የአዲስ ኪዳን አምልኮ

የአዲስ ኪዳን አምልኮ

መግቢያ

እግዚአብሔር ለዓመታት በግብፅ ባርነት ሥር የነበሩትን ሕዝቡን እስራኤልን ከፈርዖን አገዛዝ ነጻ ሲያወጣ ዓላማው እርሱን እንዲያመልኩት ለማድረግ ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር ፈርዖንን «ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ» ለማለት ተገብቶታል (ዘጸ.8፡11)። እነርሱም በግብፅ ከታዘዘው የእግዚአብሔር ፍርድ በበጉ ደም ከዳኑ በኋላ ከዚያ ወጥተው በምድረ በዳ እግዚአብሔርን አመለኩ። እንደዚሁም ክርስቲያኖች በክርስቶስ ደም የተዋጁት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ነው (ዕብ.9፡14)። በአዲስ ኪዳን በጌታ በኢየሱሰ ቤዛነት ከኃጢአትና ከሞት ከዲያብሎስም ባርነት ነጻ የወጡ አማኞች የመዳናቸውና ዳግም የመወለዳቸው ዋና ዓላማ “አምልኮ” ነው፤ የሚያመልኩትም መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔርን ነው።

አምልኮ ሲባል «መገዛት» ማለት ሲሆን ቃሉ ለአማኞች ሲነገር ለሕያው አምላክ በሁለንተናችን ያለንን መገዛት ይገልጣል። ይህም በኑሮአችን ሁሉ እርሱን በመፍራትና ለእርሱ በመታዘዝ፣ ከክፋትም ሁሉ ርቀን በመኖር ሊገለጥ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ እንዳለ ሆኖ እግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ዓለም ለእርሱ የተለዩት አማኞች ተሰብስበው በጉባኤ እንዲያመልኩት ይፈልጋል።

በጉባኤ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮን በተመለከተ በየዘመናቱ ከእግዚአብሔር የተሰጡ መርሆዎች የተለያዩ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል። በክርስትናው ዓለም የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት የተከተለ አምልኮ ለዘመናት ሲቀርብ ለመኖሩ ዋናው ምክንያት ይህንን አለማወቅ ነው። የብሉይ ኪዳን አምልኮ ቋሚ ሥርዓት፣ ቊሳዊ የመገልገያ ዕቃዎች፣ የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ፣ ምድራውያን ካህናት እና የእንስሳት መሥዋዕት የነበረው ፊደላዊ አምልኮ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ወደዚህ ዓለም መጥቶ ስለሚመጣው ሌላ አዲስ የአምልኮ ጊዜ ሲያስተምር “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” የሚል ግልጽ የአምልኮ መመሪያን ሰጠ (ዮሐ4፡24)። ስለአዲስ ኪዳን አምልኮ የተጻፈው ይህ ጽሑፍም ይህን የጌታ ቃል መሠረት ያደረገ ነው።

ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ

(ማቴ.4፡10፤ ሉቃ.4፡8)

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ስለ አምልኮ ያለው ቀዳሚ እውነት «አምልኮ የሚገባው እውነተኛው አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው» የሚል ነው። ዛሬ በአገራችን ውስጥ የእውነተኛውን አምላክ የእግዚአብሔርን ህልውና የሚያውቁና ራሳቸውንም ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ነገር ግን የጥንቆላ እና የመሳሰሉትን ባዕድ አምልኮዎች አዳብለው የያዙ ብዙ ወገኖች ይኖራሉ፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ እነዚህን አምልኮዎች ከአምልኮተ እግዚአብሔር ጋር ጐን ለጐን ይዞ መኖር እግዚአብሔርን የሚያሳዝነውና የሚያስቆጣው እንደሆነ እንኳ አያውቁም፤ እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም እና እነርሱ ቅዱሳን በሚሏቸው ፍጡራን ስም የሥዕልና የቅርፅ ምስሎችን በማበጀት ለእነርሱ መስገድና ወደ እነርሱ መጸለይ እግዚአብሔርን የሚያስቀና ባዕድ አምልኮ መሆኑን ብዙዎች ገና አልተረዱም።

በዓለማችን ውስጥ በተለይም በአሕዛብ ዘንድ አማልክት የሚባሉት በቊጥር ብዙ ናቸው። አንድ ሰው ብዙ አማልክትን ሊያመልክ ይችላል። ለምሳሌ ጎልያድ ዳዊትን እንደረገመው በተጻፈበት ክፍል «ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ስም ረገመው» የሚል ስናነብ (1ሳሙ.17፡43) ኤልዛቤል በኤልያስ ላይ ያቀረበችውን ዛቻ በተመለከተ ደግሞ «...አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ» እንዳለች እናነባለን (1ነገሥ.19፡2)፤ ይህም ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው የተለያየ አማልክትን ከመፈለግ የመጣ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክርለት አንድ አምላክ ግን በሁሉ ስፍራ የሚገኝና ሁሉን መሥራት የሚችል ለማንኛውም የሰው ልጅ ጉዳይ የራሱ የሆነ በቂ ምላሽ ያለው አምላክ ነው፤ ይህንን በሚመለከት «መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፣ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ከእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን» የሚል ቃል እናነባለን(1ቆሮ.8፡5-6)። እንደዚሁም በሌላ ስፍራ ላይ «ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር፣ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ» የሚል ቃልን እናነባለን(ኤፌ.4፡5)። በእነዚህ በሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ «ነገር ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆንን»፣ «ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር» የሚሉት እነዚህ ቅጽሎች ለአንድ ሕያው አምላክ ካልሆነ በቀር ለማንም ሊነገሩ የሚችሉ አይደሉም። ሌሎች አማልክት የሚባሉት ሁሉ እንዲህ ያለ ብቃት የላቸውም።

ሰይጣን በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በስም ክርስቲያኖች በሚባሉ ወገኖች መካከል የሌሎች አማልክትን አምልኮ በማስገባት ብዙዎችን ተቈጣጥሮአል፤ ሆኖም በተለያዩ አማልክት ስም ይገለጥ እንጂ በሁሉም ዘንድ ባዕድ አምልኮን የሚቀበለው «የዚህ ዓለም አምላክ» የተባለው ራሱ ሰይጣን ነው(2ቆሮ.4፡4)። ሰይጣን ብዙዎችን ወደዚህ ባዕድ አምልኮ የሚስበው በዓለማዊ ክብርና ጥቅም ነው። ብዙዎች ሥራ ለመያዝ፣ ንግድን ትርፋማ ለማድረግ፣ ትዳርን ለማሳካት፣ «ጠላቴ ነው» የሚሉትን ለመበቀልና ለማጥፋት፣ ከበሽታ ለመዳን፣ የወደፊት ዕድልን ለመወሰን፣ ... ወዘተ ግልጽና ስውር የሆኑ ባዕዳን አማልክትን ያመልካሉ። ሰይጣን በዚህ መልኩ ዐይንን ሊማርኩ የሚችሉ የዚህ ዓለምን ነገሮች እያሳየ ለመመለክ ጥረት ሲያደርግ ጌታ ኢየሱስ የመለሰለትን ቁርጠኛ መልስ መስጠት ይገባል። ጌታችን በምድረበዳ በሰይጣን በተፈተነ ጊዜ ሰይጣን ወደ ረጅም ተራራ ወስዶ «የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ» ብሎ ላቀረበለት ፈተና የሰጠው መልስ «ሂድ አንተ ሰይጣን፣ ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና» የሚል ነበር(ማቴ.4፡8-11፤ ሉቃ.4፡8)፤ እኛም በዚሁ ዓይነት «...እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና» በማለት ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀስን የሰይጣንን ሽንገላ በጥብቅ ልንቃወም እንደሚገባን ከዚህ እንረዳለን። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ያሉት ቅዱሳት መጻሕፍት ከአንድ አምላክ ከእግዚአብሔር በቀር ሌሎች አማልክትን እንዳናመልክ በግልጽ ይነግሩናል፤ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ጥቅሶች መካከል ከ10ሩ ቃላት የመጀመሪያው የሆነውን ቃል ብንመለከት «እግዚአብሔር ይህን ቃል እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ» ይላል (ዘጸ.20፡1-3፤ ዘዳ.5፡6-7)። እንደዚሁም በአዲስ ኪዳን ክፍል «... ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን» ይላል(1ቆሮ.8፡4)። በዚህ መልክ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ «ተብሎ ተጽፎአልና» ብለን ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ባዕድ አምልኮን የሚቃወሙ ግልጽ ቃላት በብዛት ይገኛሉ፤ ለእግዚአብሔር ቃል ከልብ የሚገዛ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን አምልኮ በሙሉም ሆነ በግማሽ ለፍጡራን ወይም ለተቀረፁ ምስሎች ሊሰጥ አይችልም።

በዓለማችን ውስጥ በተለይም በአሕዛብ ዘንድ አማልክት የሚባሉት በቊጥር ብዙ ናቸው። አንድ ሰው ብዙ አማልክትን ሊያመልክ ይችላል። ለምሳሌ ጎልያድ ዳዊትን እንደረገመው በተጻፈበት ክፍል «ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ስም ረገመው» የሚል ስናነብ (1ሳሙ.17፡43) ኤልዛቤል በኤልያስ ላይ ያቀረበችውን ዛቻ በተመለከተ ደግሞ «...አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ» እንዳለች እናነባለን (1ነገሥ.19፡2)፤ ይህም ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው የተለያየ አማልክትን ከመፈለግ የመጣ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክርለት አንድ አምላክ ግን በሁሉ ስፍራ የሚገኝና ሁሉን መሥራት የሚችል ለማንኛውም የሰው ልጅ ጉዳይ የራሱ የሆነ በቂ ምላሽ ያለው አምላክ ነው፤ ይህንን በሚመለከት «መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፣ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ከእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን» የሚል ቃል እናነባለን(1ቆሮ.8፡5-6)። እንደዚሁም በሌላ ስፍራ ላይ «ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር፣ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ» የሚል ቃልን እናነባለን(ኤፌ.4፡5)። በእነዚህ በሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ «ነገር ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆንን»፣ «ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር» የሚሉት እነዚህ ቅጽሎች ለአንድ ሕያው አምላክ ካልሆነ በቀር ለማንም ሊነገሩ የሚችሉ አይደሉም። ሌሎች አማልክት የሚባሉት ሁሉ እንዲህ ያለ ብቃት የላቸውም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አማልክት እየተባሉ የሚጠሩት የአሕዛብ አማልክት ብቻ ሳይሆኑ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው ቅዱሳን ፈራጆችም ናቸው፤ በመዝሙረ ዳዊት «እኔ ግን አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ» ተብሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ «አማልክት» የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እንደሚያመለክት ጌታ ኢየሱስ ተናግሯል (መዝ.82፡6፤ ዮሐ.10፡34-36)። ለምሳሌ እግዚአብሔር ሙሴን «እይ፡- እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል» እንዳለው እናነባለን (ዘጸ.7፡1)። ከዚህ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ቃሉን የሚሰጣቸው ባሪያዎቹን በክፉ ነገር ላይ (ለምሳሌ በፈርዖን ላይ) አምላክ አድርጎ እየሾመ በአምላካዊ ሥልጣን ይልካል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር እርሱን የሚያመልከውን ሕዝብ ለእነዚህ በአምላካዊ ሥልጣን ለተላኩት የእግዚአብሔር ባሪያዎች እንዲሰግድና ወደ እነርሱም እንዲጸልይ እንዲሁም የገንዘብ፣ የጧፍና የዕጣን መሥዋዕት ከመዝሙር ጋር በማቅረብ እንዲያመልካቸው አላደረገም፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን ሙሴን በሕይወት እያለም ሆነ ከሞተ በኋላ በስግደት እና በጸሎት በመዝሙርም አያመልኩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም የሙሴን መቃብር እንዳይታወቅ ያደረገውስ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል?(ዘዳ34፡6፤ ይሁ9)።

በእስራኤል ምድር እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር ሳይጀመር በነገደ ኲሽ አማካኝነት በምድራችን የሚታወቅ አምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበር በሚተርኩ ሰዎች ዘንድ በዚህችው ምድር ቀደም ባለው ዘመን ዘንዶ ይመለክ እንደነበር የሚነገረው ታሪክ ሲያስከፋቸው ይታያል፤ ታሪክ ደግሞ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የጨረቃና የፀሐይ አምልኮ፣ እንደዚሁም «ማሕረም» የተሰኘ ጣዖት እንደነበረ ታውቋል። አምልኮተ እግዚአብሔር በአሕዛብ አገሮች በማይታወቅበት በዚያን ጊዜ ቀርቶ አሁን እንኳ ብዙ ወገኖቻችን ለዛፍና፣ ለወንዝ፣ ለጠንቋይና ለጨሌ እየሠዉ፣ እየገበሩና እየሰገዱ ምን ያህል በባዕድ አምልኮ ውሰጥ እንዳሉ ይታያል፤ ነገር ግን ይህን የተገለጠ እውነት ማመን የማይፈልጉና ቢቻላቸው ይህንኑ የረከሰ አምልኮ የተቀደሰ የሚመስል ታሪክ ሊያበጁለት የሚጥሩ መኖራቸው አሳዛኝ ነው፤ እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ብርሃኑን ብርሃን ጨለማውን ጨለማ፣ እውነቱን እውነት ስህተቱን ስህተት፣ ቅዱሱን ቅዱስ ርኵሱን ርኵስ ማለትን የማያውቅ በመሆኑ በምድራችን ላይ ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩት ሁሉ በብዙዎች ወገኖቻችን እየተመለኩ የመሆኑን እውነታንም ለመካድ አይቸገርም። ይልቊንም ለእነዚህ ፍጡራን የሚቀርበው የስግደትና የዕጣን፣ የጸሎትና የመዝሙር አምልኮ እንዳይፈራርስበት የመከላከያ ትምህርት በማቅረብ ምክንያታዊ መንፈሳዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊም ለማስመሰል ይሞክራል። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለእግዚአብሔር ባሪያዎች ስግደት ላቀረቡ ሰዎች የተሰጠው ማስጠንቀቂያ በግልጥ ስለተጻፈ ማስመሰላቸው ከንቱ ይሆናል። ቆርኔሌዎስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ከእግሩ በታች ወድቆ በሰገደለት ጊዜ ጴጥሮስ «ተነሣ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ» ብሎ እንዳነሣው ተጽፏል (የሐ.ሥ.10፡26)፤ ዮሐንስ ራእዩን ባሳየው መልአክ ፊት ይሰግድ ዘንድ ሲደፋ መልአኩ «እንዳታደርገው ተጠንቀቅ... ለእግዚአብሔር ስገድ» እንዳለው ተመዝግቧል (ራእ.22፡8-9)።

በመሆኑም የፍጡራን አምልኮን ትተው እግዚአብሔርን ብቻውን ለማምለክ ያልቻሉ የዋሃን እናቶችና አባቶች እንዲሁም ወጣት ወንድሞችና እኅቶች «እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ፤ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ ወደ እናንተም ይቀርባል» በሚለው ቃል መሠረት ለእግዚአብሔር ብቻ ሊገዙና ዲያብሎስም ከፈጠራቸው አምልኮዎች ሊለዩ ይገባቸዋል (ያዕ.4፡7-8)። ረዘም ላለ ጊዜ ግልጽና ስውር በሆነ የባዕድ አምልኮ ባርነት ውስጥ እያወቁም ይሁን ባለማወቅ ተይዘው የኖሩ ሰዎች የእውነት ወንጌል በርቶላቸው የእውነተኛውንና የብቸኛውን አምላክ ማንነት ባወቁ ጊዜ እስከዚያን ጊዜ ማስተዋላቸውን የጋረደውንና በተለያዩ መንፈሳዊ እና ባህላዊ በሚመስሉ አስተሳሰቦች ያታለላቸውን የነፍሳቸውን ጠላት «ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፏል» በማለት ሊቃወሙት ያስፈልጋል። በዚህ መልክም በእምነት ቢቃወሙት ወዲያውኑ ከእነርሱ ይሸሻል። እነርሱም ሕያው ለሆነው ለአንድ አምላክ ብቻ በምስጋናና በውዳሴ፣ በመዝሙርና በጸሎት ለቃሉም በመገዛት በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አምልኮን እያቀረቡ ሊኖሩ ይገባቸዋል።

እውነተኛው የአምልኮ ስፍራ

«ኢየሱስም እንዲህ አላት አንቺ ሴት እመኚኝ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል» (ዮሐ.4፡21)።

