነሳ ፍርድ ለማምጣት መዘጋጀቱን የሚያሳይ ምልክት ለመስጠት ነው። ስለሆነም ከኢሳ.28፡11 የተወሰደው ቃል ከተጠቀሰ በኋላ «እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም» ተብሎ ሊጻፍልን ቻለ። «እንግዲያስ» የሚለውን ቃል ልብ ብለን ስንመለከት ቀደም ሲል ለተነገረው ነገር የሚሆን የመደምደሚያ ሐሳብ ቀጥሎ ለመናገር እንደተፈለገ የሚያስረዳ ነው። ስለሆነም «በባዕድ አፍ፣ በልዩ ልሳን» መናገር ባላመኑት እስራኤላውያን ላይ እግዚአብሔር ፍርድን ሊያመጣ እንደነበረው ለማሳየት ምልክት እንደሆነ ሁሉ፣ በማያምኑ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ሰዎች ላይም እግዚአብሔር ፍርድን ያመጣ ዘንድ እንዳለው ሊያሳያቸው የሰጣቸው የፍርድ ምልክት እንደነበረ እንገነዘባለን። የሚያስፈልጋቸው በጊዜው ያለበትን ሁኔታ የሚመለከት የሚወቅስ፣ የሚመረምር፣ በልብ የተሰወረውን የሚገልጥ ቃል ነው፤ ይህን የጊዜውን ቃል የሚያገኙት ደግሞ ትንቢት በመናገር ስጦታ ውስጥ ነው፤ በመሆኑም «ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም» ሊባል ቻለ።
በአማኞች ማኅበር ሳይተረጐሙ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩ ወደ ስብሰባው በድንገት ለሚገቡ ላልተማሩ ወይም ለማያምኑ ሰዎች መሰናክል ይሆናል። ሐዋርያው ይህን በተመለከተ ሲናገር «እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ አብደዋል አይሉምን?» በማለት ይጠይቃል። በዚህኛው ንባብ ውስጥ «ያልተማሩ» ሲል የእግዚአብሔርን ነገር በጥልቀት የማያውቁ እንግዶችን ሲያመለክት፣ «የማያምኑ» ሲል ደግሞ ጨርሶውኑ በጌታ የማያምኑ በውጭ ያሉትን ሰዎች ያመለክታል። «አብደዋል አይሉምን?» የሚለው ጥያቄ በዘመናችን የምንሰማቸው የሐሰት ልሳኖች በወንጌል ሥራ ላይ ካላቸው አሰናካይነት አንጻር ሊነሣ የሚገባው ጥያቄ ነው፤ ለክርስትናው እንግዳ ለሆኑ ሰዎችና ለብዙ የማያምኑ ሰዎች መሰናክል እየሆኑ ካሉት ምክንያቶች ቀዳሚውን ቦታ የያዙት በእውነተኛ ልሳኖች ስም ሲባሉ የሚሰሙት እነዚህ የሐሰት ልሳኖች መሆናቸው ግልጽ ነው። መዳን በኢየሱስ ብቻ እንደሆነ የነገረው የምሥራቹን ቃል ተሰብኮላቸውም ሆነ ሳይሰበክላቸው በአማኞች መካከል እየሆነ ያለውን ለማየት ወደ አንዳንድ የክርስቲያኖች ማኅበር የሚሄዱ ሰዎች ከእኛ ይሻላሉ ያሏቸው አማኞች እየተንዘፈዘፉና እየተንቀጠቀጡ ወይም እየወደቁ እየተነሡ ልሳን የሚሉትን የፊደላት ቅጥልጥል ለማሰማት እንደ ሕፃን ልጅ ሲሽቀዳደሙ፣ አእምሮቸውን ስተው ሲወድቁ ሲንጫጩና ሲተረማመሱ ተመልክተው «እነዚህስ አብደዋል እንዲህስ ከመሆን ቢቀር ይሻላል» ብለው እየተሰናከሉ መጥፋታቸው አሳዛኙ የዘወትር ክስተት ሆኗል። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች በኢየሱስ ማመን ማለት ያ እነርሱን ያጋጠማቸው ሥርዓት የለሽ ክስተት ብቻ እስኪመስላቸው ድረስ ሌላ ጊዜ ስለ ኢየሱስ ሲመሰክርላቸው ያው የሚሆን እየመሰላቸው ነጻ ሆነው ለመቀበል ይቸገራሉ ለዚህ ተጠያቂ የሆኑትና በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዘመኑ የሐሰት ልሳን ባለቤት የሆኑ ሰዎች ወደ አእምሮአቸው ተመልሰው ቀኑ ሳያልፍባቸው ንስሐ ሊገቡ ያስፈልጋል።
በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ሲነገር የነበረው ልሳን እውነተኛ ልሳን ቢሆንም እንኳ፣ በአጠቃቀም ጉድለት የተነሣ ማለትም ተራ መጠበቅና የልሳኑ ትርጐም በሌለበት ሁሉም እየተንጫጩ ሲናገሩ በመታየታቸው ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ ሊሰናከሉ ይችሉ ነበር፤ ትንቢት ሲነገር ግን የማያምኑ ወይም ያልተማሩ ሰዎች ቢገቡ ግን መልእክቱን በገዛ ቋንቋቸው የሚሰሙት በመሆኑ በእጅጉ ይጠቀማሉ፤ «ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል በሁሉም ይመረመራል በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ይሰግዳል» የሚለው ቃል ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ምንም እንኳ ትንቢት መናገር ዓላማው ለሚያምኑት ቢሆንም መልእክቱ ለማንኛውም ሰው የሚሰማ በመሆኑ በድንገት የገቡት የማያምኑ ሰዎች ላመኑት ሰዎች በመጣው መልእክት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በዚያ ማኅበር ያለውን የእግዚአብሔርን መገኘት ተረድተው ወድቀው ለእርሱ ክብርን ይሰጣሉ፤ ይህም ልባቸው በሰሙት ነገር መማረኩን ያሳያል ።
ቍ.26-33 «እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፣ መግለጥ አለው፣ በልሳን መናገር አለው፣ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤ የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል። ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ። የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ። እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።»
በዚህ ክፍለ ንባብ በልሳን መናገርና በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም አማኞች በሚሰበሰቡበት ማኅበር ውስጥ ከሚኖሩት የተለያዩ የጸጋ ስጦታዎች ጋር አብረው መጠቀሳቸውን እንመለከታለን። ይህም በልሳን መናገርም ሆነ የመተርጐሙ ስጦታ ገና ስላልቀረ ማለትም ገና በሥራ ላይ ስለነበረ፣ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያንም ከነበረችበት ውድቀት አኳያ ስጦታው አስፈላጊ ስለነበረ እንደ መዝሙር፣ እንደትምህርት፣ እንደ መግለጥ ሁሉ ስጦታው አገልግሎት ላይ ስለነበረ የተነገረ ነው። ይሁን እንጂ በ1ቆሮ.13፡8 ላይ «ልሳኖችም ሆኑ ይቀራሉ» የሚለውን ስናጠና በግልጽ እንደተመለከትነው ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ እግዚአብሔር ስጦታውን ያስቀረው በመሆኑ በዘመናችን በማኅበር ስንሰበሰብ እንደማንኛውም ተአምራዊ ስጦታ ሁሉ ልሳኖችም ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር አብረው ሊኖሩ እንደማይችሉ እንገነዘባለን።
በልሳኖች የመናገር ስጦታ እስከነበረበት ጊዜ ድረስ የነበረው ዓላማ «ሁሉ ለማነጽ ይሁን» ተበሎ በተነገረው ቃል ውስጥ መገለጹን እንመለከታለን። ይህ የማነጽ ዓላማም በማኅበር መካከል አገልግሎት ላይ የሚውሉ የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባ ዓላማ መሆኑ በ1ቆሮ.14፡12 ላይ ተደንግጓል። ስለሆነም በልሳኖች መናገር ማኀበሩን ለማነጽ ይውል ዘንድ ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሦስት የአጠቃቀም ድንጋጌዎችን በ1ቆሮ.14፡27-28 ባለው ክፍል ጽፎላቸውል። እነዚህንም ድንጋጌዎች የሚጽፍላቸው «በልሳን የሚናገር ቢኖር» እያለ ነው። «ቢኖር» ሲል በማኅበር መካከል በልሳን የሚናገር የግድ ይኖራል ማለት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ሆኖም አልፎ አልፎም ቢሆን በሚኖር ጊዜ እንዲጠቀሙባቸው የአጠቃቀም ሥርዓቶቹን ይጽፍላቸዋል። እነዚህንም ሥርዓቶች በዘመናችን የሚታየው የሐሰት ልሳን ከሚከተለው የአጠቃቀም ልማዶች ጋር በማነጻጸር ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን።
- 1. ብዛት
-
በማኅበር መካከል በልሳን የሚናገር ቢኖር «ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት» ሆነው መናገር እንዳለባቸው ተገልጿል(ቍ.27)። «ቢበዛ ሦስት» የሚለው ቃል እንደሚያስረዳው ከሦስት አማኞች በላይ በልሳን እንዲናገሩ አይፈቀድም ማለት ነው። በዘመናችን የሚታየው የሐሰት ልሳን በሚነገርባቸው ስብሰባዎች ግን ቃሉን ያስተምራሉ ከሚባሉ ሰዎች ጀምሮ ልሳን አለኝ የሚል ሁሉ በጉባኤው ውስጥ፣ ኅሊናን ጥሎ፣ በአንደበቱ ትርጉም የለሸ አንዳች ድምጽ ሲያወጣ እንዲሁም ከመድረክ መሪዎች «ሁላችሁም በልሳኖቻችሁ ጸልዩ» እየተባለ ሲበረታታ ይታያል።
- 2. ተራ መጠበቅ
-
በልሳን የሚናገር ሊከተለው ይገባ የነበረው ሁለተኛው ድንጋጌ «በተራቸው ይናገሩ»(ቍ.27) የሚል ነው። በተራ መናገር ሲባል አንዱ መናገር የጀመረውን ሲጨርስ ሌላው ከእርሱ ቀጥሎ የሚናገርበትን ሥርዓት የሚያመለክት ነው። በዘመናችን ግን ሰዎች ልሳን የሚሉትን ነገር ተራ ሳይጠብቁ በአንድ ጊዜ በማሰማት እንደሚጠቀሙበት ከተናጋሪዎቹ ጀምሮ ሁሉም ሰው በግልጽ የሚያውቀው ነው። ይህም መተረማመስን በመፍጠር አንዳንድ አማኞችን ግራ ያጋባ ሲሆን የማያምኑትን ደግሞ «እነዚህ ሰዎች አብደዋል» እንዲሉ ያደረገ ሆኗል።
- 3. መተርጐም 4.