ይህን ቃል ለአንዲት የሰማርያ ሴት በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ የነገራት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፤ ታሪኩ የሚጀምረው «ውኃ አጠጪኝ» በሚል የልመና ቃል ነው፤ ምን አልባትም ይህ ገጠመኝ ለሴቲቱ የመጀመሪያዋ ሳይሆን አይቀርም፤ በባህል፣ በታሪክና በሃይማኖት የማይመስላት አንድ ከአይሁድ ወገን የሆነ እጅግ በጣም ትሁት ሰው ውኃ አጠጪኝ ብሎ ሲጠይቃት በጣም እንደተደነቀች ማሰብ ይቻላል። በታሪካቸው አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በምንም ነገር አይተባበሩም ነበርና በእርግጥም ጥያቄው ያስደንቃል፤ የሴቲቱም መልስ «አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?» የሚል ነበር፤ እርግጥ ነው አይሁድ ሳምራውያንን ሲጸየፏቸው ሳምራውያን ግን ለአይሁድ የእነርሱን ያህል ጥላቻ አልነበራቸውም ነበር፤ ለሳምራዊቱ የቀረበውና «ውኃ አጠጪኝ» የሚለው ይህ የጌታ ጥያቄ ግን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስወግድ፣ የአይሁድን ትምክህት ባዶ የሚያደርግ በፍጻሜው ደግሞ የሰማርያ ሰዎችን ከይሁዳ ወገን ከሆነው ከኢየሱስ ጋር እንዲተባበሩና እንዲመሰክሩለትም የሚያደርግ ነበር (ዮሐ.4፡39-42)።

በጌታና በሳምራዊቷ ሴት መካከል የተደረገው ይህ ውይይት ለልብ ታላቅ ጥቅምን ሊያስገኝ ለሚችል አዲስ ሕይወት የሚያዘጋጅ ጸጋን የተሞላ ውይይት ነበር። ጌታ ኢየሱስ ከያዕቆብ ጉድጓድ የሚመነጭን ውኃ ምክንያት ያደረገ ጥያቄ ለሴቲቱ አቅርቦ አንድ ጊዜ ከተጠጣ ለዘላለም የማያስጠማውን፣ ከእርሱ የጠጡትን ሁሉ ደግሞ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ የሚያደርገውን የሕይወት ውኃ እንድትጠይቀው አነሳሳት (ዮሐ4፡15)። በውይይቱ መጨረሻ ላይ ሴቲቱ የራሷን ትታ ከእርሱ ብቻ የሚገኘውን የሕይወት ውኃ በመሻት «ውኃ አጠጪኝ» ብሎ የለመናትን ጌታ መለመን ጀመረች፤ «ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ» አለችው (ቊ.15)፤ የጌታ መልስ ግን ለየት ያለ ነበር፤ «ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ነይ» የሚል። ይህ ደግሞ ለሴቲቱ ሌላው አስደናቂ ነገር ነው። «ይህ ሰው ማነው? የቤቴን ምስጢር አንድም ሳይቀር የሚያውቅ ይህ ማነው?» ብላ እንድታስብና ነቢይ መሆኑን እንድትገምት አስችሏታል ብንል ከእውነታው የተለየ አይደለም፤ ምክንያቱም «አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ» ብላ ስለ እርሱ ማንነት በልቧ የታሰባትን ተናግራለችና፤ እንደዚህ ካለው ሰው ጋር ዋና ዋና በሆኑ አርእስት የእግዚአብሔርን ነገር መወያየት በውስጥ ለተሰወረ የልብ ጥያቄ መልስ ያስገኛል። ከዚህ የተነሣ ይህች ሳምራዊት ሴት ስለ አምልኮ ስፍራ በልቧ ይመላለስ የነበረውን ርእስ «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ እናንተም ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» በማለት አነሳችለት (ቊ.19-20)። ጌታ ኢየሱስም፡- «አንቺ ሴት እመኚኝ፤ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል» አላት(ዮሐ.4፡21)።

በኢየሩሳሌም የነበረው ታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከመሠራቱ በፊትም በእስራኤል ማኅበር መካከል ልዩ በሆነ ትእዛዝ የተሠራው የመገናኛው ድንኳን (ደብተራ ኦሪት) ነበር። በዚህ ድንኳን ውስጥም የተሟላ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ይከናወን ነበር። እግዚአብሔርም በዚያው ድንኳን ውስጥ የሚቀርበውን መሥዋዕት መቀበሉን ለመግለጥ በመገናኛው ድንኳን በዓምደ ደመና በመገለጥ የአምልኮውን መሪዎች ያነጋግራቸው ነበር (ዘጸ40፡34-38፤ ዘሌ1፡1)።

በዚሁ መሠረት እግዚአብሔር ራሱ ለሙሴ የአምልኮውን ዝርዝር ሥርዓት ከሰጠውና አምልኮው የሚከናወንበትን ተንቀሳቃሽ ድንኳን እንዲሠራ ካዘዘው በኋላ አምልኮው በምድረ በዳ ሲከናወን ቆይቷል። እስራኤል ወደሚወርሷት አገር በገቡ ጊዜም አምልኮው ስለሚከናወንበት ስፍራ እግዚአብሔር ሲናገር «በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ሌላ መሥዋዕታችሁንም አሥራታችሁንም በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቊርባን ለእግዚአብሔር ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ውሰዱ» (ዘዳግ.12፡11) ብሏቸዋል። ይህም ስፍራ ከሌሎች ስፍራዎች የሚለየው በእግዚአብሔር በመመረጡና እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ስላኖረ ነው። ያም ስፍራ «ኢየሩሳሌም» እንደነበር በኋላ ዘመን ተገልጦአል (2ዜና.6፡5-6፤ መዝ.132፡13)። ከዚያ ስፍራ ውጪ እስራኤላውያን የተሟላ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የማይፈጽሙ ሲሆን ይህም ለዘመናት ሲከናወን የኖረ የእግዚአብሔር ሥርዓት ነበር።

የሰማርያይቱም ሴት «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» ያለችበት ምክንያትም ይኸው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበር። ጌታ ኢየሱስ ግን ሁኔታው መቀየሩን ለሴቲቱ ያበሰራት «አንቺ ሴት እመኚኝ፤ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል» በማለት ነበር። ይህ ቃል አዲስ የሆነ የአምልኮ ስፍራ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተዘጋጀ በእርግጠኝነት የሚያመለክት ነው።

በዘመናችን ይህን አዲስ የሆነ የአምልኮ ስፍራ ያላወቁ አንዳንድ ወገኖች ይህን የአይሁድና የሳምራውያንን ሃይማኖታዊ ልማድ በግልጽ ሲያከናውኑት እናያለን። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ሊመለክበት ራሱ ወደመረጠው ስፍራ በመሄድ ፈንታ ባማረ ድንጋይ በተገነባ ሕንፃ ወይም ቅዱሳት መካናት ተብለው በሰዎች ወደተሰየሙ አድባራትና ገዳማት በመሄድ ስፍራና ቦታ በሚወስነው የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ገብተው ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሲያባክኑ የሚታዩት ብዙዎች ናቸው። ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ ተራራ ወጥተው፣ ረጅም መንገድ በእግራቸው ተጉዘው፣ ቀናትንና በዓላትን ምክንያት አድርገው ራሳቸው በሠሩት ሥርዓት እግዚአብሔርን ለማምለክ መድከማቸውና ይህንንም ድካማቸውን እንደ ታላቅ ጽድቅ፣ የኃጢአት ሥርየት ማግኛ (ኃጢአትን ማስተስረያ) እንዲሁም የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ አድርገው ሲቆጥሩት ማየቱ ነው። ጌታ ኢየሱስ ለሰማርያይቱ ሴት የነገራትና ከንቱ ከሆነ ከዚህ ድካም የሚገላግል ልብንም የሚያሳርፍ የሕይወት ቃል ዛሬም ለእነዚህ ሰዎች ሊነገራቸው የተገባ ነው፤ ዛሬ እግዚአብሔር የሰው እጅ የሠራውን ስፍራ ለቅቆ ራሱ ወዳዘጋጀው የከበረ ስፍራ እንደሄደም ሊነገራቸው የግድ ነው።

እንግዲያውስ ታዲያ እግዚአብሔር የመረጠው የአምልኮ ስፍራ ወዴት ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያመኑ ክርስቲያኖች ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ሆነው በክርስቶስ ስም በተሰባሰቡበት በማናቸውም ስፍራ ጌታ ይገኛል (ማቴ18፡20)። እግዚአብሔር አምልኮና ለስሙ የሚሆን መሥዋዕት ይቀርብለት ዘንድ በአዲስ ኪዳን ስሙን ሊያኖርበት የመረጠው ስፍራም ይህ ወደ ክርስቶስ ስም የምንሰበሰብበት ጉባኤ ነው። የእግዚአብሔር የመገኘቱም ምስጢር የስፍራው ታሪካዊነት ወይም ክብር ሳይሆን በክርስቶስ ስም ዙሪያ መሰባሰቡ ነው። ይህም መሰባሰብ (ጉባኤ) በጌታ በኢየሱስ ስም እስከሆነ ድረስ የእግዚአብሔር መቅደስ ነው። እግዚአብሔርም በአማኞች መካከል በክብር ይኖራል።

ጌታ ኢየሱስ በሊቀ ካህናትነት በሚያገለግልባት በእውነተኛይቱ ሰማያዊት መቅደስ ሆኖ በመንፈስ በመካከላችን የሚገኝ ሲሆን እኛም ወደ ስሙ በተሰበሰብን ጊዜ እርሱ ባለባት ሰማያዊት መቅደስ እንገባለን ማለት ነው። ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ጌታ የገባባት ሰማያዊት መቅደስ ክርስቲያኖች ሁሉ በግልም ሆነ በማኅበር በሚሰባሰቡበት ጊዜ በልጅነት መንፈስ ሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየታገዙ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ማዕከል ናት (ዕብ.6፡20)። በዚያች ማዕከል መሥዋዕቱም መሠዊያውም ሊቀ ካህናቱም አንድ ብቻ ሲሆን እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምድር ላይ ያሉ አማኞች በሙሉ በጋራ ያላቸው የአምልኮ ማዕከል ያቺው በሰማይ ያለች የእግዚአብሔር መቅደስ ናት። እግዚአብሔር ልጁን ልኮ የተሻለ አምልኮ መፈጸም የምንችልበትን መንገድና የአምልኮ ማዕከል አመለከተን፤ ከእንግዲህ ወዲያ በቦታ ተወስነን ሳይሆን እጅ ባልነካትና ባልተጠበበባት ሰማያዊት መቅደስ በልጅነት መንፈስ እየገባን አብን በነጻነት የምናመልክበት ማዕከል በክርስቶስ ኢየሱስ እንደተዘጋጀልን ይህም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በእርሱ ወደዚያች መቅደስ መግባት እንደ ተጀመረ አውቀናል (ዕብ10፡19)፤ ክብር ለእርሱ ይሁን!

በዘመነ ብሉይ በምድር የተበተኑ አይሁድ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ይሰግዱ እንደ ነበር ሁሉ በዘመነ ሐዲስ ያሉ አማኞችም በሰንበት ወይም በበዓላት ወይም በወር መባቻ ወይም በዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን በፈለጉት ጊዜ ወደ ሰማያዊት መቅደስ በመንፈስ በመግባት ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ፤ በምድር ላይ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተሰብስበው እግዚአብሔር በመካከላቸው በክብር ሲገለጥ እነርሱም በአንድ ልብ በመንፈስ ሆነው በሰማያዊቷ መቅደስ በአብ ፊት በክርስቶስ ክብር ይገለጣሉ። ይህ ደግሞ ለአማኞች የተሰጠ ታላቅ ጸጋ ነው። ይህንንም ተረድቶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ለአብ መስገድ (አብን ማምለክ) ሕይወትና ዕረፍት ነው፤ የክርስቲያኖችም ሁሉ ያልተገደበ መብት ነው።

... ጊዜ ይመጣል

«...በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል» (ዮሐ.4 ቊ.21)።

«...ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኗል» (ቊ.23)።

ሳምራዊቲቱ ሴት «የይሁዳ ሰው» ስትለው የነበረውን ኢየሱስን የተሰወረ ማንነቷን በማወቁ ምክንያት «ጌታ ሆይ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አያለሁ» ካለችው በኋላ በአይሁድና በሳምራውያን መካከል አነጋጋሪ ስለ ነበረው የአምልኮ ስፍራ አንስታለት ነበር። ያነሳችው ርእስ በዚያው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከሕግና ከነቢያት (ከብሉይ ኪዳን) መጻሕፍት አንጻር የአምልኮ ስፍራን በተመለከተ የነበረውን ሁለት አመለካከት ነበር። ሳምራውያን ትክክለኛው የአምልኮ ስፍራ በገሪዛን ተራራ ነው ሲሉ (ዘፍ.12፡7፤ 33፡20፤ ዘዳግ.11፡29፤ 27፡12) አይሁድ ደግሞ በኢየሩሳሌም ነው ብለው ያምኑ ነበር (ዘዳ.12፡5፤ 2ዜና.6፡6፤ 7፡12፤ መዝ.78፡68፤ 132፡13-14)። ሳምራዊቲቱ ሴት ያነሳቻቸው ሁለቱ አመለካከቶች እነዚህ ናቸው፤ ሆኖም ትክክለኛው የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ስፍራ ኢየሩሳሌም ቢሆንም ያንን ሊነግራት አልፈቀደም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ በብሉይ ኪዳን የነበረውን ሥርዓተ አምልኮ የሚሽርበት ወቅት ቀርቦ ስለነበር ኢየሩሳሌምም ብትሆን የአዲስ ኪዳን የአምልኮ ማዕከል ስላልሆነች ሴቲቱን ከገሪዛን ወደ ኢየሩሳሌም እንድትሄድ ማድረጉ አንዳች ጥቅም አይኖረውም ነበር። በመሆኑም ቦታን ወስኖ ምድራዊ የአምልኮ ስፍራን ከማሳወቅ ይልቅ አምልኮተ እግዚአብሔር የማይፈጸምበት ሌላ ጊዜ እንደሚመጣ «አንቺ ሴት እመኚኝ፤ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል» (ቊ.21) በማለት ነገራት። ይህ የጌታችን ንግግር በሰማርያ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ይፈጸም የነበረው አምልኮ የሚያበቃበትና በምትኩም ያለ ተራራና ያለ ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር የሚመለክበት ጊዜ እንደሚመጣ ያረጋግጣል፤ ጌታችን «ይመጣል» ሲል የተናገረለት ይህ ጊዜም ቤተክርስቲያን ከተመሠረተች ጀምሮ ያለው የአዲስ ኪዳን ዘመን ነው። «አንቺ ሴት እመኚኝ» በሚለው የማረጋገጫ ቃል የጸናው ይህ የጌታ ኢየሱስ እውነት በእርግጥም የብሉይ ኪዳን አምልኮ ቀርቶ የአዲስ ኪዳን አምልኮ እንደሚመሠረት በግልጥ ያስረዳል።

ጌታችን ኢየሱስ «ይመጣል» ብሎ በተስፋ የተናገረለት ያ ጊዜ መጥቶ ከምድራዊ ስፍራ ጋር ያልተያያዘውና ሰዎች «በስፍራ ሁሉ» (1ጢሞ.2፡8)፣ «የተቀደሱ እጆቻቸውን እያነሡ» የሚጸልዩበት የአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ብንገኝም በምንኖርበት አለም ውስጥ ግን በብሉይ ኪዳን ተጽዕኖ ሥር የወደቀ አምልኮ ለእግዚአብሔር ሲቀርብ መታየቱ አልቀረም። ከምድራዊ ስፍራ ጋር የተያያዘው አምልኮ ባቆመበት ዘመን ለአምልኮአችን የተቀደሰ ነው የሚባል የተለየ ስፍራን መወሰን ጌታ ኢየሱስ «ይመጣል» ብሎ ወደ ተናገረለት የአዲስ ኪዳን ዘመን አለመድረስ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤ ጌታ ሳምራዊቷ ሴት ከምድራዊ ቦታ ጋር አያይዛ ካቀረበቻቸው አመለካከቶች በመነሣት ከቦታ ጋር የተያያዘ አምልኮ የማይፈጸምበት ጊዜ እንደሚመጣ የተናገረ ቢሆንም ከዚሁ ጋር አያይዞ ለእግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚሰገድበት ጊዜ እንደሚመጣም ተናግሯል። ይኸውም «... ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኗል» ብሎ የተናገረው ቃል ነው (ቊ.23)። ይህም በሁሉም ጠባዩ ከብሉይ ኪዳን የተለየ አምልኮ የሚከናወንበት ዘመን እንደሚመጣ ያሳያል።

«አሁንም ሆኗል» ከሚለው የጌታ ቃል እንደምንረዳው ይመጣል የተባለው የአምልኮ ጊዜ የሚጀምረው ከዚያው ጌታ ኢየሱስ ትምህርቱን ካስተማረበት ዘመን ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ትምህርቱ የተሰጠው ለአንዲት ሳምራዊት ቢሆንም በባሕርዩ ግን የአምልኮ ዘመንን የሚከፍል ለሰው ሁሉ የተሰጠ መለኮታዊ መመሪያ ነው። ኢየሱስ ራሱ አምላክ ስለሆነ ይህን መለኮታዊ መመሪያ ማወጅ ተችሎታል። የአምልኮውን ክፍለ ዘመን በተመለከተ ያስተማረው የመለኮት ሙላት ያለው እርሱ ራሱ ኢየሱስ መሆኑን ማስተዋል ወደ እውነተኛ አምልኮ ይደርሱ ዘንድ የእርሱ የሆኑትን ይረዳቸዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር በአዲሱ የአምልኮ ዘመን ሊመለክ የፈለገበትን መንገድ ከቃሉ መረዳት በእጅጉ ያስፈልጋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረው ፊደላዊ ሥርዓተ አምልኮ በጊዜው ትክክል ነበር፤ አሁን ግን ያ ጊዜ አልፎ እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚመለክበት ሌላ ጊዜ ላይ መሆናችን ሊስተዋል ይገባል።

እግዚአብሔርን በማወቅ ማምለክ

«እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን» (ቊ.22)

በብሉይ ኪዳን ማብቂያ ላይ በአይሁድም ሆነ በሳምራውያን ዘንድ ለእግዚአብሔር ስግደት (አምልኮ) ይቀርብ ነበር። ይሁን እንጂ ከሳምራውያን አምልኮ ይልቅ የአይሁድ አምልኮ ትክክለኛና መሠረት ያለው ነበር፤ የዚህም ምክንያቱ በሳምራውያን አምልኮ ውስጥ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ማወቅ የሌለ ሲሆን በአይሁድ አምልኮ ውስጥ ግን እግዚአብሔርን ማወቅ መኖሩ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ለሰማርያይቱ ሴት ይህንን ሲያስረዳ «እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን» ብሏታል (ቊ.22)። በዚህ ውስጥ ለአምልኮ ቦታ ትኲረት የሰጠው ቃለ ምልልስ እውነተኛ የአምልኮ ባሕርይን ለመግለጥ እንዴት እያደገ እንደመጣ እናያለን፤ ራሱን ከአይሁድ ጋር እኛ ብሎ የገለጠው ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋ አይገባም፤ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ በትክክለኛነቱ ያጸደቀው የአይሁድ አምልኮ ከሰማርያውያን አምልኮ ይልቅ ምን ያህል የከበረ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። የአይሁድ አምልኮ በጊዜው ትክክለኛ በነበረው የአምልኮ ስፍራ ማለትም በኢየሩሳሌም የሚፈጸም ቢሆንም ከሰማርያ ሰዎች አምልኮ የሚለየውና ትክክለኛ እንዲሆን ያደረገው ግን በኢየሩሳሌም መፈጸሙ ሳይሆን የሰማርያ ሰዎች ለማያውቁት አምላክ ሲሰግዱ አይሁድ ደግሞ ለሚያውቁት አምላክ መስገዳቸው ወይም የሚያመልኩትን ለይተው ማወቃቸው ነበር።

  1. እናንተ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ (ዮሐ.4፡23)
    1. በጌታችን ዘመን የነበሩት የሰማርያ ሰዎች የአሦር ንጉሥ በግዛቱ ከሚገኙ አምስት አገሮች አምጥቶ ወደ አሦር ባፈለሳቸው እስራኤላውያን (10ሩ ነገድ) ምትክ ያሰፈራቸው ሰዎች እንደሆኑ በ2ኛነገሥ.17 ውስጥ እናነባለን። እነዚህ ሰዎች በሰማርያ ከተሞች መኖር በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ የአገሩን አምላክ ወግም አያውቁም ነበር፤ እግዚአብሔርም የሚገድሏቸውን አንበሶች ሰደደባቸው፤ በመሆኑም ከዚህ ይድኑ ዘንድ የአገሩን አምላክ ወግ እንዲያስተምራቸው የአሦር ንጉሥ ከምርኮኞቹ እስራኤላውያን መካከል አንድ ካህን ላከላቸው፤ ካህኑም በቤቴል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርን መፍራት ያስተምራቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከተማሩም በኋላ ቢሆን እግዚአብሔርን ይፈሩና ያመልኩ የነበረው ከሌሎች ሰባት አማልክቶቻቸው ጋር አዳብለው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ምንም እንኳ በ2ነገሥ. ምዕ. 17 ቊ.32 ላይ «እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር» ቢባልም በቊ.34 ላይ ደግሞ «እስከዛሬ ድረስ እንደቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርን አይፈሩም» ተብሎ ስለ እነርሱ ተጽፏል። እንዲሁም ከባዕድ አምልኮ ጋር የተቀላቀለውን አምልኮአቸውን በተመለከተ «እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር» ተብሎ ተጽፏል (2ነገሥ.17፡41)። ይህም ሁኔታ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ እስከ ነበረበት ዘመን ድረስ ሳይቀጥል እንዳልቀረ መገመት ይቻላል።በመሆኑም አምልኮአቸው እግዚአብሔርን እና እግዚአብሔር የሚፈልገውን ባለማወቅ የሚከናወን፣ እግዚአብሔር ስለ አምልኮው ቀናተኛ መሆኑንም በማያውቁ ሰዎች የሚፈጸም ስለነበር ጌታ ኢየሱስ «እናንተ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ» ለማለት ችሏል።

      1. እኛ ግን ለምናውቀው እንሰግዳለን

      ሐዋርያው ጳውሎስ «ልጅነትና ክብር፣ ኪዳንም፣ የሕግም መሰጠት፣ የመቅደስም ሥርዓት፣ የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱ ክርስቶስ በሥጋ መጣ» ብሎ እንደጻፈው (ሮሜ9፡4-5) አይሁድ እግዚአብሔር ብዙ ነገር የሰጣቸው ስለሆነ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ያውቁታል። እግዚአብሔር በብሉይ የተገለጠውን ሕጉን ሐሳቡንና ፈቃዱን ለእነዚህ ሰዎች የሰጠበት ዋናው ምክንያትም ዓለምን የሚያድነው አንድ ልጁ ከእነርሱ በሥጋ እንዲገለጥ ከቀድሞ ጀምሮ ስለወሰነ ነው፤ ስለዚህም አይሁድ እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንደ ሳምራውያን ከሌሎች አማልክት ጋር ቀላቅለው አልነበረም፤ የእግዚአብሔርን ማንነትና እግዚአብሔር የሚፈልገውን የልቡን መሻት በማወቅ ያመልኩት ነበር። በመሆኑም ጌታችን ኢየሱስ ለሳምራዊቱ ሴት «እኛ ግን መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን» ብሏታል (ቊ.22)።

      እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ ሳያውቁ እንዲሁም በልቡ ያለውን ፈቃዱንና ሐሳቡን ሳይረዱ ማምለክ በዘመናት ሁሉ የሚታይ የሰው ልጅ ጉድለት ነው። «ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል» (ሆሴ.4፡6) ተብሎ እንደተጻፈ በብዙዎች ዘንድ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ማወቅ ባለመኖሩ ከእግዚአብሔር ፊት መጥፋት በብዛት ይታያል፤ እግዚአብሔርን ማወቅ የጎደለው አምልኮም ብዙ ጊዜ ይፈጸማል። የሰማርያ ሰዎች እግዚአብሔርን በተገቢው መንገድ ቢያውቁት ኖሮ ሌሎች አማልክትን እያመለኩ እርሱንም አብረው አያመልኩትም ነበር፤ ከዚያ ይልቅ ብቻውን ይፈሩትና ያመልኩት ነበር፤ ምክንያቱም ቀዳሚው የእግዚአብሔር እውቀት እርሱ አምላክ መሆኑን መገንዘብ ብቻ ሳይሆን እርሱ ብቻውን አምላክ መሆኑንና ብቻውንም ሊመለክ የሚወድ «ቀናተኛ» አምላክ መሆኑን ማወቅ ነው፤ ይህን ፍላጎቱንም «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ» ሲል ገልጧልና (ዘጸ.20፡3-6)። የሰማርያ ሰዎች ግን ይህ እውቀት ስላልነበራቸው እግዚአብሔርን ከሰባት አማልክት ጋር አዳብለው ለማምለክ ይጥሩ ነበር፤ እግዚአብሔርን እንደሌሎች አማልክት የማየትና ከአማልክት አንዱ አድርጐ የመቊጠር ዝንባሌ በዓለማችን ላይ ዛሬም እንኳ ያለ ቢሆንም ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን ከቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ተብለው ከሚጠሩ የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ተርታ የማስቀመጥ ዝንባሌ በስመ ክርስትና በሚጠራው ዓለም ላይ በስፋት ይታያል። ጸሎትን፣ ስግደትንና፣ ዝማሬን ለቅዱሳን መላእክት እና ለሙታን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር አጋርቶ የማቅረብ ልማድ እርሱንና ፈቃዱን ሳያውቁ ማምለክ ነው፤ እግዚአብሔርን እያወቁ ማምለክ ግን ከእርሱ በቀር ሊፈራና ሊመለክ የሚገባው፤ ጸሎትን፣ ስግደትን፣ ስዕለትን (ልመናን)፣ መሥዋዕትን፣ ዝማሬን ሊቀበል የሚችል ሌላ እንደሌለ ተረድቶ በማስተዋል ማምለክ ነው።

      አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ብቻውን እየተመለከ በማንነቱ ሊታወቅ የሚችለውን ያህል ሳይታወቅ እንዲሁ በልማድ ብቻ የማምለክ ሁኔታ አለ። በእርግጥ የእግዚአብሔርን ማንነት ሰው አውቆ ይጨርሰዋል ለማለት አንደፍርም፤ እግዚአብሔር ከመታወቅ ያለፈ ማንነት ያለው አምላክ እንደሆነ እርግጥ ነው፤ «እግዚአብሔር ታላቅ ነው እኛም አናውቀውም» ተብሎ እንደተጻፈ (ኢዮ.36፡26) ነው። ይሁን እንጂ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን ያህል እግዚአብሔርን ልናውቀው ያስፈልጋል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ቢሆን በሥጋዊ አእምሮ ብቻ እንደዓለማዊ እውቀት ብናውቃቸው ሕይወት አይሆንልንም። ጌታ ኢየሱስ «እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱ ግን ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው» ብሏል (ዮሐ.5፡39)። እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናውቅ የምንችለው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስናውቅ ነው (ዮሐ.1፡18፣ 8፡40፣ 14፡7)፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በተገለጠው ማንነቱ አውቀነው ብናመልከው እግዚአብሔር በእጅጉ ይደሰታል፤ ስለሆነም አምልኮአችን የእርሱን የአምላካችንን ማንነቱንና ለእኛ ያደረገውን ነገር እያወቅን የምንፈጽመው አምልኮ ሊሆን ይገባል። ከአፋችን የሚወጡ የምስጋና ቃላት የተለመዱ ስለሆኑና ሁል ጊዜም ስለሚባሉ ብቻ የምንላቸው፣ የምንዘምራቸውም መዝሙሮች ዜማቸውንም ሆነ ግጥማቸውን ስለምንችለው ብቻ ባልተመሰጠ ልብ የምንዘምራቸው ሊሆኑ አይገባም። እያስተዋልንና የአምላካችን ማንነቱ እየታወቀን፣ የሚፈልገውንም ለይተን እያወቅን ልናመልክ ይገባናል፤ ምክንያቱም በአምልኮ ውስጥ ቢካተት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንና የማያሰኘውን ለይተን በማወቅ ብናመልከው በእርግጥ እውነተኛ አምላኪዎች እንሆናለንና። አይሁድ በብሉይ ኪዳን የተገለጠውን ያህል እግዚአብሔርን ያውቁት ነበር፤ ሕጉንና የመቅደሱንም ሥርዓት በሚገባ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፤ ስለዚህም አምልኮአቸው ለሚያውቁት አምላክ የሚቀርብ አምልኮ ነበር። አምልኮውም እግዚአብሔር በደነገገው መሠረት ይከናወን ነበር፤ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ስለአሠራሩ መለኮታዊ መመሪያ ባለውና በውድ ነገሮች ባሸበረቀ ቤተመቅደስ፣ ከሕዝብ ተለይተው በክህነት በሚያገለግሉ ሊቃነ ካህናትና ካህናት የእንስሳት መሥዋዕት፣ ጌጠኛ ልብስን በለበሱ መዘምራን በሙዚቃ የታጀበ ዝማሬ ይቀርብ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድ አምልኮ ምንም እንኳ ለሚያውቁት አምላክ በቅዱሳት መጻሕፍት በተደነገገው መንገድ የሚቀርብ ቢሆንም አምልኮአቸውን በሚመለከት የተሰጣቸው ሕግና ሥርዓት ግን ቀጣይነት አልነበረውም፤ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ሕግና ሥርዓት መሠረት የማይመለክበት ጊዜ ይመጣ ዘንድ እንደነበረው ሁሉ በምትኩም እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚመለክበት የአዲስ ኪዳን ዘመን ይመጣ ዘንድ ነበረው።

      በአዲስ ኪዳን ግን ከዚህ በተለየ መልኩ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ካህናት እንደሆኑ በግልጽ ተጽፎልናል፤ መጽሐፍ ቅዱ ስ ይህንን ሲገልጥ «... በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ይላል (1ጴጥ.2፡5)፤ በዚህ ቃል ውስጥ ከአምልኮ ጋር የተያያዘው የአማኞች ክህነት ተነግሮናል፤ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ካህናት በሚመሩት አምልኮ ውስጥ ዋናው የአምልኮ ክፍል የእንስሳት መሥዋዕትን ማቅረብ ነበር። በመሆኑም ካህናት ሕዝቡን ሁሉ በመወከል በመሠዊያው ላይ የተለያየ መሥዋዕትን ያቀርቡ ነበር፤ በአዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት «መንፈሳዊ መሥዋዕት» ነው፤ ይህም መንፈሳዊ መሥዋዕት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በኤፌ5፡2 ላይ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር «የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ራሱን ለእኛ አሳልፎ እንደሰጠ» ተጽፏል፤ በዕብራውያን መልእክትም ጌታ ኢየሱስ ራሱን ዘላለማዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረበ በተደጋጋሚ ተገልጿል (ዕብ7፡27፤ 9፡9-14 እና 26፤ 10፡11-22)። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን አምልኮ ውስጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መሥዋዕት ራሱን አንድ ጊዜ ለዘላለም ያቀረበው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም የምናቀርበው በመንፈሳዊ መንገድና በእምነት ነው፤ ይህም ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገሩና መሥዋዕትነቱን የሚያወሱ ቅዱሳን የምስጋና ቃላትን ወደ እግዚአብሔር በመናገርና እርሱን የሚመለከቱ ዝማሬዎችን በመዘመር ሊገለጥ ይችላል። እንዲህ ያለውን የተወደደ አምልኮ ከምእመናን ተለይተው መሪ ሆነው የሚመደቡ ሰዎች ሊመሩት አይችሉም። በመሠረቱ ሁላችንም ቅዱሳን ካህናት የሆንነው መንፈሳዊ መሥዋዕትን እናቀርብ ዘንድ መሆኑ በ1ጴጥ2፡5 ላይ ተገልጧል፤ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ከምእመናን መካከል ተራም ሆነ ሰሞን ወይም ፕሮግራም ሊወጣለት የሚገባው የካህናት ቡድን የለም። ሁላችንም ካህናት በመሆናችን በአንድነት በሰማያዊት መቅደስ ገብተን መሥዋዕቱን የማቅረብ እኩል መብት አለን፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሁላችን በሞተ ጊዜ ካህናቱንና ሕዝቡን ይለይ የነበረው የቤተመቅደስ መጋረጃ ዳግም ላይዘጋ ለሁለት ተቀዷል (ማቴ27፡51)፤ ይህም በሰው እጅ ወዳልተሠራችው ቅድስት እንገባ ዘንድ ለሁላችንም በሩ ክፍት መሆኑን ያሳየናል። በመሆኑም የዕብራውያን ጸሐፊ እንዳለው ጌታ ኢየሱስ «በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ» ድፍረት አለን (ዕብ.10፡19)። በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ወደፊቱ እንገባ ዘንድ የሰጠን መጋረጃ የኢየሱስን ሥጋ ነው፤ በእርሱ በኩል ገብተን ወደ ዙፋኑ የመቅረብ ድፍረቱ አለን፤ ስለሆነም በዚህ ዘመን አንዳንድ የአምልኮ መሪዎች ከመጋረጃው ኋላ፣ ሕዝቡ ደግሞ ከመጋረጃው በስተውጭ ሆኖ የሚካሄደው አምልኮ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችለው ይህ ድፍረት የሌለውንና ሁሉም ካህናት ያልሆኑበትን አምልኮተ ኦሪትን የተከተለ ነው። ሁላችንንም ከነገድ ከቋንቋ ዋጅቶ ካህናት እንድንሆን ያደረገን ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው (ራእ.1፡6፤ 5፡9-10)፤ ጴጥሮስ የሁላችንንም ካህናትነት ሲገልጥ «እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ» ብሏል(1ጴጥ2፡9)፤ ስለዚህ ሁላችንም ካህናት ከመሆናችን የተነሣ በምድር ላይ በአምልኮ ጊዜ እኛን የሚመሩ የተለዩ ካህናት እና የአምልኮ መሪዎች ሊኖሩን አይገባም።

      በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን መጋረጃ ባይኖርም ዓለማዊ የስብሰባን መንገድ በመከተል ለአምልኮ ጉባኤ መሪዎችን መመደብም የአዲስ ኪዳን የአምልኮ ባሕርይ አይደለም፤ አንድ ግለሰብ ¬«አስመላኪ»፣ ሕዝቡ ደግሞ «አምላኪ» የሚሆንበት ሥርዓትም አንድ ሰው «መሪ» ሕዝቡ «ተመሪ» ከሚሆንበት የዓለም ስብሰባ የተቀዳ ከመሆኑም ባሻገር በይዘቱም ከአምልኮተ ኦሪት ያልራቀ ነው። በአዲስ ኪዳን የአምልኮ ጉባኤ ግን እንዲህ ያለ የሰው ሥርዓት ሊኖር አይገባም፤ በአምልኮው ጊዜ የተሰበሰቡት ሁሉ የሚያደርጉት ነገር ራሳቸውን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ነው፤ የስብሰባውም መሪ ሰው ሳይሆን የሰውን ልብና የእግዚአብሔርንም መሻት የሚያውቀው መለኮታዊ አካል ነው።

      ሁለት ወይም ሦስት ከዚያም በላይ ሆነን እግዚአብሔርን ልናመልክ ስንሰበሰብ በቀጥታ ጌታ ኢየሱስ ወደሚገኝበት ሰማያዊ መቅደስ በመንፈስ እንገባለን። በዚያም ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናቱን አምልኮ ይመራል፤ ጌታ ኢየሱስ ብቸኛ ሊቀካህናት ሲሆን የተሰበሰቡት አማኞች ሁሉም ያለመለየት ካህናት ናቸው፤ አምልኮውም አማኞች በሙሉ እንደአሮን ልጆች ሆነው ተሰብስበው ጌታ ደግሞ በመካከላቸው እንደአሮን ሆኖ እየመራ የሚፈጸም የመንፈስ አገልግሎት ነው፤ በዚህ ረገድ ከሆነ ዛሬ ዛሬ «አስመላኪ» የሚባሉት ሰዎችም ሆኑ «ሠራኢ ቄሶች» የሚባሉት ራሳቸው በሊቀካህናችን በኢየሱስ የሚመሩ አምላኪዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል። ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ ያለችውን ጉባኤውን የሚመራው ደግሞ እርሱን ተክቶ አሁን በአማኞች ውስጥና በመካከላቸው በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ በኩል ነው፤ ከዚያም መንፈስ ቅዱስ የሚፈልገውን ነገር ይናገርበት ዘንድ በወደደው ሰው በኩል የምስጋና ቃል ወይም የምስጋና ዜማ ያመጣል፤ ሁላችንም ያን የምስጋና ቃል ወይም የምስጋና ዝማሬ ከተናገረው ወንድም ጋር በመተባበር በአንድነት እናመልካለን። በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያንም ከጌታ እራት ጋር ተያይዞ ይካሄድ የነበረው የአምልኮ ጉባኤ አፈጻጸምም ይህንኑ የተከተለ ነበር (ማቴ26፡26-30፤ የሐ.ሥ.20፡7፤ 1ቆሮ.14፡26)። ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚመራውና የአካሉ ብልቶች ከሆኑ አማኞች የሚወጣው ይህ የአዲስ ኪዳን አምልኮ እግዚአብሔርን በእጅጉ ያስደስተዋል።

በመንፈስና በእውነት ማምለክ

«... ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኖአል» (ዮሐ4፡23)

ጌታ ኢየሱስ የአይሁድ አምልኮ በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት ትክክለኛ መሆኑን ለሳምራዊቷ ቢገልጥላትም የመጨረሻው የእግዚአብሔር ፍላጎት ግን ያ ነው ብላ እንዳትደመድም ከዚያ የበለጠና በባሕርዩ ልዩ የሆነውን የአዲስ ኪዳን አምልኮ ሳይነግራት አልቀረም፤ ዋናውና የሚፈለገውም ይህ የአዲስ ኪዳን አምልኮ ነው። የጌታ ንግግር ሳምራዊቷን ሴት ከሳምራውያን አምልኮ ወደ አይሁድ አምልኮ ማሻገርን ዓላማው ያደረገ አልነበረም፤ የመጨረሻው ግቡ አብ ወደሚፈልገው እውነተኛው የአዲስ ኪዳን አምልኮ ማድረስ ነበር፤ ስለሆነም «እኛ ግን መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን» ካላት በኋላ «ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኖአል» በማለት ከአይሁድ አምልኮ በባሕርያቱ ልዩ የሆነውና እግዚአብሔር የሚፈልገው አምልኮ የሚፈጸምበት ጊዜ እንደሚመጣ ነገራት። በዚህ የጌታ ቃል ውስጥ የሚገኙት የአዲስ ኪዳን አምልኮ ባሕርያት በመንፈስ እናበእውነት bበሚሉት ሁለት ቃላት ተገልጠዋል፤ የእነዚህንም ሁለት የአምልኮ ባሕርያት ምንነት ቀጥሎ እንመለከታለን።

  1. በመንፈስ ማምለክ

ማንኛውም የአዲስ ኪዳን አገልግሎት በመንፈስ ሊፈጸም የሚገባው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «እርሱ ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን»(2ቆሮ3፡6) ይላል። በዚህም መሠረት የአዲስ ኪዳን አምልኮም በመንፈስ ሊፈጸም ይገባዋል። ጌታ ለሳምራዊቷ ሴት ከሰጠው ትምህርት ይዘት አንጻር ስንረዳው በመንፈስ ማምለክ በተራራና በከተማ ማለትም በምድራዊ ቦታ ሳይወሰኑ በመንፈሳዊ መንገድ የሚከናወን አምልኮተ እግዚአብሔርን ያመለክታል። ለአምልኮ የሚሆን ምንም ዓይነት ቊሳዊ ነገር በሌለበት፣ ዝርዝር የሆኑ የአምልኮ ሥርዓታት ባልተደረጉለት፣ የተለዩ ሰዎች የአምልኮ መሪ ባልሆኑበትና፣ የተለየ ቦታም ሆነ የተለየ አለባበስ በሌለበት ሁኔታ በሥጋ ከሚታዩ ሥርዓቶች ውጪ ሆነን እግዚአብሔርን ስናመልክ አምልኮአችን በመንፈስ የቀረበ አምልኮ ይሆናል። እነዚህን ነገሮች በዚሁ ጥናታችን ከጥቂት ገጾች በኋላ በስፋት እንመለስባቸዋለን።

የብሉይ ኪዳንን አምልኮ ስንመለከት እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው የተለየ ስፍራ ነበረው (ዘዳ.12፡11)፤ ያም ስፍራ የኢየሩሳሌም ከተማ እንደነበረች ቀደም ሲል ተመልክተናል (2ዜና.6፡6፤ መዝ.131፡13-14)፤ እንዲሁም ብሉይ ኪዳን “የአገልግሎት ሥርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ” ነበረው (ዕብ.9፡1)፤ በመቅደስም በቅድስትና በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ብዙ ንዋያተ ቅድሳት (የመገልገያ ዕቃዎች) ነበሩ (ዕብ9፡2-5)፤ አምልኮውን የሚመሩም የተለዩ ሊቃነ ካህናትና የተለዩ ካህናት(ዕብ5፡1-4፤ 8፡3-5፤ 9፡6-8) እንዲሁም በአምልኮውም ጊዜ የሚቀርቡ የተለያዩ የእንስሳት መሥዋዕቶች ነበሩ(ዕብ9፡13፤ 10፡1-4)። እነዚህ ሁሉ «እስከ መታደስ ዘመን» ድረስ በዚህ መልክ የተፈጸሙት ሥርዓቶች በዕብራውያን መልእክት ውስጥ «የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በሕሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም» ተብለዋል (ዕብ9፡10)፤ ለጊዜው በዘመናቸው እነዚህ ነገሮች ለሰማያዊና ለመንፈሳዊ ነገር ምሳሌና ጥላ ሆነው አገልግለዋል (ዕብ.8፡5፤ 10፡1)፤ ይሁን እንጂ በአዲስ ኪዳን ጌታ ኢየሱስ «ይመጣል» ብሎ የተናገረለት የመንፈስ አምልኮ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲደርስ ከላይ የተዘረዘሩት እነዚህ ሁሉ የብሉይ ኪዳን ነገሮች በሙሉ ቀርተዋል፤ በምትካቸውም ይመጣል የተባለለት ከሥጋ ዓይኖች እይታ ውጪ በእምነት ብቻ የሚፈጸመው የመንፈስ አምልኮ ቦታውን ይዞታል፤ ጊዜውም ጌታችን «አሁንም ሆኗል» ባለው መሠረት እርሱ ከነበረበት ጊዜ የሚጀምር እንደሆነ አይተናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ «እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን ነን»(ፊልጵ3፡3) እንዳለው በጥቅሉ የአዲስ ኪዳን አምልኮ ከብሉይ ኪዳን በተለየ ባሕርይ በመንፈስ የሚፈጸም አምልኮ ነው። ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች በማኅበርም ሆነ በየግላቸው እግዚአብሔርን ሲያመልኩ በመንፈስ ሊሆን ይገባል። «ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው» ተብሎ እንደተጻፈው (ዮሐ3፡6) በጌታ በኢየሱስ አምኖ ከማይጠፋ ዘር ዳግመኛ የተወለደ ሰው መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ካለው ባሕርይ ጋር የሚጣጣም ባሕርይ ያለው አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት ተሰጥቶታል፤ እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ሰው «የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤ ዳግም ተወልጃለሁ» ብሎ የሚያምነው በዓይነ ሥጋ ያየው ምንም ዓይነት ነገር ኖሮ አይደለም። ነገር ግን በመንፈስ የሚሆነውን ልጅነት የመቀበሉን እውነታ በእምነት ያረጋግጣል፤ እንዲህ ያለው አማኝ በዳግም ልደት ያገኘውና እግዚአብሔርን በመንፈስ ለማምለክ የሚችልበት የአዲስ ሕይወት ባሕርይ አለው። ይሁን እንጂ ዳግመኛ የተወለደ ሰውም ቢሆን በሥጋ የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል (1ቆሮ.3፡1-4)፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል» (ገላ.5፡16)፤ የሥጋ ምኞትም ባየለበት ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው በሥጋ ስሜት መሞላት፣ በዓይነ ሥጋ የሚታይ ነገርን መፈለግ፣ በምድራዊ ቊሳቊሶች መታገዝ፣ በሰዎች እና የሥጋ በሆኑ ሥርዓቶች ለመመራት መፈለግ ይታይበታል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሰው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ቢመስለውም እንኳ የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ሰው በመንፈስ ስለማምለክ ጌታ ኢየሱስ ባስተማረን ትምህርት ለመቃናት የልብ ፈቃደኝነትን ሊያሳይ ይገባዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በመንፈስ ማምለክ የሚለው ጌታ ኢየሱስ ያስተማረን ይህ የከበረ እውነት የኃጢአት ማዕከል የሆነው ሥጋ ስሜቶቹን ለሚገልጥባቸው ልምምዶች መሸፈኛ ሆኖ መቅረብ እንደሌለበት በጥንቃቄ ሊስተዋል ይገባል፤ «የማመልከው በመንፈስ ስለሆነ መንፈስ እንዳረገኝ እሆናለሁ» በሚል ሰበብ በአምልኮ ጊዜ የሚታየው የሥጋ አርነት በእውነተኛ የጌታ ልጆች ዘንድ በቀላሉ የሚታለፍ ሊሆን አይገባም። እግዚአብሔር የሰጠን መንፈስ «ራስን የመግዛት መንፈስ» (2ጢሞ.1፡7) እንደሆነ ለማስጣል የሚፈልገው ይህ ሥጋዊ አመለካከት ምንም እንኳ ራሱን ከመንፈሳዊ ነገር ጋር ለማዛመድ ቢሞክርም ጌታ «በመንፈስ ስለማምለክ» ካስተማረን እውነት ጋር ሲነጻጸር ባዕድ አስተሳሰብ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል። በመሠረቱ ምእመናን እግዚአብሔርን በመንፈስ እንዲያመልኩ የመንፈስ ቅዱስ እገዛ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ይመሰክራሉ። በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ለመሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ሊኖርብን ይገባል፤ ይህንን ጳውሎስ ሲያስረዳ «እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፡ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም» ይላል (ሮሜ 8፡9)፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ዘንድ መኖሩ በመንፈስ እንድንመላለስ፣ በመንፈስ እንድንኖር፣ በመንፈስ እንድናገለግልና በመንፈስ እንድናመልክ ያደርገናል እንጂ ለሥጋችን አርነትን አይሰጥም፤ መንፈስ የሥጋንም ምኞት ለማሸነፍ በውስጣችን በቅንዓት ይመኛል (ያዕ.4፡5)፤ አንዱ የመንፈስ ምኞትም እግዚአብሔርን ማምለክ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ አምልኮ ሲመራን ጌታ ኢየሱስ ካስተማረን በሚቃረን መልኩ በሥጋ ሥርዓታትና በሥጋ ስሜቶች እንድንሆን አያደርገንም፤ ይልቁንስ የእግዚአብሔር መንፈስ በራሱ ባሕርይ መሠረት መንፈሳዊ በሆነ መንገድ ብቻ እግዚአብሔርን እንድናመልክ፣ የሥጋ ነገርንም እንድንንቅ ሥጋንም በመግዛት ወይም ጸጥና ዝግ ብሎ እንዲኖር በማድረግ በመንፈሳዊ ስሜት ብቻ እንድናመልክ ያግዘናል። ከዚህም የተነሣ የሥጋ ዓይን ማረፊያ የሆኑ ባህላዊም ይሁን ዘመናዊ ሥርዓቶችና ቊሳቊሶች ከፊታችን ዘወር ይላሉ። ሥጋዊነትም ከመሻቱና ከስሜቱ ጋር ከአምልኮ ጉባኤያችን ይወገዳል።

  1. በእውነት ማምለክ

የአዲስ ኪዳን አምልኮ ሌላው መለያ ባሕርይው እግዚአብሔርን በእውነት ማምለክ ነው። በእውነት ማምለክም ልባዊ የሆነ አምልኮ ማቅረብን ያመለክታል። ጌታ ኢየሱስ በንግግሩ ውስጥ «በእውነት የሚሰግዱ.. ..» ሲል የተናገረላቸው ሰዎች የሚፈጽሙት አምልኮ እውነተኛ(ልባዊ) አምልኮ ነው፤ ይህም አምልኮውን ያለምንም ማስመሰል በቅንነትና በታማኝነት በሐቀኛ መንፈሳዊ ስሜት ሆነው እንደሚፈጽሙት ያሳያል።