በልሳኖች የተነገረው መተርጐም እንዳለበት የሚገልጸው ይህ ድንጋጌ በ1ቆሮ.14 ውስጥ በስፋትና በተደጋጋሚ የተነገረ መለኮታዊ ሥርዓት ነው። በዚህ ስፍራ ላይም «አንዱም ይተርጐም» ተብሎ በአጽንዖት ተነግሯል (ቍ.27)። በልሳኖች መናገር ማኀበሩን ማነጽ የሚችለው ተተርጐሞ በማኅበር የተሰበሰቡት እንዲሰሙት ሲደረግ ብቻ ነው። ስለዚህ የመተርጐም ስጦታ ያለው በሌለበት በልሳን የመናገር ስጦታን መጠቀም አልተፈቀደም ማለት ነው። በዘመናችን ግን ሰዎች «ልሳን» ብለው የሚያሰሙት ድምጽ ልሳን ባለመሆኑ ምክንያት ሊተረጐም ስለማይችል ከመሪዎች ጀምሮ ስለመተርጐሙ የሚያስብ የለም። አልፎ አልፎ አንዳንዶች እንተረጐማለን የሚል እንዳሉ ቢታወቅም ልብ ብሎ ያስተዋለ ሰው የተነገረው ትርጉም የውሸት ወይም የፈጠራ መሆኑን ይገነዘባል። አንድ ወይም ሁለት መስመር የሚሆን የሐሰት ልሳን ተሰምቶ አንድ አንቀጽ የሚወጣው ትርጐም ሲነገር የሚሰማ ሰው ትርጉሙ ፈጠራ መሆኑ አይጠፋውም። ይህን የተገነዘበ ሰው ከዚያ በኋላ በሐሰት ልሳኖች መታለል የለበትም።
5. ዝም ማለትበልሳን መናገር ብቻ የተሰጠው የቆሮንቶስ አማኝ ልሳኑን በጀመረ ጊዜ የሚተረጉምለት ሰው በማኀበሩ ውስጥ ከሌለ ዝም ማለት ይኖርበታል፤ ይህም «የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር» ተብሎ ተነግሯል(ቍ.28)። «ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር» የሚለው መመሪያ «ዝም ይበል» ከተባለ በኋላ የተነገረ ነው። ስለሆነም ተርጓሚ ከሌለ በልሳን ወይም በሌላ ቋንቋ መናገር የጀመረውን በዝምታ ሆኖ፣ ጽምፅ ሳያሰማ፣ በውስጡ፣ ለራሱና ለእግዚአብሔር ተናግሮ መፈጸም እንደነበረበት የሚያሳይ ነው። በዘመናችን ግን ለዚያውም «ልሳን» ያልሆነውን ነገር ያለማቆም በማሰማት ማኀበሩን ማወክ የተለመደ ነው። በተጨማሪም ይህንኑ ትርጉም የለሽ ድምፅ የሚያሰማው ሰው ዝም ብሎም ቢሆን ለራሱና ለእግዚአብሔር ሊናገርበት እንደማይችልም ግልጽ ነው።
በመቀጠል ደግሞ በማኅበር መካከል ስለነበረው የነቢያት አገልግሎት የተሰጠውን መለኮታዊ ሥርዓት እንመለከታለን።
- 1. በቅድሚያ በአንድ ጉባኤ ጊዜ የሚመክር፣ የሚያንጽና የሚያጽናና ቃል ለማኀበሩ ማምጣት የሚችሉት ነቢያት ብዛታቸው ሁለት ወይም ሦስት መሆን እንዳለበት ተነግሯል፤
- 2. ቀጥሎ «ሌሎች ይለዩአቸው» ተብሏል። ይህም አስቀድሞ በሚወጣ ፕሮግራም ተናጋሪዎቹ ከወዲሁ የሚታወቁ ባለመሆናቸው ከሥጋ ወይም ከሰይጣን የሆነ ነገር ተደባልቆ ሊነገር ስለሚችል የተሰጠ ሥርዓት ነው። ነቢያቱ በሚያገለግሉበት ጊዜ አንድ በአንድ ወይም ተራ በመጠበቅ እየተደማመጡ እንጂ በሁከት መሆን እንደሌለበት ተደንግጓል። አንዱ ሲናገር ሌላው አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ማለት አለበት፤ የዚህ ምክንያትም «የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና» ተብሎ ተገልጿል። ይህም ቃል ሁከት የበዛባቸው የዚህ ዘመን አገልግሎቶች ከእግዚአብሔር እንዳልሆኑ የሚያስገነዝበን ነው።
በልሳኖች በመናገርና በነቢያት አገልግሎቶች ላይ የተሰጡት እነዚህ የአጠቃቀም ሥርዓቶች በዚህ መልእክት ከመጻፋቸው በፊት በየስፍራው ባሉ አብያተክርስቲያናት ይጠበቁ እንደነበር ማወቅ እንችላለን። ምክንያቱም ሐዋርያው ሲጽፍ «በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው» ብሏል (ቍ.33)። በአንድ ስፍራ የምትሰበሰብ ቤተክርስቲያን ከሌሎቹ በመለየት ተናጠላዊ በሆነ መልኩ በራሷ ሥርዓትና በራሷ መንገድ መሄድ እንደሌለባት ከዚህ እንማራለን። አብያተ ክርስቲያናት በትምህርትም ሆነ በእምነት አንድ ሊሆኑ የሚገባቸውን ያህል በሚሰበሰቡበት ጊዜ የሚከናወኑ አገልግሎቶችን በተመለከተ ሊከተሉት የሚገባው የአጠቃቀም ሥርዓት አንድ ሊሆን ይገባል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ የጸጋ ስጦታን እንደፈቃዱ እያካፈለ የሚሰጠው መንፈስ አንድ እንደመሆኑ መጠን የአጠቃቀም ሥርዓቱም እርሱ በሚፈልገው መልኩ አንድ ሊሆን ይገባል።
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በማኅበር መካከል በመናገር ከሚከናወኑ አገልግሎቶች አንጻር የሴቶች ስፍራ ምን እንደሆነ እንማራለን። 1ቆሮ.ምዕ.14 በሙሉ የሚናገረው በልሳኖች መናገር እና ትንቢት መናገር በማኅበር ውስጥ እንዴት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ መሆኑን እስከአሁን በስፋት ተመልክተናል። በማኅበር መካከል በመናገር የሚከናወኑት እነዚህ ሁለት አገልግሎቶች በሚገባ ከተገለጹ በኋላ «ሴቶች በማኅበር ዝም» ይበሉ። ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደምና» የሚል መለኮታዊ ሥርዓት ተሰጠ። ይሁንና በዘመናችን «ልሳንም» ሆነ «ትንቢት» እንናገራለን በሚል ሰዎች ማኅበር ውስጥ ሴቶችም በስፋት እንዲናገሩ መፍቀዱ «ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ» ለሚለው የመንፈስ ቅዱስ ሥርዓት አለመታዘዝ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ አለን የሚሉት «ልሳን» ወይም «ትንቢት» ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጠ አለመሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው። ሴቶች በማኅበር መካከል እንዲናገሩ ያልተፈቀደበት ምክንያት አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ሴቶች ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ስጦታ ወይም ችሎታ ከማቃለል ሳይሆን በማኅበር መካከል ዝም በማለት እግዚአብሔር እነርሱን ያስቀመጠበትን የተገዢነት ስፍራ በማኅበር መካከል እንዲያሳዩ ስለተፈለገ ነው። ይህም «እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም» በሚለው ቃል ውስጥ በግልጽ ተነግሯል። ይሁንና በዘመናችን በግልጽ ለተነገረው ለዚህ ቃል ተገቢ ያልሆኑ ትርጉሞችን በመስጠት ሴቶች በቤተክርስቲያን ማኅበር መካከል እንዲናገሩ የማደፋፈር ሥራ በስፋት ሲሠራ ይታያል። ይህም በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተነሣ የዘመናችን እልከኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ «ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና» ይላል (ቍ.35)፤ ስለሆነም በጌታ የሆኑት እህቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ «ነውር» ያለውን ነገር እንዲያደርጉ የሚያደፋፍሯቸውን ሰዎች ከመስማት ይልቅ ቃሉ የሚለውን መስማት ይኖርባቸዋል። ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶበት በአጽንዖት የተነገረ መሆኑን የምናውቀው ደግሞ «ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ» በሚለው ቃል ነው። ይህም ቃል ሴቶች ጥያቄ እንኳ ቢኖራቸው ጥያቄውን ማቅረብ የሚችሉት በቤት ወይም በግል ደረጃ እንጂ በቤተክርስቲያን ማኅበር መካከል እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ «ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ» የሚለው ቃል የተጻፈው በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ሴቶች ማኀበሩን ያውኩ ስለነበረ ነው የሚል ትርጉም ሲሰጠው ይታያል፤ ሆኖም ይህ ሥርዓት ከቆሮንቶስ ሴቶች አኳያ ብቻ የተነገረ እንዳልነበረ የሚያሳየው ቃል «ምነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሷልን?» የሚለው ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከቆሮንቶስ እንዳልነበረ ሁሉ የደረሰውም ወደ ቆሮንቶስ ብቻ አልነበረም፤ ለምሳሌ በኤፌሶን ለነበረች ቤተክርስቲያንም ሴቶች እንዲያስተምሩ አልተፈቀደም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በጊዜው በኤፌሶን ተቀምጦ ሲያገለግል ለነበረው ለጢሞቴዎስ ይህንን በተመለከተ ሲጽፍለት «እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለቁጣና አለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ፤.... ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም። አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። የተታለለም አዳም አይደለም፤ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች» ብሏል (1ጢሞ.2፡8-14)። በመሆኑም በሌሎች ስፍራዎችም ሴቶች በማኅበር መካከል ዝም እንዲሉ ይደረግ ነበረ። በተጨማሪም ሴቶች በማኅበር መካከል ሥርዓት በሌለው መልኩ በሁካታ ከሚያሰሙት ንግግር ዝም እንዲሉ ብቻ ሳይሆን ከማስተማርም ዝም እንዲሉ መደንገጉን ለጢሞቴዎስ የተጻፈው ቃል በግልጽ ያስረዳል፤ እንዲሁም በዚህ ክፍል «ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር»፣ «በዝግታ ትኑር» በሚሉት ቃላት በቆሮንቶስ 14 ላይ እንደተገለጸው ሁሉ ሴቶች በማኅበር ዝም የሚሉት መገዛታቸውንና በዝግታ መኖራቸውን ለማሳየት እንጂ ችሎታ ስለሚያንሳቸው ወይም ተጽዕኖ ስለተደረገባቸው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ስለሆነም ሴቶችን በተመለከተ በተነገረው በዚህ መለኮታዊ ሥርዓት አብያተክርስቲያናት ሁሉ መመራት እንዳለባቸው እንገነዘባለን።
ቍ. 37-40 ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን እንመለከታለን። በልሳን መናገርንም ሆነ ትንቢት መናገርን እንዲሁም ሴቶች በማኅበር ያላቸውን ስፍራ በተመለከተ ሐዋርያው እየጻፈ ያለው የጌታን ትእዛዝ እንደሆነ አስረግጦ ይናገራል። «ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው» ብሎ ሐዋርያው የጠቀሳቸው ሰዎች ራሳቸውን ነቢይና መንፈሳዊ አድርገው በማቅረብ ሐዋርያው የጻፈው ቃል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማስተባበል የሚፈልጉትን ሰዎች ያመለክታል፤ በተለይም «ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ» የሚለው ቃል የጌታ ትእዛዝ እንደሆነ የማያምኑና «ነቢይ» ወይም «መንፈሳዊ» የሆኑ የሚመስላቸው የዘመናችን ሰዎች ይህ ቃል የጌታ ትእዛዝ እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል፤ ለማወቅ ካልፈለጉ ግን «የማያውቅ ቢኖር አይወቅ» ተብለው ለራሳቸው ይተዋሉ።
ሐዋርያው እነዚህን ሥርዓቶች ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈላቸው ትንቢት መናገርንም ሆነ በልሳኖች መናገርን እንዳይጠቀሙባቸው ለመከልከል አልነበረም። እንዲያውም ትንቢት መናገር ማኀበሩ እንዲታነጽ ካለው የጎላ ድርሻ አንጻር በብርቱ እንዲፈልጉት የተነገረ ሲሆን በልሳኖች የመናገር ተአምራዊ ስጦታን በተመለከተ ደግሞ የሚቀርበት ወይም የሚያቆምበት ጊዜ ገና ስለነበርና በዚያን ጊዜ ገና ያልቀረ በመሆኑ «በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ» ተብሏል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጠው እውነተኛ ልሳን እስከተነገረ ድረስ የቆሮንቶስ አማኞች ሊከለክሉ አይገባቸውም ነበር። በእኛ ዘመን ግን በ1ቆሮ.13፡8 «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ስናጠና እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ከሌሎች ተአምራዊ ስጦታዎች ጋር ልሳኖችንም ስላስቀራቸው እንዲነገሩ ሊፈቀድላቸው የሚችሉ ልሳኖች አይኖሩም። እዚህ ላይ «አትከልክሉ» የተባለው እውነተኛውን ተአምራዊ ልሳን እንጂ በዘመናችን የምንሰማውን የፊደላት ቅጥልጥል የሆነውን ነገር እንዳልነበረ አንባቢው ልብ ሊል ይገባል። ስለዚህ ጥቅሱን አለቦታው በመጠቀም በልሳን ስም እንደዚህ ዓይነቱን ትርጉም የለሸ ድምጽ የሚያሰሙትን «አትከልክሉ» እንደተባለ ተደረጎ መውሰድ የለበትም።
የሐሰት ልሳኖች አጀማመርና አመጣጥ
እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ካኖራቸው ተአምራዊ ስጦታዎች መካከል አንዱ የነበረው በልሳኖች የመናገር ስጦታ ከሌሎቹ ተአምራዊ ስጦታዎች ጋር አብሮ እንደቀረ መመልከታችን ይታወሳል። ከዚያ በኋላ በክርስትናው ዓለም ታሪክ ውስጥ ልሳኖችን እንናገራለን ሲሉ የነበሩት ሁሉ ሰይጣን በስንዴው መካከል እንክርዳድ አድርጎ የዘራቸው (ማቴ.13፡24-25) የሐሰት አስተማሪዎችና ተከታዮቻቸው ነበሩ። ከቤተክርስቲያን ታሪክ የምንረዳውን ይህንን እውነታም ቀጥሎ እናቀርባለን።
የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን ለማጥቃት ሰይጣን መሣሪያ አድርጓቸው ከነበሩትና ልሳን እንናገራለን ይሉ ከነበሩት ቡድኖች መካከል ዋነኞቹ ግኖስቲኮች ናቸው። እነርሱም በሐ.ሥ.8 ላይ የተጠቀሰው እና «አምኛለሁ» ብሎ ወደ ክርስትናው ገብቶ እንደነበረ የሚታወቀው የሰማርያው ጠንቋይ የሲሞን ተከታዮች እንደሆኑ በቤተክርስቲያን ታሪክ ይነገራል። በእነዚህ ቡድኖች መካከል የቋንቋነት ጠባይ የሌላቸው በአፍ ላይ የሚደመጡ ፊደላትን ማሰማት የተለመደ ነበር። በኮፕት፣ በአራማይክና በግሪክ ቋንቋ በተጻፉት የግኖስቲኮች መጻሕፍት ውስጥ እነዚህ የሐሰት ልሳኖች ተቀላቅለው ተገኝተዋል። ለምሳሌ «የግብጻውያን ወንጌል» ተብሎ በሚታወቅ አንድ መጽሐፍ ውስጥ የተገኘው ሊጠቀስ ይችላል።
እነዚህ ግኖስቲኮች ስሜታዊ በሆነ መልኩ በተለይ ምንም የማያውቁ ሞኞች ሴቶችን መንፈስን እንድትቀበሉ ትንቢትን እንድትናገሩ እናደርጋችኋለን እያሉ ያታልሉ እንደነበር ተመዝግቧል። ለምሳሌ ከ120 - 205 የነበረው ኢሬኔየስ (Irenaeus) የተባለው ሰው ማርኩስ (Marcus) የተባለው አንድ የጥንት ግኖስቲክ ምንም የማያውቁ ሴቶችን እንዴት ያታልል እንደነበረ ሲናገር እንዲህ ብሏል። «ማርኩስ ጨዋታውን (ማታለሉን) እንዲህ እያለ ይጀምራል፤ 'እኔ አንቺን የመንፈሳዊ ስጦታዎቼ ተካፋይ ላደርግሽ እፈልጋለሁ፤ የሁሉ አባት መልአክሽን በፊቱ ሁልጊዜ አድርጓልና። ..... አሁን ያንቺ መልአክ በመካከላችን አለ፤ አንድ ልንሆን ያስፈልጋል። መንፈሳዊ ስጦታን ከእኔና በእኔ ተቀበይ፤ ምናልባት አንቺ እኔን፣ እኔም አንቺን እንሆን እንደሆነ ሙሽራዋን እንደምትጠብቅ ሙሽሪት ራስሽን ሸልሚ። በጋብቻ ክፍልሽም ውስጥ የብርሃንን ሕዋስ አኑሪ፤ ባል የሚሆንሽን ከእኔ ተቀበይ፤ እርሱ ሲቀበልሽ አንቺም ተቀበይው፤ እነሆ መንፈሳዊ ስጦታ ባንቺ ላይ ነው፤ አፍሽን ክፈቺና ትንቢት ተናገሪ' (ምናልባት ይቺ ሴት በትንሹም እንኳ ከተቃወመች) 'ባንቺ የተከሰተው ምንም ይሁን ምን አፍሽን ክፈቺና ተናገሪው፤ ትንቢትም ትናገሪያለሽ'» ይላት እንደነበረ ተናግሯል። በተጨማሪም ኢሬኔየስ ሲናገር «ከዚያ በኋላ እርስዋ በእነዚህ ቃላት በከንቱ እየተነፈሰችና እየተሟሟቀች ትንቢት እንደምትናገር በመጠበቅ በነፍስዋ በጣም ትጎመጃለች፤ ልብዋም በኃይል እየመታ ሥርዓት በሌለው መልኩ በስሜት ተውጣ ትርጉም የሌላቸውና ስሜት የማይሰጡ ነገሮች በእርስዋ ላይ እንደተከሰቱ አድርጋ ከአፍዋ ታወጣለች። ..... ከዚያ በኋላም ራስዋን ነቢይት እንደሆነች ትቁጥራለች ማርኩስንም የእርሱን ስጦታ ስላስተላለፈባት ምስጋናዋን ትገልጽለታለች።» ብሏል። ስለሆነም በዘመናችን እንደሚታየው ሁሉ በግኖስቲኮች ዘንድ ሰዎችን ስሜት ውስጥ በማስገባት በአፍ ላይ የመጣውን ስሜት የሌለው ነገር በትንቢት መልክ እንዲናገሩ በማነሳሳት ከፍተኛ የማሳት ሥራ ይሠራ እንደነበር በግልጽ የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሐሰት አስተማሪዎችና ከሐሰተኞች ነቢያት መካከል እንደነበረ የሚታወቀው «ሞንታነስ» የተባለ ሰው የሐሰት ልሳን ይናገር ነበር፤ ይህ ሰው በታናሽ እስያ ውስጥ በምትገኘው በፍርግያ ውስጥ በነበረች ፔቹዛ በተባለች መንደር ይኖር የነበረ ሰው ነው።ወደ ክርስትናው ውስጥ ከገባ በኋላ በ2ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሁለት ሴቶችን በማስከተል በመንፈስ ተሞልቻለሁ እያለ በስሜት ተውጦ እንግዳ ነገሮችን ከአፉ ያወጣ ነበር። እንዲያውም ይባስ ብሎ በዮሐ.14፡16 ላይ «እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል» ብሎ ጌታ የተናገረውን የተስፋ ቃል በመጠቀም በተስፋው ቃል መሠረት አጽናኙ የእውነት መንፈስ በእርሱ ሥጋ ውስጥ እንደመጣ በድፍረት ያስተምር የነበረ ሰው ነው።
ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁለቱ ሴቶች ፕርስካ እና ማክሲ ሚላ የሚባሉ ሲሆን እንደ እርሱ ሁሉ ቀጥተኛ መገለጥና ራእይ ተቀብለናል የሚሉ ነበሩ፤ እንዲያውም ፕርስካ የተባለችው ጌታ ኢየሱስ በራእይ በሴት ቅርጽ(ምሳሌ) እንደታያት ተናገራለች። ሞንተነስ ክርስቶስ በእርሱ ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣና የእግዚአብሔርም መንግሥት እርሱ «አዲሱቱ ኢየሩሳሌም» ብሎ በጠራት በመኖሪያ መንደሩ በፔፑዛ እንደሚመሠረት በዚያች መንግሥት ውስጥም እርሱ ዋነኛ ተዋናይ እንደሚሆን አስተምሯል። በዚህም የሐሰት ነቢይ መሆኑን አረጋግጧል። እርሱና ተከታዮቹ ራእይ ታየኝ፣ ተገለጠልኝ፣ በመንፈስ ተሞላሁ በማለት እውነትን ወደማወቅ ያልደረሱ ሰዎችን ያሳሳቱ ቢሆንም በዚያች በጥንቷ ቤተክርስቲያን ግን ተቀባይነት አላገኙም።
ሰይጣን በግኖስቲኮችና በሞንታነስ አማካኝነት የጀመረው እንደዚህ ያለው የሐሰት አሠራር ከጊዜ በኋላ እየከሰመ ሄዶ የጠፋ ቢመስልም ብዙ ምዕተ ዓመታት ካለፉ በኋላ በአንዳንድ የሐሰት ነቢያትና የሐሰት አስተማሪዎች አማካኝነት ከ18ኛው ምዕተ ዓመት መግቢያ ጀምሮ በድጋሚ ሲታይ እንመለከታለን፤ ከዚያም ጊዜ አንስቶ «ልሳን» ተብለው የተጠሩ ተመሳሳይ ክስተቶች እየታዩ የመጡ ሲሆን በየጊዜው እያደጉ ሄደው አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ ችለዋል።
በአውሮፓ ውስጥ የሐሰት ልሳን የተጀመረው ራሳቸውን የሴቬኖል ነቢያት (Cevenol Prophets) ብለው በሚጠሩ የሐሰት ነቢያት አማካኝነት ነው። እነዚህ ቡድኖች ካሚዛርድስ (Camisards) በመባልም የሚታወቁ ሲሆን በፈረንሳይ አገር በሴቬንስ ተራራዎች አካባቢ ይኖሩ የነበሩና ከ1685 ጀምሮ ከክርስትና ይልቅ የውትድርና እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። በጊዜው በፈረንሳይ ውስጥ የነበረው የሎይስ 14ኛ መንግሥት እነርሱን በኃይል ወደ ሮም ካቶሊክነት ለመቀየር ያደረገውን ሙከራ ለመቋቋም የተደራጁ ታጣቂዎች ነበሩ። የሮም ካቶሊክን ለመቃወም የታጠቀ ሠራዊትን መጠቀም ያስፈልጋል ብለው ያምኑ ነበር። በዚህም መሠረት በመካከላቸው በሚነገሩ የሐሰት ትንቢቶች በመበረታታት ከ1701 እስከ 1710 ከሎይስ (Louis) መንግሥት ጋር ጦርነት አድርገዋል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለም በኢዮኤል ትንቢት መሠረት መንፈስ ቅዱስ ወርዶብናል በማለት የሐሰት ልሳኖችን ከአፋቸው ሲያወጡ ይሰሙ ነበር፤ በእነዚህ ሰዎች ስብሰባ ላይ የሚታየውን ስሜታዊነት በተመለከተ የተጻፈ አንድ ታሪክ «...... ራሳቸውን በእጃቸው ይመታሉ፣ በጀርባቸው ይወድቃሉ፣ ዐይናቸውን ይጨፍናሉ፣ በደረታቸው ይሳባሉ፣ ለጥቂት ጊዜ ተኝተው ይቆያሉ፣ ተወራጭተው ይነሳሉ፣ ወደ አፋቸው የመጣውንም ቃል ያወጡታል (ይሉታል)›› ይላል። ልሳን የሚሉትም ይህንኑ ወደ አፋቸው የመጣውን ነገር ነበር።
በእንግሊዝ አገር የተጀመረው የሜቶዲስቶች እንቅስቃሴ መሥራች የነበረው ጆን ዌስሊ (John Wesley) (1703-1791) የተባለው ሰው ለሐሰተኛ ልሳኖች መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኣ አድርጓል። ጆን ዌስሉ የካሚዛርዶትን እንቅስቃሴና በመካከላቸው የተሰሙትን ሐሰተኛ ልሳኖች ይደግፍና ያበረታታ ነበር። ይህ ሰው «መንፈስ ቅዱስን መቀበል በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ፍጹም ቅድስና ለማግኘት ያስችላል» ብሎ ባስተማረው ትምህርት ተከታዮቹ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት በሚል ከልክ ላለፈ ስሜታዊነት ራሳቸውን ልቅ ያደርጉ ነበር፤ በዚህም በስብሰባዎቻቸው ራሳቸውን መልሶ ግራ ያጋባ የሳቅ መንፈስ ገብቶ ነበር። ለሁለት ለመክፈላቸው ምክንያት ሆኗቸዋል።
እንደዚሁም በእንግሊዝ አገር ጆርጅ ፎክስ (George Fox) 1624-16191 በተባለ ሐሰተኛ ነቢይ የተጀመረውና ከካሚዛርዶች ውስጥ የወጣ የኪዌከሮች (Quakeres) እንቅስቃሴ የሐሰተኛ ልሳኖች ልምምድ የሚታይበት እንቅስቃሴ ነበር። ኩዌከሮች (Quakeres) ስማቸው እንደሚያመለክተው በስብሰባዎቻቸው ውስጥ መንቀጥቀጥና መንዘፍዘፍ በስፋት የተለመደ ነው።
እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና መወለድ የማያምኑ ሲሆን ለትምህርታቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ በውስጤ ተስማኝ የሚሉትን ነገርና ቁርኣንን ጨምሮ ማንኛውንም ሰነድ በማስረጃነት ይቀበላሉ። ብዙዎቹ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት የማያመኑ ሲሆን ሁሉም ሃይማኖት ትክክል ነው የሚል የዮኒቨርሳሊዝም አቋም አላቸው።
በአሜሪካን አገር የሐሰት ልሳኖችን በመጀመር የሚታወቀው ደግሞ አን ሊ ስታንሌይ (Ann Lee Stanley (1736-1784) በተባለች ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ በሄደችና በኩዌከሮች (Quakers) መካከል በነበረች ሴት የተመሠረተው የሼከሮች (Shakers) እንቅስቃሴ ነው። ሼከሮች በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት አያምኑም። መሥራችዋ አን ሊ ስታንሌይ (Ann Lee Stanley) በ1746 ተከታዮቿን በኒውዮርክ አሰባስባ የሐሰት ትምህርቱን ታሰራጭ ነበር፤ ክርስቶስ ሲመጣ እንደ ሴት ሆኖ እንደሚመጣና እርስዋም ያ ማንነት እንደሆነች በድፍረት ትናገር ነበር። በሌላ አባባል ራስዋን እንደ ክርስቶስ አድርጋ ያቀረበች የሐሰት ነቢይት ነበርች። እርስዋም ሆነች ተከታዮቿ በመንፈስ መሳቅ፣ በመንፈስ መስከር፣ በመንፈስ መታረድ፣ በመንፈስ መደነስ... ለተባሉት የሐሰት ትምህርቶችና አሠራሮች ጀማሪዎች ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በስብሰባዎቻቸው ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተወዛወዙ በመዝሙር እየደነሱ የሐሰት ልሳኖቻቸውን ከአፋቸው ያውጡ ነበር። ዊሊያም ሃስኬት (Wiliam Haskett) የተባለ አንድ ጸሐፊ በዚህ ስብሰባቸው ላይ ያየውን ነገር በተመለከተ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል «በቅድሚያ ሴቶች በማይታወቁ ልሳኖች ተናገሩ፤ ከዚያም ዘግናኝ ጩኸትና ረብሻ ተጀመረ፤ ቀጥሎ ኃይለኛ የወንዶች ጩኸት ተሰማና እየቀነሰ ሄደ፤..... መርከብ እየተረጋጋ ባለ ማዕበል ላይ ወዲያና ወዲህ እንደሚዋልል ወደፊትና ወደኋላ ተወዛወዙ፤ ራሳቸውንም ያወዛውዙ(ይንጡ) ልብሳቸውንም በኃይል ይይዙ ነበር፤ ከዚያም በኃይል በወለሉ ላይ ይወድቁ ነበር። ....» ብሏል።
በአውሮፓ ለሐሰተኛ ልሳኖች መስፋፋት ምክንያት ከሆኑት ሐሰተኞች ነቢያትና ሐሰተኞች አስተማሪዎች መካከል ኤድዋርድ አይርቪንግ (Edward Irving) (1792-1834) የተባለው የስኮትላንድ ሰው በዋናነት ይጠቀሳል። ይህ ሰው ቀደም ሲል «ፕሪስቢቴሪያን ቤተክርስቲያን» ተብሎ የሚታወቅ የሃይማኖት ድርጅት አገልጋይ የነበረ ቢሆንም ከ1830 ጀምሮ ከዚያ ወጥቶ የራሱን ትምህርት ማስፋፋት ቀጠለ። ከሐሰት ትምህርቶቹ መካከልም በእጅጉ የሚከፋው «ክርስቶስ ኃጢአትን ያልሠራው ተቋቁሞት ነው እንጂ ኃጢአትን ሊሠራ የሚችል ባሕርይ (Sinful Nature) ነበረው» የሚለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ክርስቶስ በኃጢአት እንዳልተፈተነ (ዕብ.4፡1-5)፣ «ቅዱስና ያለተንኰል ከኃጢአተኞችም የተለየ» እንደሆነ (ዕብ.7፡26)፣ ባጠቃላይ በባሕርዩ ኃጢአት እንደሌለበት (ሉቃ.1፡35፤ 2ቆሮ.5፡21፤ 1ጴጥ.2፡22፤ 1ዮሐ1፡5) ይናገራል። ኤድዋርድ አይርቪንግ ግን ይህንን እውነት ክዶ ማስተማሩ ሐሰተኛ አስተማሪ መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ ሲያስተምር በራእ.20 ላይ የተጠቀሰው ሺህ ዓመት (ሚሌኒየም) በ1867 ይጀምራል ብሎ ሐሰተኛ ትንቢት ተናግሮ ነበር። በዚህም ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ሰው ነው እንግዲህ ልሳን የመጨረሻው ዘመን ምልክት ነው በማለት ተከታዮቹ ያለልክ እየተንዘፈዘፉ ትርጉም የለሽ ድምዖችን እንዲለማመዱ ያደርግ የነበረው። ከተከታዮቹ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ማርች 28 ቀን 1830 የሐሰት ልሳን ከአፍዋ ያወጣችው ሜሪ ካምፕቤል የተባለች ሴት ስትሆን በመቀጠል ደግሞ ኦክቶበር 30 ቀን 1831 ካርደሌ የተባለች እኀትዋ በተመሳሳይ መልኩ ሐሰተኛውን ልሳን ከአፍዋ አወጣች። ከዚያ በኋላም ሆን በስብሰባዎቻቸው ሁሉ በ1ቆሮ14፡34 ላይ የተጻፈውን በመቃረን ልሳንም ሆነ ትንቢት እንናገራለን እያሉ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ሴቶች ናቸው። ኤድዋርድ አይርቬንግ ይባስ ብሎ ኖቬምበር 7 ቀን 1832 የራሱነ 12 ሐዋርያት ሾሞ የሐሰት ትምህርቱን ሐሰተኛ ትንቢቶቹንና ሐሰተኛ ልሳኖቹን ማስፋፋት በመቀጠሉ በዘመናችን ለምናየው ተመሳሳይ የስህተት አሠራር ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሐሰተኛ ልሳኖችን ካስፋፉት እንቅስቃሴዎች መካከል እጅግ አስከፊ የሆነው ደግሞ ጆሴፍ ስሚዝ (Joseph Smith) (1805-1844) በተባለው የሐሰት ነቢይ የተመሠረተውና የተስፋፋው የሞርሞኖች እንቅስቃሴ ነው። ጆሴፍ ስሚዝ ቀደም ሲል የባለራእይ ድንጋይ በሚለው ድንጋይ አማካኝነት እያሟረተ የጠፋ ዕቃ የሚገኝበትን ቦታና የከበሩ ማዕድናት የተቀበሩበትን ቦታ ማሳየት እችላለሁ የሚል ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በ1823 በአንድ ተራራ ውስጥ ተቀብሮ አገኘሁት ያለውን አንድ ጥፍጥፍ ወርቅ ሞርሞን በተባለ የቀድሞ ሰው የተጻፈ ቃል አለበት በማለት በዚያው በሟርት መንገድ በማንበብ ከጥፍጥፍ ወርቁ ላይ ወሰዱኩት ያለውን ቃል በጽሑፍ አድርጎ በ1830 በኒውዮርክ በማሳተም ከአዲስ ኪዳን ቀጥሎ 3ኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፤ ብሎ ተከታዮቹ እንዲመሩበት አድርጓል።
በተጨማሪም በልሳኖች እንናገራሉን የሚሉት ሞርሞኖች አንድ ወንድ ብዙ ሴቶችን ማግባት (Poligamy) እንደሚችል የሚያስተምሩ ሲሆን ጋብቻውም ዘላለማዊ እንደሚሆን ያምናሉ። ይህም ማለት ጋብቻው ከሞት በኋላ ባለው ሕይወትም ይቀጥላል ማለታቸው ነው። ጆሴፍ ስሚዝም ሆነ የሞርሞን መጽሐፋቸው ይህንኑ የከፋ ትምህርት የሚያስተምር ሲሆን በ1852 በይፋ ያወጀው ደግሞ ብሪግሃም ያንግ (Brigham Young) የተባለው አንዱ መሪያቸው ነው። ይህ ሁሉ ክፉ ትምህርት ያላቸው ሞርሞኖች በእምነት መግለጫቸው ላይ በልሳኖች በመናገር እናምናለን ከማለታቸው ሌላ በየስብሰባቸው የሐሰት ልሳኖችን ከአፋቸው ሲያወጡ ይታያሉ። እንግዲህ በዘመናችን የሚሰሙት የሐሰት ልሳኖች ከዚህ ሁሉ የክፋት አሠራር ውስጥ የተገኙ ናቸው። ዘመናዊ በሆነ መልክ በየስፍራው ለሚሰሙት ሐሰተኛ ልሳኖች አጀማመር እስካሁን የተመለከትናቸው ታሪካዊ መነሻዎች ሊጠቀሱ የሚቻል ቢሆንም ቻርለስ ፎክስ ፓርሃም (Charles Fox Parham) (1873-1929) በተባለው ሰው አማካኝነት በአሜሪካን አገር በካንሳስ ግዛት በቶፔካ ከተማ «ቤቴል የፈውስ ቤት» ብሎ በተመሠረተው አንድ የቲዎሎጂ ት/ቤት ውስጥ የታየው ክስተት ግን በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ሰው ቀደም ሲል «ሜቶዲስት» በተሰኘው የክርስትና ሃይማኖት ድርጅት ውስጥ አባል የነበረ ሲሆን በሃይማኖቱ ደንብ መሠረት በ20 ዓመቱ «ጊዜያዊ ፓስተር» ተደርጎ የነበረ ሰው ነው። ይሁንና ብዙ ጊዜ ከመሪዎች ጋር ይጋጭ ስለነበርና ዓለምን በወንጌል ለመድረስ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቆ በልሳኖች መናገር ያስፈልጋል ብሎ ያምን ስለነበር ለብቻው ተለይቶ የራሱን አገልግሎት ጀምሮ የነበረ ሰው ነው። በቶፔካ የቲዎሎጂ ት/ቤት የከፈተውም ወንጌልን በየቋንቋው ለማዳረስ የሚችሉ በተአምራዊ መንገድ በልሳኖች የሚናገር መልእክተኞችን ለማፍራት ነበር። ይሁን እንጂ እርሱም ሆነ ተከታዮቹ በዓለም ሁሉ ቋንቋዎች ወንጌል ለመስበክ የሚያስችሉ ልሳኖችን መናገር አልቻሉም።
ፓርሃም በቤቴል ት/ቤቱ ላሰባሰባቸው ወደ 40 ለሚደርሱ ተማሪዎቹ ይህን አመለካከት አስተምሮአቸው ስለነበር በልሳኖች ለመናገር ከፍተኛ ጥማት አደረባቸው፤ በተጨማሪም ፓርሃምም ሆነ ተማሪዎቹ በመጨረሻው ዘመን ላይ እንዳሉ ያምኑ ስለነበር በልሳኖች የመናገር ስጦታን ለመለማመድ የነበራቸው ጥማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄደ፤ ምክንያቱም ፓርሃም ራሱ ዓለም በ1925 ዓ.ም. ታልፋልች ብሎ ተንብዮ ነበር።* ስለሆነም በኢዮ.2፡28 መሠረት በመጨረሻው ዘመን መንፈስ የሚፈስባቸው ለመሆንና ለዚህ ምልክት ነው ብለው ስላመኑ በልሳን ለመናገር አጥብቀው ይፈልጉ ነበር። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ 1900 ተጠናቆ አዲሱ ምዕተ ዓመት በሚጀምርበት ጊዜ በልሳን መናገር ይችሉ ዘንድ በጾም በጸሎት ከቆዩ በኋላ ጃንዋሪ 1 ቀን 1901 በዋዜማው የአዳር ጸሎት ጉባኤ ሲያደርጉ አንዲት አግነስ ኦዝማን የተባለች የ30 ዓመት ሴት እነርሱ «ልሳን» ነው ብለው ያመኑትን ነገር ከአፍዋ አወጣች። ይሁንና ቀደም ሲል አጥብቀው በሚያምኑት መሠረት ወንጌል ሊሰብኩበት አልቻሉም ነበር፤ ለራሳቸው ማኅበርም ሊተረጐም አልቻለም። ከዚያ በኋላም ባሉት ጥቂት ቀናት ራሱ ፓርሃምን ጨምሮ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች እነርሱ «ልሳን» ያሉትን ነገር እንደተለማመዱ ይተረካል።
በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩት የሐሰት ትምህርቶችና የሐሰት አሠራሮች የሚከተሉት ናቸው።
- 1. በልሳኖች መናገር የመንፈስ ቅዱስ መገለጫ ስለሆነ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበሉ የሚታወቀው በልሳን ሲናገር ነው የሚለው የፓርሃም አስተሳሰብ የስህተት ትምህርት ነው። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ራሱን የሚገልጥባቸው የጸጋ ስጦታዎች ልዩ ልዩ ሲሆኑ በልሳን መናገር ከእነዚህ መካከል አንዱና የመጨረሻው ነው እንጂ ብቸኛው ስላልነበረ ነው (1ቆሮ.12፡4-11፣ 28-31)።
- 2. በጸሎት ጉባኤያቸው ላይ እነርሱ ልሳን ያሉትን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገረች የተባለችው ሴት መሆንዋ የስህተት አሠራር ነበር፤ ይህም ከሞንታነስ ጀምሮ በተመለከትናቸው ተመሳሳይ የሐሰት አሠራሮች ሁሉ ሲታይ የነበረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በልሳኖች ስለመናገር በስፋት በሚናገርበት በ1ቆሮ14 ውስጥ «ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ»1ቆሮ14፡34) ስለሚል አሠራሩ ቃሉን የጣሰ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሴቶችን በማኅበር ሊያናግር የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ራሱ ካስጻፈው ቃል ጋር በተቃራኒ አይሠራምና።