እግዚአብሔርን በእውነት ለማምለክ አስቀድሞ እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ያስፈልጋል። የስም ክርስቲያን ወይም በግብዝነት ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ አማኝ በእውነት ማምለክ አይችልም። የሚያመልክ ቢመስለው እንኳ የሚያመልከው የተለመደ የአምልኮ ፕሮግራም ስላለ፣ መዝሙር ስለሚችል ብቻ ወይም ሰዎችን ደስ ለማሰኘት አልያም ለታይታ ብቻ ይሆናል። እንዲህ ያለው አምልኮ ከንቱ አምልኮ ነው። ስለሆነም አማኝ አስቀድሞውኑ በእውነት የክርስቶስ ደቀመዝሙር መሆን አለበት። የክርስቶስ እውነተኛ ደቀመዝሙር ሊሆን የሚቻለው ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቃል በመኖር ብቻ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ሲናገር «እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ» ብሏል (ዮሐ.8፡31)፤ ቃሉን ማወቅ ብቻውን እውነተኞች አያደርገንም፤ በእውነት የእርሱ ደቀመዝሙር የሚያደርገን በቃሉ መኖር ነው። በቃሉ የሚኖሩ አማኞች ልባቸውን የሚሞላው የእግዚአብሔር እውነት ብቻ ነው፤ ለውሸትና ለማስመሰል ምንም ስፍራ አይኖራቸውም፤ በየትኛውም ንግግር ከባልንጀሮቻቸው ጋር መቼም ቢሆን በእውነት ላይ አይዋሹም (ያዕ.3፡14)፤ ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አይችሉም (2ቆሮ13፡8)፤ እውነት በሁለንተናቸውና በኑሮአቸው ሁሉ ስለምትዋሐዳቸው የማስመሰልና የማቻቻል ባሕርይ ሊኖራቸው አይችልም። እነዚህ ሰዎች እውነትና ውሸት ተቻችለው አብረው እንዲኖሩ በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድም ተወዳጅነት ላይኖራቸው ይችላል። ጌታ ኢየሱስ እውነትን የሚናገር እና እውነትን የሚያደርግ በመሆኑ ከእግዚአብሔር ያልሆኑ ሰዎች እንዳልተቀበሉት ሁሉ በእውነት የሚያመልኩትም ከእውነት ባልሆኑ ሰዎች ተቀባይነት ላያገኙ ይችላሉ፤ ሆኖም በዚህ ቅር ሳይሰኙ ደስ ብሏቸው ይኖራሉ።

በእውነት የክርስቶስ ደቀመዝሙር የሆነ አማኝ እግዚአብሔርን በሚያመልክበትም ጊዜ በእውነት ያመልካል። በማስመሰልና በማያምንበት ነገር ውስጥ ሆኖ ራሱን እያሳተ ማምለክ ባሕርይው አይደለም። ለሌሎች ሰዎች ብሎ የሚዘምረውም ሆነ የሚያመሰግነው ነገር አይኖረውም። ወይም በብዙዎች ተጽዕኖ ሥር በመውደቅ ብዙዎች ስለተስማሙበት ወይም ችላ ስላሉት ብቻ የውሸትና የስህተት አምልኮን መታገሥ አይችልም። የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረው የአምልኮ ባሕርያት በቀር ከሰዎች ልምምድ በመኰረጅ ወይም በብዛት የተለመደው የአምልኮ ሥርዓት እንዲህ ነው በማለት ለሰው ሥርዓትና ልምምድም አይሸነፍም። በጉባዔም ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔርን ሲያመልክ በጉባዔው የአዘማመር ስልት ወይም አጠቃላይ የዕለቱ የአምልኮ ጊዜ በመሞቁና በመቀዝቀዙ ላይ ተመሥርቶ አያመልክም። መዝሙር በድምቀት ሲዘመርና አንዳንዶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ቃላትንም አስረግጠው ሲያመሰግኑ «የዛሬው አምልኮ የሚባርክ ነው»፣ በዝግታ ሲመለክ ደግሞ «የዛሬው አምልኮ አይባርክም» እያለ አምልኮን በተራ ምክንያቶች አይገመግምም፤ ምክንያቱም በድምቀት ማምለክም ሆነ በዝግታ ማምለክ በእውነት የማምለክ ምልክቶች አይደሉምና። በእውነት የሚያመልክ ሰው ቀድሞውኑ የአምልኮውን ድምቀት ወይም ዝግታ በመገምገም ጊዜ አያጠፋም፤ ልቡናው በሚያመልከው በሕያው አምላክ ላይ ያርፋል እንጂ የአምልኮ ሥርዓትን በመከታተል አይሞላም። ስለሆነም በግልም ይሁን በማኅበር ክርስቲያኖች ከምድራዊና ቊሳዊ ምክንያቶች፣ ከሰው ሥርዓቶችና ከሥጋዊ ስሜቶች ተለይተው እግዚአብሔርን በእውነት ሊያመልኩ ይገባል።

አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና

(ዮሐ.4፡23)

አምልኮ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡት ምስጋናና ውዳሴ ነው፤ ይህም ሲባል እግዚአብሔርን በማንነቱ እያደነቅን ከፍ ከፍ በማድረግ የምንሰጠው ክብር እና ያደረገልንን ነገር በማሰብ የምናቀርብለት ምስጋና ነው። ስለሆነም እግዚአብሔርን ስናመልክ የእግዚአብሔር የአባታችንን መሻት ለይተን በማወቅ ሊሆን ይገባል። ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩትን እነዚህን ይሻል።

በቅድሚያ ልናውቅ የሚገባን እግዚአብሔር አምልኮን የሚፈልግ አምላክ መሆኑን ነው፤ በዘዳግ.10፡13 ላይ «እስራኤል ሆይ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው?» ይላል፤ ስለሆነም እግዚአብሔር እንድናመልከው ይፈልጋል።«እግዚአብሔርን በማንነቱ ካወቅነውና ካመንነው በጥሩ ሥነምግባርም ከኖርን በቂ ነው» ብለው ራሳቸውን ከአምልኮ ውጪ ያደረጉ ሰዎች ይህንን የእግዚአብሔርን መሻት ሲያውቁ እርሱን ያመልኩት ዘንድ ልባቸው ሊነሣሣ ይችላል።

እግዚአብሔርን ስናመልከው መሻቱን ጠብቀን ሊሆን ይገባል። ሰዎች «እንዲህ መመለክ አለበት» ወይም «እኛ የምንፈልገው ሥርዓተ-አምልኮ እንዲህ ነው» ስላሉ ልናመልክ አይገባንም፤ ይህ የሰዎችን ፍላጎት የተከተለ አምልኮ ከንቱ አምልኮ ነው። በተጨማሪም ከሥጋችን ውስጥ መንፈሳዊ መስሎ በሚነሣ ፍላጐት ተጠላልፈን የራሳችንን መሻት ለማርካትም ልናመልክ አይገባም፤ ስለሆነም እነዚህን ትተን እግዚአብሔር የሚፈልገውን (የሚሻውን) የመንፈስና የእውነት አምልኮ በማቅረብ ልንተጋ ይገባናል። በተለይ እግዚአብሔር አባት እንደመሆኑ እኛም ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን የእኛን መሻት ትተን ለአባታችን መሻት ልንታዘዝ ይገባናል። እንደልቡ መሻት የቀረበለት አምልኮም እግዚአብሔርን በእጅጉ ያስደስተዋል።

በመንፈስና በእውነት ያልሆነ አምልኮ

«እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» (ዮሐ.4፡24)

በአዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር የሚመለክበት መንገድ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ይመለክበት ከነበረው መንገድ በእጅጉ ይለያል፤ በብሉይ ኪዳን ማናቸውም አገልግሎት ይፈጸም የነበረው በብዙ ዝርዝር ሥርዓትና የዚህ ዓለም በሆነ ምድራዊ መቅደስ በመገልገል ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ሲገልጥ «ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዓት እና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት» ይላል (ዕብ9፡1)፤ አዲስ ኪዳን ግን ከዚህ በተለየ መልኩ በመንፈስ የሚፈጸም አገልግሎት አለው። ይህም «እርሱ ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን» ተብሎ ተገልጧል (2ቆሮ3፡6)፤ በብሉይ ኪዳን የነበረው ፊደላዊ የሆነ የአገልግሎት ሥርዓትና በምድራዊ ቤተመቅደስ ይቀርብ የነበረው አምልኮ ለሰማያዊና ለመንፈሳዊ ነገር ምሳሌና ጥላ ከመሆን ባሻገር የእግዚአብሔርን መሻት የሚያሟላ አልነበረም (ዕብ.8፡5)፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ስለሆነም በመንፈስና በእውነት የሚቀርብ አምልኮን ይሻል (ዮሐ4፡23-24)። የብሉይ ኪዳን ዘመን ነገሮች ሁሉ ፊደላዊና ዝርዝር የአገልግሎት ሥርዓትን የተከተሉ እንጂ በመንፈስ የሚፈጸሙ ባለመሆናቸው ይህን የእግዚአብሔርን መሻት የሚያረኩ አልነበሩም። ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም ከመጣ በኋላ እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት የሚመለክበት ጊዜ ደርሷልና ሰዎች በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል። ጌታ ኢየሱስ «የሚሰግዱለት ሁሉ በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» ብሎ ሲናገር በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ መፈጸም ያለበትን ዋነኛና መሠረታዊ የሆነ የአምልኮ መመሪያ መስጠቱ መሆኑን ልናስተውል ይገባል፤ «ያስፈልጋቸዋል» የሚለው ግስ ጌታ የተናገረው ይህ ቃል «መመሪያ» እንደሆነ ያሳያልና። ጌታችንና መምህራችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ ባስቀመጠልን የአምልኮ መመሪያ መሠረት መንፈስ ለሆነው እግዚአብሔር የሚሆን በመንፈስና በእውነት የሚፈጸም አምልኮ ልናቀርብ ይገባናል። በአምልኮ ጊዜ ማሰብ ያለብን እኛ የምንፈልገውን ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነው፤ እንደዚሁም ማተኰር ያለብን ለእኛ ደስ በሚያሰኘን የአምልኮ አፈጻጸም ላይ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ደስ በሚያሰኘው ላይ ነው።

እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ማምለክ ሲባል ከዝርዝር የአገልግሎት ሥርዓት፣ ከቊሳዊ የመገልገያ ዕቃዎችና ከሥጋ ስሜቶች ተለይቶ ከልብ በሆነ እምነት ማምለክ ማለት ነው። ይህም ዳግም የተወለደው የአዲሱ ሕይወታችን አንዱ መለያ ባሕርይ ነው። የአዲስ ኪዳኑ እውነት ይህ ሆኖ ሳለ በዘመናችን በብሉይ ኪዳንና በዓለማዊነት ተጽዕኖ ሥር የወደቀ አምልኮ ሲፈጸም በብዙ ስፍራዎች ይታያል፤ ዝርዝር የአገልግሎት ሥርዓት፣ ቊሳዊ የመገልገያ ዕቃዎችና የሥጋ ስሜቶች ብዙ የአምልኮ ጉባዔያትን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ወደ ተሻረው አምልኮተ ኦሪት ባፈገፈጉ ሰዎች አማካኝነት ከብሉይ ኪዳን የተቀዱ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከዓለምና ከአምልኮተ አሕዛብ የተኰረጁ ሆነው እናገኛቸዋለን፤ ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በስፋት ተቀባይነት አግኝተውና በሰው አሠራር ውስጥ ተለምደው ብንመለከታቸውም በክርስቶስ የአምልኮ ትምህርት ውስጥ የማይገኙ እስከሆኑ ድረስ ከአምልኮአችን ልናስወግዳቸው ያስፈልጋል፤ ለዚህም ይረዳን ዘንድ በዘመናችን የሚታየው በመንፈስና በእውነት ያልሆነው አምልኮ በየጉባኤያቱ ራሱን የሚገልጥባቸውን የሰው ሥርዓቶችንና ልምምዶችን በመዘርዘር የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረንን እውነት ቀጥሎ እንመለከታለን።

  1. አምልኮን የሚመራ ሰው መመደብ

የጉባዔ አምልኮ በሚፈጸምበት ጊዜ ከሚታዩት የሰው ሥርዓቶች አንዱ አምልኮውን የሚመራ ሰው መመደብ ነው፤ ይህም አምልኮን የሚመራ ሰው አንዳንድ ጊዜ በዘልማድ በተወሰኑት ዘንድ «ሠራኢ ቄስ» በሌሎች ዘንድ ደግሞ «አስመላኪ» ተብሎ ይጠራል። «ሠራኢ ቄስ» የሚባለው ከሕዝቡ የተለዩ ሰዎችን የካህናት ወገን በሚያደርገው ሥርዓት የሚመደብ የአምልኮ መሪ ሲሆን «አስመላኪ» ደግሞ በዓለማዊው መድረክ «ኮንዳክተር ወይም ፕሮግራም መሪ» ተብሎ የሚጠራውን ሰው ባሕርይ የተላበሰ፣ የንግግርና የአቀናባሪነት ችሎታ ያለውና ሌሎች ሲያመልኩ እርሱ እንዲያስመልክ የሚመደብ ሰው ነው።

በብሉይ ኪዳን ከእስራኤል ሁሉ ተለይተው አምልኮን የሚመሩ ሰዎች ከአሮን ወገን የሆኑት ካህናት ብቻ ነበሩ፤ ለካህናቱም ሊቀ ካህናት ነበራቸው፤ እነዚህ ካህናት በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ሥርዓተ አምልኮውን የሚያካሂዱት ዘወትርና በየበዓላቱ ነበር፤ በሙሴ ዘመንም አሮንና ልጆቹ ይህንን የክህነት ሥራ ይሠሩ ነበር (ዘጸ.28፡1)፤ በአምልኮው ውስጥ ካላቸው አገልግሎት መካከልም ዋና ዋናዎቹ በየቀኑ ሁለት ጠቦቶችን ለሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ፣ በዕጣን መሠዊያው ላይ ጣፋጭ ዕጣን ማጠንና ከማታ እስከ ማለዳ የሚቆይ መብራትን ማብራት ናቸው (ዘጸ.29፡38-30፡8)፤ እነዚህ ካህናትም ሲሾሙ ሰውነታቸውን ይታጠባሉ፤ የተለየ ልብሰ-ተክህኖም ይለብሳሉ፤ የቅብዓት ዘይትም ይፈስባቸዋል (ዘሌ.8፡1-13)፤ በዚህ መልክም የአሮን ወገኖች ከሕዝቡ ተለይተው የካህናት ወገን ይሆኑ ነበር። ከእነርሱ ሌላ ሰው በክህነት ሊያገለግል አይችልም ነበር (ዘኁል.16፡40፤ 18፡5)። በየዕለቱም ሆነ በየሳምንቱ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮ የሚመሩ ካህናት በተራ ወይም በሰሞን ይመደቡ ነበር። በዳዊት ዘመን በዕጣ ተመድበው የሚያገለግሉ 24 ካህናት ነበሩ (1ዜና.24፡1-19)፤ ይህም በተራ እየተመደቡ በክህነት ማገልገል ጌታችን እስከ ተወለደበት ዘመን ድረስ እንደቀጠለ ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ይቻላል፤ በሉቃ1፡8-10 ዘካርያስ በክፍሉ ተራ መሠረት በመቅደስ ገብቶ ያገለግል እንደነበርና ሕዝቡ ግን በውጭ ቆመው ይጸልዩ እንደነበር እናነባለን፤ ስለሆነም የብሉይ ኪዳን አምልኮ በዚህ ዓይነት ካህናቱ በመቅደስ ውስጥ ሕዝቡ ግን በውጪ ሆኖ የሚፈጸም አምልኮ ነበር።

በአዲስ ኪዳን ግን ከዚህ በተለየ መልኩ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ካህናት እንደሆኑ በግልጽ ተጽፎልናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲገልጥ «... በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ይላል (1ጴጥ.2፡5)፤ በዚህ ቃል ውስጥ ከአምልኮ ጋር የተያያዘው የአማኞች ክህነት ተነግሮናል፤ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ካህናት በሚመሩት አምልኮ ውስጥ ዋናው የአምልኮ ክፍል የእንስሳት መሥዋዕትን ማቅረብ ነበር። በመሆኑም ካህናት ሕዝቡን ሁሉ በመወከል በመሠዊያው ላይ የተለያየ መሥዋዕትን ያቀርቡ ነበር፤ በአዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት «መንፈሳዊ መሥዋዕት» ነው፤ ይህም መንፈሳዊ መሥዋዕት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በኤፌ5፡2 ላይ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር «የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ራሱን ለእኛ አሳልፎ እንደሰጠ» ተጽፏል፤ በዕብራውያን መልእክትም ጌታ ኢየሱስ ራሱን ዘላለማዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረበ በተደጋጋሚ ተገልጿል (ዕብ7፡27፤ 9፡9-14 እና 26፤ 10፡11-22)። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን አምልኮ ውስጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መሥዋዕት ራሱን አንድ ጊዜ ለዘላለም ያቀረበው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም የምናቀርበው በመንፈሳዊ መንገድና በእምነት ነው፤ ይህም ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገሩና መሥዋዕትነቱን የሚያወሱ ቅዱሳን የምስጋና ቃላትን ወደ እግዚአብሔር በመናገርና እርሱን የሚመለከቱ ዝማሬዎችን በመዘመር ሊገለጥ ይችላል። እንዲህ ያለውን የተወደደ አምልኮ ከምእመናን ተለይተው መሪ ሆነው የሚመደቡ ሰዎች ሊመሩት አይችሉም። በመሠረቱ ሁላችንም ቅዱሳን ካህናት የሆንነው መንፈሳዊ መሥዋዕትን እናቀርብ ዘንድ መሆኑ በ1ጴጥ2፡5 ላይ ተገልጧል፤ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ከምእመናን መካከል ተራም ሆነ ሰሞን ወይም ፕሮግራም ሊወጣለት የሚገባው የካህናት ቡድን የለም። ሁላችንም ካህናት በመሆናችን በአንድነት በሰማያዊት መቅደስ ገብተን መሥዋዕቱን የማቅረብ እኩል መብት አለን፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሁላችን በሞተ ጊዜ ካህናቱንና ሕዝቡን ይለይ የነበረው የቤተመቅደስ መጋረጃ ዳግም ላይዘጋ ለሁለት ተቀዷል (ማቴ27፡51)፤ ይህም በሰው እጅ ወዳልተሠራችው ቅድስት እንገባ ዘንድ ለሁላችንም በሩ ክፍት መሆኑን ያሳየናል። በመሆኑም የዕብራውያን ጸሐፊ እንዳለው ጌታ ኢየሱስ «በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ» ድፍረት አለን (ዕብ.10፡19)። በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ወደፊቱ እንገባ ዘንድ የሰጠን መጋረጃ የኢየሱስን ሥጋ ነው፤ በእርሱ በኩል ገብተን ወደ ዙፋኑ የመቅረብ ድፍረቱ አለን፤ ስለሆነም በዚህ ዘመን አንዳንድ የአምልኮ መሪዎች ከመጋረጃው ኋላ፣ ሕዝቡ ደግሞ ከመጋረጃው በስተውጭ ሆኖ የሚካሄደው አምልኮ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችለው ይህ ድፍረት የሌለውንና ሁሉም ካህናት ያልሆኑበትን አምልኮተ ኦሪትን የተከተለ ነው። ሁላችንንም ከነገድ ከቋንቋ ዋጅቶ ካህናት እንድንሆን ያደረገን ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው (ራእ.1፡6፤ 5፡9-10)፤ ጴጥሮስ የሁላችንንም ካህናትነት ሲገልጥ «እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ» ብሏል(1ጴጥ2፡9)፤ ስለዚህ ሁላችንም ካህናት ከመሆናችን የተነሣ በምድር ላይ በአምልኮ ጊዜ እኛን የሚመሩ የተለዩ ካህናት እና የአምልኮ መሪዎች ሊኖሩን አይገባም።

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን መጋረጃ ባይኖርም ዓለማዊ የስብሰባን መንገድ በመከተል ለአምልኮ ጉባኤ መሪዎችን መመደብም የአዲስ ኪዳን የአምልኮ ባሕርይ አይደለም፤ አንድ ግለሰብ ¬«አስመላኪ»፣ ሕዝቡ ደግሞ «አምላኪ» የሚሆንበት ሥርዓትም አንድ ሰው «መሪ» ሕዝቡ «ተመሪ» ከሚሆንበት የዓለም ስብሰባ የተቀዳ ከመሆኑም ባሻገር በይዘቱም ከአምልኮተ ኦሪት ያልራቀ ነው። በአዲስ ኪዳን የአምልኮ ጉባኤ ግን እንዲህ ያለ የሰው ሥርዓት ሊኖር አይገባም፤ በአምልኮው ጊዜ የተሰበሰቡት ሁሉ የሚያደርጉት ነገር ራሳቸውን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ነው፤ የስብሰባውም መሪ ሰው ሳይሆን የሰውን ልብና የእግዚአብሔርንም መሻት የሚያውቀው መለኮታዊ አካል ነው።

ሁለት ወይም ሦስት ከዚያም በላይ ሆነን እግዚአብሔርን ልናመልክ ስንሰበሰብ በቀጥታ ጌታ ኢየሱስ ወደሚገኝበት ሰማያዊ መቅደስ በመንፈስ እንገባለን። በዚያም ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናቱን አምልኮ ይመራል፤ ጌታ ኢየሱስ ብቸኛ ሊቀካህናት ሲሆን የተሰበሰቡት አማኞች ሁሉም ያለመለየት ካህናት ናቸው፤ አምልኮውም አማኞች በሙሉ እንደአሮን ልጆች ሆነው ተሰብስበው ጌታ ደግሞ በመካከላቸው እንደአሮን ሆኖ እየመራ የሚፈጸም የመንፈስ አገልግሎት ነው፤ በዚህ ረገድ ከሆነ ዛሬ ዛሬ «አስመላኪ» የሚባሉት ሰዎችም ሆኑ «ሠራኢ ቄሶች» የሚባሉት ራሳቸው በሊቀካህናችን በኢየሱስ የሚመሩ አምላኪዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል። ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ ያለችውን ጉባኤውን የሚመራው ደግሞ እርሱን ተክቶ አሁን በአማኞች ውስጥና በመካከላቸው በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ በኩል ነው፤ ከዚያም መንፈስ ቅዱስ የሚፈልገውን ነገር ይናገርበት ዘንድ በወደደው ሰው በኩል የምስጋና ቃል ወይም የምስጋና ዜማ ያመጣል፤ ሁላችንም ያን የምስጋና ቃል ወይም የምስጋና ዝማሬ ከተናገረው ወንድም ጋር በመተባበር በአንድነት እናመልካለን። በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያንም ከጌታ እራት ጋር ተያይዞ ይካሄድ የነበረው የአምልኮ ጉባኤ አፈጻጸምም ይህንኑ የተከተለ ነበር (ማቴ26፡26-30፤ የሐ.ሥ.20፡7፤ 1ቆሮ.14፡26)። ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚመራውና የአካሉ ብልቶች ከሆኑ አማኞች የሚወጣው ይህ የአዲስ ኪዳን አምልኮ እግዚአብሔርን በእጅጉ ያስደስተዋል።

  1. የመዘምራን አገልግሎት መኖር

በሃይማኖተኛው የክርስትና ዓለም በስፋት እንደሚታየው በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የአምልኮ ጉባኤና የእግዚአብሔር ቃል የሚቀርብበት ጉባኤ ተለይተው አይታወቁም። ሁለቱንም ባንድ ላይ የመቀላቀል ልማድ በስፋት ይታያል። ከዚህም የተነሣ ሰባኪዎች በመድረክ ላይ ከመቆማቸው በፊትና ከጨረሱ በኋላ አምልኮ የማድረግ ልማድ አለ፤ አምልኮውም በአንድ የአምልኮ መሪ ከመመራቱም በተጨማሪ ከቃል በፊትና በኋላ ፊታቸውን ወደ ሕዝብ በማድረግ በመድረክ ላይ ተሰልፈው የሚዘምሩ መዘመራን መዝሙር የሚያቀርቡበት ጊዜም አለ። በጉባኤ መዝሙር መዘመር እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባ የከበረ አምልኮ መሆኑ የታወቀ ነው፤ በመዘምራን አማካኝነት እየተመሩ የመዘመርና የማምለክ ሥርዓት ግን የብሉይ ኪዳን ልማድ ከመሆኑ የተነሣ እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት በሚያመልክ ጉባኤ ሊታይ የሚገባው አይደለም።

በመጀመሪያ ደረጃ የአምልኮ መዝሙር ወደ እግዚአብሔር የሚዜምና የከንፈር ፍሬ የሆነ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፤ «እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቅርብለት» ተብሎ እንደተጻፈው የምስጋናው መሥዋዕት የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ነው (ዕብ13፡15)፤ እንደዚሁም «በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ» ተብሎ ተጽፏል (ቈላ3፡16)፤ ከዚህ አኳያ ሕዝቡ ተቀምጦ በአምልኮ ጊዜ መዘምራን ከመድረክ ወደ ሕዝብ የአምልኮ መዝሙር ሲዘምሩ የሚደመጥበት ሥርዓት ከተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል ጋር ምን ያህል እንደሚቃረን መረዳት ይቻላል። «በሕዝቡ ፈንታ መዘምራኑ እየዘመሩ ነው» እንዳይባል የተለዩ ካህናት ስለሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡበት አገልግሎት አብቅቶ ሁሉም ካህናት ወደሆኑበት የአዲስ ኪዳን ዘመን ገብተናል።

ለመሆኑ የመዘምራን አገልግሎት የተቀዳው ከየት ነው? የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ስናጠና የዚህን ጥያቄ መልስ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የመዘምራን አገልግሎት እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ አልነበረም፤ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከሴሎ ወደ ጽዮን ካመጣና ታቦቱም አርፎ ከተቀመጠ በኋላ በመገናኛው ድንኳን የሚያገለግሉ መዘምራንን አደራጀ (1ዜና6፡31-32)፤ መዘምራኑም ከሌዊ ነገድ ብቻ ነበሩ (1ዜና.6፡48፤ 9፡33)፤ በአጠቃላይ በዳዊት ዘመን 4ሺህ የሚሆኑ መዘምራን ነበሩ (1ዜና.23፡5)፤ ከነዚህም ውስጥ ትንቢት እየተናገሩም ጭምር ያገለግሉ የነበሩት መዘመራን ቊጥር 288 ነበር(1ዜና.25፡1-7)፤ አሳፍ፣ ኤማንና ኤዶታም በተባሉ አለቆች ለሦስት ተከፍለው ይመሩ ነበር፤ ለአገልግሎታቸውም ሰሞን (ተራ) ነበራቸው (1ዜና.25፡8-31)፤ ይህ ከዳዊት በኋላም በየዘመናቱ ቀጥሏል። ንጉሥ ሕዝቅያስ በዘመኑ ቤተመቅደሱን ከርኵሰት ካነጻ በኋላ መዘምራንን በማቆም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አድርጓል። ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃል «ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፤ መዘምራኑም ዘመሩ፤ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ሁሉ ይህ ሆነ» ይላል (2ዜና.29፡28)። በኢዮስያስ ዘመንም የመዘምራን አገልግሎት ነበር (2ዜና.35፡15)፤ ከባቢሎን ምርኮ መልስም በእስራኤላውያን መካከል 200 ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ (ዕዝ.2፡65)።

በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ግን ከምእመናን መካከል ተለይተው በሕዝብ ፊት ቆመው የሚዘምሩ መዘምራንን በአንድም ስፍራ አናይም፤ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ብናነብ በቤተክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በዳዊት ሥርዓት መሠረት መዘምራንን እንድናደራጅ የተነገረን አንድም ቃል የለም። የእኛ ዳዊታችን ጌታ ኢየሱስ ነው፤ እርሱ ደግሞ በመዘምራን እየተመሩና እየተገለገሉ ማምለክን ሳይሆን በመንፈስና በእውነት ማምለክን አስተምሮናል። እርሱ ሊቀካህናችን ሲሆን እኛ ደግሞ ካህናቱ እንደመሆናችን መጠን እርሱ የመዘምራን አለቃ ሲሆን እኛ ሁላችን ደግሞ ያለመለያየት መዘምራኑ ነን። በእርሱ እየተመራን ሁላችንም በአንድ ቃል ሆነን በመንፈስ እንዘምራለን። ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ጉባዔ ናት፤ ስለሆነም እርሱ በዚህች ጉባዔ መካከል በመንፈስ ተገኝቶ አብሮን ያመሰግናል፤ «ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጉባኤም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ» ተብሎ የተነገረው ቃል ስለ እርሱ እንደሆነ በዕብራውያን መልእክት ተነግሮናል (ዕብ.2፡13)፤ በስቅለቱ ዋዜማ የእርሱን እራት ለደቀመዛሙርቱ ካበላ በኋላ ከደቀመዛሙርቱ ጋር አብሮ መዝሙር እንደዘመረ እናነባለን (ማር.14፡26)፤ ከዚህ ውጪ ግን በማስተማር ዘመኑ ይከተለው ከነበረው ብዙ ሺህ ሕዝብ መካከል እንዲሁም በመጨረሻ አብረውት ከጸኑት ከ120ቹ ሰዎች መካከል መዘምራንን ሲያደራጅ አናይም። ከእርሱ በኋላም ሐዋርያት በየአገሩ ወንጌልን በመስበክ ሕዝብን በሚሰበስቡበት ጊዜ መዘምራንን ሲያቆሙ አናይም። የኋላ ዘመን ሰዎች ግን የስህተት አስተማሪዎች ትምህርታቸውን በመዝሙር ያስፋፉ ስለነበር በእነርሱ ዘዴ ትምህርታቸውን ለማፍረስ ሲሉ ደናግል መዘምራንን እያስከተሉ በመዘዋወር ያገለግሉ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፤ ይህም ቢሆን ወንጌል የሚሰበከው በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወይም በሰው ጥበብ ለዚያውም ሐሰተኞች የተጠቀሙበትን ዘዴ በመከተል ስላልሆነ ተቀባይነት የለውም (1ተሰ1፡5፤ 1ቆሮ2፡5)፤ በዚህ መልኩ ትክክለኛ ባልሆነ መነሻ የተጀመረው የመዘምራን አገልግሎት አሁን የቤተክርስቲያንን ትክክለኛ ባሕርያት ባጡት ጉባኤያት መካከል መደበኛ ሥርዓት ለመሆን በቅቶአል። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ሰዎች ይህንኑ የመዘምራን አገልግሎት በብሉይ ኪዳን ከነበረው የዳዊት መዘምራን አገልግሎት ጋር ለማያያዝ ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የዳዊት የመዘምራን አገልግሎት ለአዲስ ኪዳኑ አምልኮ መሠረት ሊሆን ስለማይችል ምክንያታቸው ትክክል አይደለም።

በዳግመኛ ልደት ከመንፈስ የተወለዱ የእግዚአብሔር ልጆች በዳዊት ዘመን የነበረውን ፊደላዊ ሥርዓተ አምልኮ አይከተሉም። እውነተኛው የአዲስ ኪዳን ዳዊት ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማራቸው መንፈስ ከሆነው አዲሱ ልጅነታቸው ጋር እና መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣጣመውን የመንፈስና የእውነት አምልኮ በማቅረብ ደስ ይሰኛሉ። በአምልኮ ጊዜ እውነተኛ አማኞች ደስታቸው የሚመነጨው እግዚአብሔር እንዲቀርብለት በወደደው መንገድ አምልኮን ለማቅረብ በመቻላቸው ነው፤ ከፊታቸው ጌጠኛ ልብስ ለብሰው የተሰለፉ መዘምራንን ባለማየታቸውም ቅር አይሰኙም። ይልቁንም ያለእነዚህ መዘምራን መሪነት መንፈስ ለሆነው አምላካቸው በአንድነት በሚያቀርቡት የመንፈስ አምልኮ በእጅጉ ይመሰጣሉ።