- 3. ፓርሃም የዓለም መጨረሻ በ1925 ይሆናል ብሎ የተናገረው ትንቢት የሐሰት ትንቢት ነበር። ራሱ ፓርሃም የሞተው ከ1925 በኋላ አራት ዓመት ቆይቶ በ1929 በመሆኑ እርሱ በተናገረው ትንቢት መሠረት ዓለም አለማለፏን ማረጋገጥ ችሏል። በመሆኑም በዚህ የሐሰት ትንቢት ላይ ተመሥርተው ሲጠባበቁት ወደ እነርሱ የመጣው መንፈስ ቅዱስ እንደማይሆን እርግጥ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ተነገረ የተባለውም «ልሳን» የሐሰት ልሳን መሆኑ በጣም ግልጽ ነው።
ቻርለስ ፎክስ ፓርሃም የቶፔካውነ ት/ቤቱን የዘጋው ወዲያውኑ ሲሆን ከዚያ በኋላ ወደ ቴክሳስ ግዛት በመሄድ በሀውስተን ከተማ በ1905 አንድ ሌላ የቲዎሎጂ ት/ቤት ከፍቶ ነበር። በዚያን ጊዜ በነጭና በጥቁር አሜሪካውያን መካከል ከነበረው የዘር ልዩነት የተነሳ በፓርሃም ራሱ ይህን የዘር ልዩነት ከሚያደርጉ መካከል አንዱ ስለነበር ወደ እርሱ ት/ቤት ሊማር መጥቶ የነበረውን አንድ ዊሊያም ጆሴፍ ሲሞር የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ ከነጮቹ ጋር ሳይቀላቀል ከክፍል ውጭ ሆኖ በበርና በመስኮት የሚወጣውን ድምፅ እየሰማ እንዲማር አድርጐት ነበር። እንዲያውም ፓርሃም በ1910 ኩ ክሉክስ ክላን (Ku Klux Klan(KKK)) በመባል የሚታወቅ ለነጮች የበላይነት የቆመና በጥቁሮች ላይ የዘር መድልዎ የሚያደርግ ቡድን አባል እንደሆነ ታውቋል። በተጨማሪም ይህ ሰው በ1907 ከሁለት ሕጻናት ወንዶች ጋር ግብረ ሰዶም ፈጽሟል በሚል ታስሮ ስለነበር ከዚያ በኋላ በተከታዮቹ ዘንድ ተቀባይነትን አጥቷል።
ከፓርሃም በመቀጠል ሐሰተኛ ልሳኖችንና ስሜታዊነትን (emotionalism) በክርስትናው ዓለም በማስፋፋት የሚታወቀው ዊሊያም ጆሴፍ ሲሞር (William Joseph Seymour((1870-1922) ነው። ይህ ሰው በቴክሳስ ውስጥ ሉሲ ፋሮው (Lucy Farrow) በተባለች ሴት «ፓስተርነት» በሚመራ አንድ የክርስትና እምነት ድርጅት ውስጥ አባል የነበረ ነው። በቴክሳስ ሀውስተን በነበረው የፓርሃም ት/ቤት እንዲማር የመከረችውም እርስዋ ናት፤ በዚያ ት/ቤት የሚሰጡትን የስህተት ትምህርቶች ከተማረ በኋላም በ1906 ጁሊያ ሁቺንስ (Julia Huchins) የተባለች አንዲት የሴት «ፓስተር» ጥሪ ተደርጎላት በካሊፎርኒያ ግዛት ወደምትገኘው ወደ ሎሳንጀለስ ከተማ በመሄድ አብሮአት መሥራት ጀምሮ ነበረ፤ ሆኖም በኋላ ላይ ከእርስዋ ጋር ባለመስማማት ስለተለያዩ ከእርስዋ ተገንጥሎ 214 ቦኒ ብራይ (214 Bonnie Bray Street) በተባለ መንገድ ላይ በሚገኝ ሪቻርድ አስቤሪ (Richard Asberry) በተባለ ሰው ቤት የሐሰት ልሳኖችን ማለማመድና ይህንኑ የተመለከቱ የስህተት ትምህርቶቹን ማስተማር ጀመረ፤ ከዚያም ይህንን አዲስ የሆነ ነገር ለማየትና ለመስማት ከየስፍራው ሰዎች ሲመጡ ቤቱ ሊበቃቸው ባለመቻሉ 312 አዙሳ ጎዳና በተባለ ስፍራ በሚገኝ በአንድ መጋዘን ውስጥ
ብዙዎች የሳቱበትን ይህን የሐሰት ትምህርትና አሠራር ማስፋፋት ቀጠለ።
ሲሞር ከ1906 ጀምሮ በዚህ ዓይነት ከፓርሃም በባሰ ሁኔታ የሐሰት ልሳኖችን ያስፋፋ ሰው ነበር። በተለይ ከአሜሪካ ተነስቶ ወደሌሎች የአለም ክፍሎች ይልቁንም ወደ አፍሪካና ወደ ሕንድ የሐሰት ልሳኖች እንዲስፋፉ በማድረግ የሚታወቅ ሰው ነው። ይኸው የስህተት አሠራር ወደ ኢትዮጵያም የገባው ከዚያው ከአዙሳ ጎዳና ሲሆን ከአዙሳ ተነስቶ አዋሳ ለመድረስ 57 ዓመት እንደፈጀበት ተመዝግቧል።
በአዙሳ ጎዳና ይካሄዱ የነበሩት ስብሰባዎች ከልክ ያለፈ ስሜታዊነት ጩኸትና መወራጨት፣ ጭፈራና ዳንስ የበዛባቸው ነበሩ፤ በዚህ የተነሳ ጠንቋዮች፣ መናፍስት ጠሪዎችና ሙታን ሳቢዎች በስብሰባዎቹ ውስጥ ይገኙ እንደነበረ ተመዝግቧል። ስለሆነም በዘመናችን ባሉ ተመሳሳይ ስብሰባዎች እንደምናየው ሁሉ በዚያ እንቅስቃሴ ውስጥም በመንፈስ ቅዱስ ስም የራሳቸውን ዓላማ ያስፈጽሙ የነበሩት ርኩሳን መናፍስት እንደነበሩ እንገነዘባለን።
በ1ቆሮ.14፡34 ላይ «ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ» ለሚለውና በ1ጢሞ.2፡11 ላይ «ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም» ለሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ የማይታዘዙት በፓርሃምም ሆነ በሲሞር ተጀምረው በየስፍራው እየተስፋፉ የሄዱት እንቅስቃሴዎች በስብሰባዎቻቸው ውስጥ ሴቶች እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ በማድረግ ይታወቃሉ። ከዚህ አኳያም በዚያው በአሜሪካ ከተነሱት መካከል ካትሪን ጆሃና ኩልማን (Kathryn Johanna Kuhlman) (1907-1976) የተባለችው ሴት ተጠቃሽ ናት። ይህች ሴት ቀደም ሲል በአንድ የሜቶዲስት እምነት ድርጅት አባል የነበረች ስትሆን በኋላ ደግሞ በአዙሳ ጎዳናው እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ሥር ተዘፍቃለች። ራስዋን የወንጌል ሰባኪና የፈውስ ስጦታ ባለቤት በማድረግ ብዙዎችን አስታለች። ተከታዮቿንም በልሳኖች መናገርን በእጅጉ እንዲፈልጉ በማበረታታት አሁን የሚሰሙትን የሐሰት ልሳኖች ታስፋፋ እንደነበር ታሪኳ ያስረዳል። እንደዚሁም በሼከሮች የተጀመሩትን «በመንፈስ መሳቅ» እና «በመንፈስ መታረድ» የሚባሉትን የስህተት ትምህርቶችና የስህተት አሠራሮችን ታስፋፋ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ካትሪን ኩልማን በተለይ በ1935 በዴንቨር ውስጥ የዴንቨር የተሐድሶ ድንኳን (Denver Revival Tabernacle) በሚል ስያሜ ሚልድሬድ (Mildred)፣ እና ሉሲሌ (Lucille) ፣ እና ቢኔይ አንደርሰን (Biney Anderson) ከተባሉ ሙዚቃ ከሚጫወቱላት ሦስት ሴቶች ጋር በጀመረችው እንቅስቃሴ ትታወቃለች። ከሌሎች ስፍራዎች ሰባኪዎችን እየጋበዘች ታሰብክ ስለነበር በ1937 ቡራውስ ኤ.ዋልትሪፕ (Burroughs A.Waltrip) የተባለ ሰባኪ በአዮዋ ውስጥ ካለችው ከማሶን ከተማ ጠርታው እንዲሰብክ አደረገችው። በዚህ የተነሳ በፈጠሩት መቀራረብም ዋልትሪፕ ከእርስዋ ጋር ለመኖር ሚስቱንና ልጆቹን ተወ። እርስዋን ለማግባት ብሎ ሚስቱን በይፋ ከፈታ በኋላ በ1938 አግብታዋለች። ይህም የሌላይቱን ባል መውሰድ በመሆኑ ግልጽ የሆነ አመንዝራነት ነበር፤ በ1944 ደግሞ እርሱንም ተወችው። በዚህም ሥራዋ በተከታዮችዋ ዘንድ የነበራትን ተቀባይነት አጣች፤ የአገልግሎትዋም ሐሰተኝነት ተረጋገጠ። በዘመናችን የምንሰማቸው የሐሰት ልሳኖች ቀደም ሲል ኩዌከርስና ሰከርስ በተባሉት ቡድኖች እንዳየነው ሁሉ የክርስትናን ስም ይዘው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት የማያምኑ ሰዎችም መገለጫ ሆነው እናያለን። በአሜሪካ ውስጥ በፓርሃምና በሲሞር የተጀመረው እነርሱ «ጰንጠቆስጤአዊ» የሚሉት እንቅስቃሴ ከ1913 በኋላ በትምህርትና በአስተዳደር ባለመስማማት የተከፋፈለ ሲሆን በዚያን ጊዜ ከተከፋፈሉት መካከል አንዱ የነበረው ዩናይትድ ፔንተኮስታል ቸርች (United Pentecostal church) የሚባለው የእምነት ድርጅት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት የማያምን ከመሆኑም ሌላ አብም ወልድም መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስ ነው የሚል የሐሰት ትምህርትን የሚከተል ድርጅት ነው። እንደዚሁም ክርስቶስ ሥጋ ከመልበሱ በፊት የነበረውን ህልውና የሚክድና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውኃ መጠመቅ ለመዳን አስፈላጊ ነው የሚል የእምነት ክፍል ነው። በዚህ የእምነት እንቅስቃሴ ውስጥ በልሳን መናገር የመዳን ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል።
የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች ከነበሩት መካከል ዊሊያም ማሪዮም ብራንሃም (Wiliam Marrion Branham) (1909-1965) የተባለው ሰው በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ሰው ራሱን በዚህ በመጨረሻው ዘመን ያለችው ማለት የሎዶቅያ ዘመን ቤተክርስቲያን መልአክ አድርጎ ይቁጥራል። ይህም ብቻ ሳይሆን ይመጣል የተባለው ነቢዩ ኤልያስ እርሱ እንደሆነ ይናገር የነበረ ሰው ነው። እንደዚሁም በራእ.20 ላይ የተጠቀሰው የሺህ ዓመት ጊዜ (Millenium) በ1977 ይጀምራል ብሎ ሐሰተኛ ትንቢት ተናግሮ የነበረ ሰው ነው ፤ ከዚህም ሌላ እጅግ ብዙ ክፉ ትምህርቶች ያሉት ሲሆን በልሳን መናገር የመዳን ምልክት ነው በማለት ሐሰተኛ ልሳኖችን ያስፋፉ ነበር። ይህም ሆነ ጠቅላላ እነዊሊያም ብራንሃም ያስፋፉት የዩናይትድ ፔንቴኮስታል ቸርች ክፉ ትምህርቶች በሙሉ በተለምዶ ብዙውን ጊዜ ኦንሊ ጂሰስ (Only Jesus) ተብሎ በሚታወቀው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታመኑና የሚነገሩ ናቸው።
እንግዲህ በዘመናችን «ልሳን» እየተባለ በየስፍራው በስሜት ተዘፍቀው ከሚንዘፈዘፉ ሰዎች ሲወጣ የሚሰማው ትርጉም የለሽ ድምፅ (Babling) በዚህ ሁሉ የአጋንንት ትምህርት የተለወሰ ነው። በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት እናምናለን እያሉ የልሳን ባለቤቶች ነን የሚሉት ሰዎችም ቢሆኑ ልሳን ብለው ከአፋቸው የሚያወጡትን ስንሰማው ያው «በኦንሊ ጂሰስ» ተከታዮች፣ በሞርሞኖችና በሌሎችም ሐሰተኛ አሠራሮች የሚባለው የከንፈርና የምላስ መንቀጥቀጥ በድንገት የሚፈጥራቸው ትርጉም የለሽ የፊደላት ቅጥልጥል (Babling) ነው እንጂ ልሳን(ቋንቋ) አይደለም። ይህም ከስሜት ወይም ከአጋንንት ነው እንጂ ከእግዚአብሔር አይደለም።
በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ሲነገር የነበረውን ልሳን በተመለከተ ግን ቀደም ሲል በ1ቆሮ.13፡8 ጥናታችን በስፋት እንደተመለከትነው እንደሌሎቹ ተአምራዊ ስጦታዎች ሁሉ በልሳን የመናገር ስጦታም የተሰጠበትን ዓላማ ከፈጸመ በኋላ ቀርቷል። ይህን በተመለከተ በኋላ በቁስጥንጥንያ የነበረው የአንጾኪያው ጆን ክሪሶስተም (ዮሐንስ አፈወርቅ(347-407)) 1ቆሮ.12ን ባብራራበት ክፍል ስለልሳኖች ሲናገር «ልሳኖች.... አልቀጠሉም» ብሏል (John Chrysostom, Homilies on First Corinthians, 29, NPNF, 1st ser., XII, 168.)፤ እንደዚሁም የሂፖው አውግስታይን (354-430) የሐ.ሥ.2፡4ን ሲተረጐም «በመጀመሪያው ጊዜያት መንፈስ ቅዱስ ባመኑት ላይ ወረደ፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስ እንደሰጣቸው አስቀድሞ በማያውቋቸው ልሳኖች ተናገሩ፤ እነዚህም ለዚያው ጊዜ የተሰጡ ምልክቶች ነበሩ፤ .. ያ ነገር የተደረገው ለምልክት ነበረ፤ እናም አለፈ።» ብሏል። (Augustine, "Ten Homilies on the First Epistle of John," Philip Schaff, ea., The Nicene and PostNicene Fathers of the Christian Church, Vol. 7 (Grand Rapids: Eerdmans, 1956), 497)
ስለሆነም ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ በአዲስ ኪዳን የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ከጸና በኋላ እንደሌሎቹ ምልክቶች ሁሉ በልሳኖች መናገርንም እግዚአብሔር ራሱ እንዳስቀረው የታወቀ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ካስቀረው በኋላ ሰዎች በብርቱ ሲፈልጉት በዘመናችን እንደሚታየው ላለ ሐሰተኛ ልሳን ስለሚጋለጡ ራስን ከዚህ አሠራር መጠበቅ ይገባል እንላለን።
ማጠቃለያ
እንግዲህ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ በልሳኖች መናገርን በተመለከተ የሚያሳየውን እውነታ ልብ ብለው መመልከት ይገባቸዋል። የሐዋ.ሥ.2 እና 1ቆሮ.12-14 ያለውን ስናጠና በሰፊው እንደተመለከትነው በልሳኖች መናገር ማለት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በምድር ላይ ካሉትና ሰዎች ከሚናገሩባቸው ቋንቋዎች በአንዱ ቋንቋ መናገር ማለት ነው እንጂ በዘመናችን እንደሚሰማው አእምሮን በመሳት ወይም ሆን ብሎ በአፍ ላይ የሚመጡ ፊደላትን እያገጣጠሙ ትርጉም የለሽ ድምፆችን ማውጣት አለመሆኑን በጥብቅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም ብዙ የጌታ ልጆችን ከሐሰት ልሳኖች ግርዶሽ ነጻ ያወጣቸዋል ተብሎ ይታሰባል።
እንደዚሁም የዘመናችን ሐሰተኛ ልሳኖች የእግዚአብሔርን ቃል ድንጋጌዎች ፈጽሞ ሊከተል እንደማይችሉ ማስተዋል ይገባል፤ ስለሆነም ቀደም ሲል 1ቆሮ.14፡27-28ን ስናጠና ከተመለከትናቸው የአጠቃቀም ድንጋጌዎች ጋር ሲነጻጸሩ በተቃራኒው የሚተገበሩ መሆናቸውን በማየት ሐሰተኝነታቸውና መለየትና በፍጥነት ከእነርሱ እስራት መፈታት ያስፈልጋል።
ሐሰተኛ ልሳኖች አመጣጣቸው በሐሰተኞች ነቢያትና በሐሰተኞች አስተማሪዎች አማካኝነት መሆኑን በመገንዘብም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እስከ አሁን ድረስ በሐሰት ልሳኖች የተታለሉ ንስሐ እየገቡ ወደ እውነት ሊመለሱ ይገባል።