ከአዲስ ኪዳን አምልኮ ባሕርይ ውጪ የመዘምራንን ቡድን በማደራጀት ለአምልኮ መገልገሉ በራሱ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው እንደሚታየው የጠብ፣ የሐሜትና የፉክክር ማዕከልን ማቋቋም መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤ በሚለብሱት ልብስ፣ በሚሰለፉበት ቦታ በሚያወጡት ድምፅና ለመታየት በሚያደርጉት እሽቅድምድም በአንድ የመዘምራን ቡድን ውስጥ ያሉት አባላት ብዙውን ጊዜ ፍቅር አይኖራቸውም፤ እንደዚሁም በአንድ ቡድን ያሉት በሌላ ቡድን ካሉት ጋር በመወዳደርና በመቀናናት ቡድናዊነት፣ ወገናዊነትና መለያየት እንዲፈጠር ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወቱ ብዙ ጊዜ የሚታዩት የመዘምራን ቡድኖች ናቸው። ከዚህም አንጻር ያለው ጎጂነት ሊዘነጋና በቀላሉ ሊታይ አይገባም።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አምልኮን የሚመሩ የመዘምራን ቡድን በሚገኙባቸው ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ውስጥ የመዘምራን ቡድን አባል መሆን እንደ አንድ የጸጋ ስጦታ የሚታይበት ሁኔታም አለ። በአዲስ ኪዳን ግን በመዘምራንነት በመድረክ ላይ ተሰልፎ ለሕዝብ የማቅረብ አገልግሎት የጸጋ ስጦታ ሆኖ ሲሰጥ አናይም። በእግዚአብሔር ቃል የምናገኘው ነገር ቢኖር «ስትሰበሰቡ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ለእያንዳንዱ ትምህርት አለው ...» የሚል ነው (1ቆሮ.14፡26)፤ ስለሆነም ለአምልኮ በምንሰበሰብበት ጊዜ መዝሙር በልባቸው ያላቸው ሰዎች መዝሙሩን መዘመር ሲጀምሩ አብረናቸው እንዘምራለን። ለዚህም አዳዲስ የመዝሙር ቅኔያትን ሊቀኙ የሚችሉ ወገኖችን ጌታ ለራሱ ያስነሳል፤ እነዚህም ወገኖች መዝሙራቸውን በአካል እየተገኙ ወይም በካሴት እያባዙ ሊያስጠኑን ይችላሉ፤ ከዚህ አንጻር መዝሙርን መቀኘት ወይም አዳዲስ መዝሙሮችን ማበርከት ከጸጋ ስጦታዎች ሊመደብ የሚችል አገልግሎት ነው። በመድረክ ላይ ተሰልፎ ለሕዝብ ማቅረብ ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደ ጸጋ ስጦታ ሊወሰድ የሚገባ አይደለም፤ በብሉይ ኪዳንም ቢሆን የነበሩት መዘምራን በመድረክ ላይ ቆመው ፊታቸውን ወደ ሕዝብ አዙረው ለሕዝብ የአምልኮ መዝሙርን የሚያቀርቡ አልነበሩም፤ ክፍለ ዘመኑ ያለፈበት ያ የብሉይ ኪዳን አገልግሎት እንኳ መዘምራኑ መዝሙራቸውን ከሕዝቡ ጋር ወደ እግዚአብሔር የሚዘምሩ ነበሩ እንጂ ወደ ሕዝቡ የሚዘምሩና በጉባኤ ላይ የመድረክ መዝሙር የሚያቀርቡ አልነበሩም፤ ስለሆነም የመዘምራን ቡድንን ማደራጀቱ ከብሉይ ኪዳን የመዘምራን አገልግሎት ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ጥረት ቢሆንም በመድረክ ተሰልፎ ለሕዝብ ማቅረቡ ግን ከዓለማውያን የተውኔት ወይም የኪነት መድረክ የተወሰደ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም። በተጨማሪም መዘምራን በመድረክ ከመቆማቸውም ሌላ «የሶሎ ዘማሪ» የሚባሉ ግለሰቦችም በየመድረኩ እየቆሙ መዝሙር የሚያቀርቡበት ሥርዓትም በብዛት ይታያል። ይህም እንዲሁ በብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳንም ፈጽሞ የማይገኝ አለማዊ ስልትን የተከተለ ሥርዓት ነው። በዓለማዊነት ተጽዕኖ ሥር የወደቀ አምልኮ ደግሞ ለእግዚአብሔር አይስማማውም። በመሠረቱ አማኞች እንደ ቤተክርስቲያን ለአምልኮ በሚሰበሰቡ ጊዜ የመሰባሰባቸው ምክንያት መንፈስ የሆነውን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ለማምለክ ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፤ የቤተክርስቲያን አምልኮ ሁሉም አማኞች ወደ እግዚአብሔር የሚዘምሩበት ጊዜ ነው እንጂ የተወሰኑ መዘምራን ሲዘምሩ የሚደመጡበት ጊዜ አይደለም። አዳዲስ መዝሙሮችን ለማጥናት ሲፈለግ ግን ያን የምናደርገው በአምልኮ ጊዜ ሳይሆን መዝሙሮችን ለማጥናት ተብሎ በተመደበ ጊዜ በመገኘት አልያም በየካሴቱ በቤት ውስጥ በማድመጥ ሊሆን ይችላል። በአምልኮ ጊዜ ግን አንዱ ያመጣውን መዝሙር ሁሉም አማኝ በአንድ ልብ ሆኖ በመንፈስ መዘመር አለበት። መንፈስ ቅዱስም ይህን አምልኮ የተስማማና የሰመረ አምልኮ ያደርገዋል።

  1. የተለዩ አልባሳትን በመልበስ ማገልገል

በአምልኮ ጉባኤ ጊዜ ሁላችንም በክርስቶስ አካል ውስጥ ባለንበት የብልትነት ስፍራችን ሆነን በአንድ መንፈስ ልናመልክ ይገባናል። አንድ ብልት ከሌላው ብልት አይበልጥም፤ አንድ ብልትም ከሌላው አያንስም። የብልቶች ሁሉ ራስ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ በመሆኑም ከኢየሱስ በቀር እኛን በመወከል በእግዚአብሔር ፊት ሊቀርብ የሚችል ማንም የለም፤ በመካከላችን የሚያገለግሉ ሰዎች በአምልኮ ጊዜ እንደማንኛውም ብልት አብረው ያመልካሉ እንጂ አምልኮውን ሊመሩም ሆነ ጉባዔውን በእግዚአብሔር ፊት ሊወክሉ አይችሉም። ከዚህም የተነሣ ለየት ብለው እንዲታዩ የሚያደርጋቸውን ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ የለባቸውም።

በአምልኮ ጉባዔ ጊዜ «አስመላኪዎች» የሚባሉትም ሆኑ «ቀዳስያን» ተብለው የሚታወቁት ሰዎች እና «መዘምራን» ተብለው የሚመደቡት ሰዎች የተለዩ አልባሳትን ለብሰው እንዲያገለግሉ ማድረግ ከሕዝቡ ለየት ብለው እንዲታዩ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ ነው። ይህም የተለዩ አልባሳትን ለብሶ የተለየ የአምልኮ አገልግሎትን መፈጸም በዘመናችን በብዙ ቦታዎች የሚታይ ቢሆንም የተቀዳው ከአዲስ ኪዳን ሳይሆን ያው የተለዩ ካህናትና ሊቃነ ካህናት መሥዋዕትን ያቀርቡበትና የተለዩ መዘምራን ያገለግሉበት ከነበረው ከብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት ነው። በብሉይ ኪዳን በቤተመቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ሁሉ የሚለብሱት የተለዩ አልባሳት እንዲኖራቸው ታዝዟል። ለምሳሌ አሮንና ልጆቹ (ሊቀ ካህኑና ካህናቱ) የሚለብሷቸው የተቀደሱ ልብሶች በዘጸአት 28 ተገልጸዋል። እነርሱም የደረት ኪስ፣ ኤፉድ፣ ቀሚስ፣ ዝንጉርጉር ሸሚዝም፣ መጠምጠሚያ እና መታጠቂያ ናቸው (ዘጸ.28፡1-5)፤ እንዲሁም ቆቦቹንና የተቀደሰውን አክሊልም ያደርጉ ነበር (ዘጸ.28፡40፤ 29፡6)፤ ከሊቀካህኑና ከካህናቱም ሌላ በመቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ሁሉ የሚለብሷቸው አልባሳት ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም አጠቃሎ ሲገልጥ «በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፣ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፣ የልጆቹንም ልብሶች» ያደርጉ ዘንድ እንደታዘዙ ይገልጻል (ዘጸ.35፡19)፤ ሆኖም ከክህነትና ከመቅደስ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የተሰጠው ይህ የአልባሳት ሕግ ከክህነቱና ከመቅደሱ አገልግሎት ጋር አብሮ ቀርቷል፤ በዘመነ ሐዋርያት የተለዩ አልባሳት እየለበሱ አምልኮን የሚመሩ ሰዎች አልነበሩም፤ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን ከታሪክ እንደምንረዳው የብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮን በቤተክርስቲያን ውስጥ አንዳንዶች እያስገቡ ሲመጡ በአምልኮ ጊዜ ከሕዝቡ ተለይተው ካህናት የሚባሉ መሪዎችን ከማቆም ጀምሮ እነዚሁ መሪዎች የተለዩ አልባሳትንም እንዲለብሱ ማድረግ ተጀመረ። ሆኖም አስቀድሞ እንዳየነው አማንያን ሁሉ መንፈሳዊ መሥዋዕትን የሚያቀርቡ ካህናት ናቸው፤ ስለሆነም የተወሰኑ ሰዎችን ከሌሎች የሚለይ የክብርና የጌጥ ልብስ በአዲስ ኪዳን አማኞች ዘንድ ፈጽሞ ሊኖር አይገባም።

በአንድ በኩል «ካህናት» ወይም «ቄሶች» እየተባሉ በሌላ በኩል ደግሞ «አስመላኪ» እየተባሉ የሚጠሩ የተለዩ ሰዎች ከሕዝብ ተለይተው የሚለብሱት የተለየ ልብስ ካለ ግን ያው በብሉይ ኪዳን የአገልግሎት ሥርዓት ሥር መውደቅ ነው። ከሕዝብ የተለዩ መዘምራን በሚቆሙባቸው ጉባዔያት ውስጥም የመዘምራን ልብስ መዘምራኑን ከሕዝቡ ለይቶ ለማሳየት እያገለገለ ይገኛል።

በዘጸ.35፡19 ላይ እንደምናየው በብሉይ ኪዳን በመቅደስ የሚያገለግሉ ሁሉ የተለየ ልብስ ስለነበራቸው በቡድን ሚደራጁት «ሌዋውያን መዘምራንም» የተለየ ልብስ ሊኖራቸው እንደሚችል እንረዳለን፤ በአንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ በ2ዜና.20፡21 ላይ ኢዮሣፍጥ ከሞዓባውያንና ከአሞናውያን ጋር በተዋጋ ጊዜ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ያቆማቸው መዘምራን ጌጠኛ ልብስ ለብሰው እንደነበር ተገልጧል። በአዲስ ኪዳን ግን ከምእመናን መካከል የተለዩ መዘመራን ስለመኖራቸው የምናነበው ነገር እንደሌለ ሁሉ የተለየ የመዘምራን ልብስ ስለመኖሩም በአንድም ስፍራ አናነብም። በአዲስ ኪዳን የምእመናንም ሆነ ከምእመናን መካከል በጸጋ የሚገለጡ አገልጋዮች ሁሉም በአንድነት የሚለብሷቸው ልብሶች ምን ምን እንደሆኑ ተገልጧል፤ በሮሜ13፡14 እና በገላ.3፡27 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርሰቶስ ራሱ የአማኞች ልብስ እንደሆነ ሲነገረን በቈላ.3፡12-14 ደግሞ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትህትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን እንዲሁም የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን እንድንለብስ ታዝዘናል። ከዚህ በተረፈ እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን በአምልኮ ጊዜ አንዳንዶችን ከሕዝብ ለየት ብለው እንዲታዩ የሚያደርጉና የተቀደሱ የሚባሉ፣ ያሸበረቁና ጌጠኛ የሆኑ የጨርቅ አልባሳት እንዲኖሩን አልታዘዝንም። ስለሆነም ከብሉይ ኪዳን የአገልግሎት ሥርዓት ተጽዕኖ ተላቅቀን እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ብቻ ልናመልከው ይገባናል። በዓይናችን ፊት የሚታዩ ጌጠኛ አልባሳትን የለበሱ ሰዎች በሌሉበት ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ ብቻ እየተመራን ማምለክ መቻል አለብን።

  1. የሙዚቃ መሣሪያን በአምልኮ ጊዜ መጠቀም

«እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» (ዮሐ.4፡24) ለሚለው የጌታ መመሪያ የሚታዘዙና ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር «እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን ... ነን» የሚሉ (ፊልጵ.3፡3) አማኞች ለአምልኮ ሲሰበሰቡም ሆነ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲፈጽሙ ከመንፈሳዊ ነገር ውጪ ምንም ዓይነት ቊሳዊ ነገር ትዝ ሊላቸው አይችልም፤ ይሁንና በዘመናችን በመንፈስ እንጂ በፊደል ያልሆነውን የአዲስ ኪዳን አገልግሎት (2ቆሮ.3፡6) ካለመረዳት ወይም ለመንፈስ አገልግሎት ካለመታዘዝ የተነሣ ቊሳዊ ነገሮችን ለአምልኮ መገልገል በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ሆኗል፤ ሕዝብ እግዚአብሔርን ሊያመልክ እንደተሰበሰበ በሚነገርላቸው በብዙ ቦታዎች በአምልኮው ክፍለ ጊዜ አገልግሎት ላይ ከሚውሉት ቊሳዊ ነገሮች መካከል ዕጣን ማጤስ፣ የሻማ ወይም የጧፍ መብራትን ማብራት፣ የሙዚቃ መሣሪያን መጠቀም ጥቂቶቹ ናቸው። ከነዚህ ቊሳዊ ነገሮች መካከል በዚህ ጽሑፍ የምናጠናው የሙዚቃ መሣሪያን በተመለከተ ነው።

«የሙዚቃ መሣሪያ» የሚለው አነጋገር ቀለል ባለ አማርኛ በተተረጐመው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በዋናው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ግን «የዜማ ዕቃ» ተብሎ ተገልጧል፤ የዜማ ዕቃዎች ሰው የሚፈጥረውን ማንኛውንም ዜማ ተከትለው የተለያየ ድምፅን ማውጣት የሚችሉ ከእንጨትና ከብረት፣ ከቆዳና ከጅማት እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ሊሠሩ የሚችሉ ቊሳዊ መሣሪያዎች ናቸው። እነዚህም የሙዚቃ መሣሪያዎች በየዘመናቱ እንደሰው ልጅ ሥልጣኔ ዕድገትን እያሳዩ መጥተው በዘመናችን በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ዘመናት የነበሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች በእጅ የሚሠሩና የዚያን የጥንት ዘመን ባህልና ሥልጣኔ የተከተሉ ነበሩ።ከአጠቃቀማቸውም አንጻር ለ3 ሊከፈሉ ይችላሉ።

እነርሱም፡-
1) አውታር ያላቸው መሣሪያዎች - ለምሳሌ ክራር፣ በገና
2) በትንፋሽ የሚሠሩ መሣሪያዎች - ለምሳሌ ዋሽንት፣ መለከት፣ እንቢልታ
3) ሲመቱ ድምፅ የሚያወጡ መሣሪያዎች - ለምሳሌ ከበሮ ጸናጽል ናቸው

እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች በተለያዩ ዓለማት ባሉ የበዓላት ሥርዓቶችና የአምልኮ ስፍራዎች ይዜምባቸው እንደነበርና በእስራኤላውያንም ዘንድ አገልግሎት እንደነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያን መሥራት የጀመሩት የቃየን ሰባተኛ ትውልድ የሆኑት የ«ዩባል» ዘሮች ነበሩ። ይህን በተመለከተ በዘፍ.4፡21 ላይ «... የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ» የሚል ቃልን እናነባለን። እነዚህ የዜማ ዕቃዎች ከጥንት ጀምሮ ዓለማዊ ወይም ምድራዊ ደስታን የሚገልጡ ዘፈኖችን ለማጀብ ያገለግሉ ነበር። ሶርያዊው ላባ ከድቶት በኮበለለው በያዕቆብ ላይ በደረሰበት ጊዜ ለያዕቆብ ከተናገራቸው ቃላት መካከል «ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኰበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርከኝም? ...» የሚል ቃል ይገኝበታል (ዘፍ.31፡27)። ሶርያዊው ላባ ጣዖትን የሚያመልክ ሰው ስለ ነበር (ቊ.3ዐ) ለያዕቆብ ሽኝት ቢያደርግለት ኖሮ ከበሮና በገናን ይጠቀም የነበረው በዚያው በአገሩ በነበረው አሕዛባዊ ዘፈን እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ዓይነት ከጥንት ጀምሮ በምድር ላይ የሰው ልጅ በዓለማዊ መንገድ ራሱን ለማስደሰት የሙዚቃ መሣሪያን ይገለገል ነበር። ነገሥታት በጦርነት ድል ካደረጉ በኋላ ሠራዊቱ በሙዚቃ መሣሪያዎች እየዘፈነ ደስታውን ይገልጥ ነበር (2ዜና.2ዐ፡27-28)። በተለያዩ ግብዣዎች ላይም ሰዎች እየሰከሩ በመሰንቆ፣ በበገና፣ በከበሮና በእምቢልታ ይዝናኑ ነበር (ኢሳ.5፡12)። እንዲሁም በአሕዛብ አገሮች በተለይም በባቢሎን እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች ለአምልኮተ ጣዖት ይውሉ ነበር (ዳን.3፡7)። የሙዚቃ መሣሪያዎች እግዚአብሔርን በማያመልከው ዓለም የተጀመሩና ለሰው ልጅ ዓመፃ እንዲሁም ለክፋት አሠራሩ የዋሉ ቢሆኑም በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያንም በአምልኮአቸው ውስጥ ይጠቀሙባቸው ነበር። ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተው የኤርትራን ባህር ከተሻገሩ በኋላ «በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ» እያሉ በዘመሩ ጊዜ የሙሴ እኅት ማርያም እና ሌሎችም ሴቶች «ከበሮ» ተጠቅመው እንደነበር ተመዝግቧል (ዘጸ.15፡2ዐ-21)። ከዚህ በኋላ ግን በምድረ በዳ ሲጓዙ አንዳንድ ነገሮችን ለሕዝብ ማወጅ ባስፈለገ ጊዜ «መለከት» ከመንፋት በቀር በማደሪያው ድንኳንም ሆነ በሌላ ስፍራ መዝሙርን በሙዚቃ መሣሪያ እንዳጀቡ አናነብም። ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላም በዘመነ መሳፍንት ሁሉ በሴሎ ይደረግ በነበረው አምልኮተ-እግዚአብሔር የሙዚቃ መሣሪያን ሲገለገሉ አንመለከትም። በሳሙኤል ዘመን በነበሩ የነቢያት ጉባዔ መካከል ግን የሙዚቃ መሣሪያዎች እናገኛለን (1ሳሙ.1ዐ፡5)። ከዚህም የምንረዳው በሌላው ዓለም ለተለያየ አገልግሎት ይውሉ የነበሩት እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች በእስራኤል ዘንድም እንደነበሩ ነው። ሳሙኤል በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቀብቶ ያነገሠውና እግዚአብሔር «እንደ ልቤ የሆነ» ይለው የነበረው የእሴይ ልጅ ዳዊት ከህፃንነቱ ጀምሮ በገናን ይደረድር የነበረ ከመሆኑም ሌላ (1ሳሙ.16፡18)፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች በእስራኤል ዘንድ ለመዝሙር አገልግሎት እንዲውሉ አድርጓል፤ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት በኮረብታው ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት ባመጣ ጊዜ እርሱና የእስራኤል ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር (2ሳሙ6፡5)። ከዚያ በኋላ ደግሞ ታቦቱ አቢዳራ በተባለ ሰው ቤት ለ3ወራት ያህል በቆየ ጊዜ ዳዊት በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ ሌዋውያን መዘምራንን በተደራጀ መንገድ አዋቀረ (1ዜና.15-24)። ከዚያም በመዘምራኑ እየተመሩ ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው በእግዚአብሔር ፊት እየዘለሉ በመዝፈን የእግዚአብሔርን ታቦት ዳዊት ወደተከላት ድንኳን አምጥተዋል (2ሳሙ.6፡12-15፤ 1ዜና.15፡25-28)። በእስራኤል ዘንድ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያን በተደራጀ መልክ መገልገል የተጀመረውም በዚህ ጊዜ ነው ለማለት ይቻላል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥም በጸናጽልና በበገና በመሰንቆም ይዘመር ነበር (1ዜና25፡6)። ሰሎሞን በሠራው ቤተመቅደስም በዳዊት ሥርዓት መሠረት በዜማ ዕቃ የሚዘምሩ ሌዋውያን ነበሩ (2ዜና.23፡13፤ 29፡25-28፤ 34፡12)። በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ በተለያዩ መዝሙራት እንደተገለጠው እግዚአብሔርን በበገናና በመሰንቆ፣ በዋሽንትና በእምቢልታ፣ በከበሮና በጸናጽል፣ እንዲሁም በመለከት፣ በዜማ ዕቃ ሁሉ ማመስገን መልካም መሆኑ ተገልጧል (መዝ.92፡1-3፤ 149፡3)፤ በተለይም በመዝ.150፡3-5 ላይ «...በመለከት ድምፅ አመስግኑት፣ በበገና በመሰንቆ አመስግኑት፣ በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት፤ ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት» የሚል ቃልን እናነባለን። ይሁን እንጂ እስራኤል በብዙ ክፋትና ዓመፅ ሆነው በዜማ ዕቃዎች ሲዘምሩለት እግዚአብሔር «የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም» በማለት ይናገራቸው ነበር (አሞጽ.5፡23)። እንዲሁም «... በመሰንቆ ድምፅ ለምትንጫጩ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ... ስለዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ» ይላቸዋል (አሞጽ.6፡5-6)።

እግዚአብሔር «ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ» ያላቸው እስራኤል (ዘጸ19፡5) የእግዚአብሔር ምድራዊ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን በሚታይና ቊሳዊ በሆነ መንገድ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር፤ ብሉይ ኪዳን የሚታይና የዚህ ዓለም የሆነ ቤተመቅደስ የነበረው ሲሆን በመቅደሱ ውስጥም የሚገኙ ልዩ ልዩ የተቀደሱ ዕቃዎች እና አልባሳት ሁሉ በአገልግሎት ላይ የሚውሉበት ጊዜ ነበር፤ በዚህ ዓይነት የዜማ ዕቃዎችም በአምልኮ ላይ መዋላቸው የዚያ ዘመን እና የዚያ ምድራዊ ሕዝብ ሥርዓተ አምልኮ ጠባይ ስለሆነ ተቀባይነት አግኝቷል። «በሥጋ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ» (1ቆሮ.1ዐ፡18) ተብሎ እንደተጻፈው በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር ይመለክ የነበረው «በሥጋ» ማለትም ሥጋዊ፣ ፊደላዊ፣ ቊሳዊና ምድራዊ በሆነ መንገድ ስለሆነ በጊዜው በዚህ ዓለም የነበሩትን የዜማ ዕቃዎች ለዝማሬ አገልግሎት መጠቀሙ ከነበረው የአምልኮ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነበር።

በመንፈስ እንጂ በፊደል በማይሆነው በአዲስ ኪዳን አገልግሎት ግን በአምልኮ ጊዜ የሙዚቃ መሣሪዎች (የዜማ ዕቃዎች) መዝሙርን ሲያጅቡ አንመለከትም። በአዲስ ኪዳን መዝሙር የሚዘመረው በመንፈስ እና በአእምሮ ነው። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ ሲገልጥ «በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ» ብሏል (1ቆሮ14፡15)፤ በዝማሬ ጊዜም መንፈስ እንዲሞላብን ያስፈልጋል እንጂ(ኤፌ5፡18-19) በሙዚቃ መሣሪያ ድምፅ ልንሞላ አይገባንም። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በጉባዔ አምልኮ ጊዜ በሙዚቃ መሣሪያ መገልገል እንደሚገባ የተነገረ ወይም አማኞች በአምልኮአቸው ላይ የሙዚቃ መሣሪያን ሲገለገሉ የሚያሳይ ምንም ቃል የለም።

በመንፈስና በእውነት ሊፈጸም ለሚገባው የአዲስ ኪዳን አምልኮ ትኲ ረት ሲነፈገው በ«ምን አለበት?» የሚለመዱ የሰው ሥርዓቶች አማኞችን እየወረሱ ይሄዳሉ። የሰው ዝንባሌ ምን ጊዜም ቢሆን ለሥጋው ደስ የሚለውን እና በዚሁ በምድር ላይ በጉባዔ መካከል በዓይን የሚታይ፣ በጆሮ የሚሰማና ድምቀትን ሊያስገኝ የሚችለውን ነገር ለመቀበል ያጋደለ መሆኑ ከሁላችንም የተሰወረ አይደለም። ይህንን ሥጋዊ ስሜታችንን ለማርካት ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቀዳሚ ድርሻ አላቸው። ስለዚህ ለሥጋዊ ስሜቱ ቅድሚያ የሚሰጥ ክርስቲያን ሰማያዊና መንፈሳዊ ይዘት ካለው ከአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሙዚቃ መሣሪያ የሚናገር ጥቅስ ሲያጣ ምድራዊና ሥጋዊ ወይም ፊደላዊ ይዘት ወደ ነበረው ወደ ብሉይ ኪዳን በመሄድ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ለመጠቀም መፈለጉ አይቀሬ ነው። ይሁን እንጂ ምን ጊዜም ቢሆን ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር በብሉይ ኪዳን የተነገሩ ነገሮች ሁሉ በአዲስ ኪዳን ላሉት ሰማያዊ ነገሮች ምሳሌና ጥላ መሆናቸውን ነው(ዕብ8፡5፤ 9፡1ዐ፤ 1ዐ፡1)። በብሉይ ኪዳን የዜማ ዕቃዎች በሚገባ ተቃኝተው አገልግሎት ላይ ሲውሉ በዚህ በፍጥረታዊው ዓለም የደመቀና የተስማማ የዝማሬ ዜማን እንደሚያወጡ ሁሉ በአዲስ ኪዳን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያንን አምልኮ በመንፈሳዊ መንገድ የተጣጣመና የተስማማ ያደርገዋል። ስለሆነም የሙዚቃ መሣሪያ የሰውን ስሜት በመቆጣጠር የመዝሙሩን ዜማ በመምራት፣ በማስማማት እና በማድመቅ በኩል ይሠራ የነበረውን ሥራ ዛሬ በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ የአማኞችን ሁለንተና ማለት ሥጋን፣ ነፍስንና መንፈስን እየተቆጣጠረ አምልኮአቸውን በመምራት ይሠራዋል። ከዚህም የተነሣ የዜማ ዕቃዎችን በቊሳዊ አካልነታቸው እንዳሉ አምጥተን በሁለንተናው መንፈሳዊ ይዘት ብቻ ባለው የአዲስ ኪዳን አምልኮ ውስጥ ለመጠቀም መሞከር ሊቀላቀል የማይችለውን የሁለቱን ኪዳናት አምልኮ መቀላቀል ነው። የዜማ ዕቃዎች በዝማሬ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚናገሩ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችንም ስናነብ ክርስቶስ ኢየሱስ እኛን አማኞችን (ቤተክርስቲያኑን) እንደ ዘማሪው እንደ ንጉሥ ዳዊት በገና እንደሚቃኘንና እንደሚደረድረን የተስማማ ቃልና ዜማ ያለው ውብ የሆነ ዝማሬን እናወጣ ዘንድ በመንፈስ እንደሚመራን ልናሰላስል ይገባናል እንጂ ቊሳዊ የሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ድምፅ ሊታሰበን አይገባም። የአዲስ ኪዳን አማኝ ብሉይ ኪዳንን ሲያነብ ምን ጊዜም ቢሆን በፊደላዊ ንባቡ ሳይሆን በመንፈሳዊ ትርጉሙ ላይ ተመሥርቶ ሊሆን ይገባል። ፊደላዊ ንባቡ በጊዜው የነበረውን የብሉይ ኪዳንን እምነትና ትምህርት ለመረዳት ከማስቻል አልፎ በአዲስ ኪዳን ውስጥ መመሪያ ሊሆን አይችልም፤ ስለሆነም «ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ፊደሉን ትተን ሕይወትን በሚሰጠው መንፈስ በሆነው የአዲስ ኪዳን ሐሳብ ላይ ልናተኲር ይገባል (2ቆሮ.3፡6)።

በመንፈስና በእውነት ሊፈጸም በሚገባው የአዲስ ኪዳን አምልኮ ውስጥ ቊሳዊና ፊደላዊ ወይም ፍጥረታዊ የሆነ ነገርን መቀላቀል ባዕድ ነገርን ማስገባት እንደሆነ በዳግመኛ ልደት ከመንፈስ የተወለዱ ሁሉ ሊረዱት ይችላሉ፤ ምክንያቱም ፍጥረታዊ ነገር መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔርን ከሚያመልከው መንፈሳቸው ጋር ሊጣጣም አይችልምና ነው፤ ይሁን እንጂ የመንፈስ አምልኮ ቸል በተባለበትና አፍአዊ አምልኮ በሰለጠነበት የክርስትና ዓለም ለዚህ ነገር ትኲ ረት አይሰጠውም፤ ይልቁንም በሙዚቃ መሣሪያ እግዚአብሔርን ማምለክ ከመንፈስ አምልኮ ጋር ሊቃረን እንደማይችል ተደርጎ ይነገራል። ከሰው አመለካከት ይልቅ ለእግዚአብሔር ቃልና ለእግዚአብሔር ፍላጎት የሚወግኑ ግን ከአዲስ ኪዳን ጋር የተያያዘውን የእግዚአብሔርን እውነት ሊስቱት አይችሉም፤ ሆኖም ለብዙ ዓመታት ምንም ሳያስተውሉት ቆይተው ይህንን እውነት በሚሰሙ ጊዜ ግራ ለሚጋቡና ለሚደናገጡ ለአንዳንድ የዋሃን አማኞች እንዲረዳ በማሰብ በዚህ ዙሪያ ሊቀርቡ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሣት እንደ እግዚአብሔር ቃል ማብራራታችንን እንቀጥላለን።

በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያት (ማቴ.26፡3ዐ፤ ማር.14፡25) መዝሙር እንደዘመሩ ተመዝግቧል፤ በኤፌ.5፡19-20፤ በቈላ.3፡16-17 እና በያዕ.5፡13 ስለ መዝሙር የተጻፉ መመሪያዎችን እናገኛለን፤ በዜማ መሣሪያ እንድንዘምር የሚገልጽም ሆነ የሚጠቁም ምንም ዓይነት ቃል ግን የለም። ሆኖም በ1ቆሮ.14፡7 ላይ «ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይም በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል?» የሚለው ቃልስ እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል። በዚህ ቅጥስ ውስጥ «መዝሙር» የሚለው ቃል በግሪኩና በሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች «ዜማ» የሚል ነው። ከአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከልም በቀላል አማርኛ እና በአዲሱ መደበኛ ትርጉም «ድምፅ»፣ «ዜማ» የሚሉ ቃላትን ሲጠቀም የግእዙ አዲስ ኪዳንም «ተውኔት» የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተገለጸው ሐሳብ «የድምፁን ልዩነት ካልገለጠ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው ዜማ(ድምፅ) እንዴት ይታወቃል?» የሚል ነው። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ላይ «በልሳን መናገር» ትርጉሙ ካልታወቀ ጥቅም እንደሌለው ለማስረዳት የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚያወጡትን ድምፅ ወይም ዜማ በማብራሪያነት ይጠቀማል፤ ስለዚህ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ «መዝሙር» የሚል ቃል ቢጠቀምም በአምልኮ ጊዜ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የምስጋና መዝሙር አለመሆኑን ማስተዋል ይገባል። በሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ የሚዜም ማንኛውም ዜማ፣ ዓለማዊም እንኳ ቢሆን፣ መዝሙር ብሎ የመጥራት ልማድ መኖሩን መዘንጋት የለብንም፤ ምሳሌውም በዓለም ከሚከናወን የሙዚቃ ሥነ-ሥርዓት የተወሰደ መሆኑን የምንረዳው ቀጥሎ ባለው በቊ.8. ላይ ነው። በዚህ ቊጥር ላይ «ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?» ይላል። ስለሆነም ምሳሌው በዚያ ጊዜ ከነበረ የክርስቲያኖች አምልኮ ላይ የተወሰደ ነው ለማለት አይቻልም፤ የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን በአምልኮ ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያን ፈጽሞ ተገልግላ አታውቅም። የንባቡ ዋና ይዘትም አማኞች ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን የምስጋና መዝሙር በዋሽንትና በክራር እንደሚያጅቡ አያሳይም፤ ነገር ግን በልሳን የተነገረ ቃል ካልተተረጐመ እንደማይጠቅም ለማብራራት በምሳሌነት የቀረበ አገላለጽ ብቻ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ውስጥ የብሉይ ኪዳን የዜማ መሣሪያዎች ከዝማሬ ጋር መገለጻቸው በአዲስ ኪዳንም ቢሆን በሙዚቃ መሣሪያ እግዚአብሔርን ማምለክ እንደምንችል አያስረዳምን? የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይችላል። በእርግጥ በራእይ5፡8 እና 15፡2 «በገና» ይዘው የሚዘምሩ ቅዱሳንን እንመለከታለን። ሆኖም ይህ በራእይ የታየ ነገር ነው እንጂ በምድር ላይ ወይም በሰማይ ላይ በተግባር እየተፈጸመ የነበረ ነገር አይደለም። እንዲያውም የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በራእይ የተገለጠ የትንቢት ቃልን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ተገልጧል(ራእ.1፡1-3፤ 22፡18)። ስለሆነም እነዚህ በገና ይዘው የሚዘምሩት ቅዱሳን ወደ ፊት በሚመጣው በታላቁ መከራ ጊዜ ከአይሁድ ወገን በጌታ የሚያምኑ ቅዱሳንን ያመለክታሉ። በዚህ ራእይ ላይ ሲዘምሩ የታዩትም በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ነው። ለምሳሌ ራእ.5፡8ን ስንመለከት «እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ» ይላል። እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው እነዚህ ዘማሪዎች አዲሱን ቅኔ ሲዘምሩ የያዙት ነገር በገና ብቻ ሳይሆን ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃም ጭምር እንደሆነ ነው። ከዚህ ጥቅስ በመነሣት በአዲስ ኪዳን አምልኮ ውስጥ «ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ» መያዝ አለብን እንደማንል ሁሉ በገናንና ሌሎችንም የሙዚቃ መሣሪያዎችን መገልገል አለብን ማለት አንችልም፤ ነገር ግን በብሉይ ኪዳን የአገልግሎት ዕቃዎች ምሳሌነት የታየ ራእይ መሆኑን በመገንዘብ በገናውም ሆነ ዕጣን የሞላበት የወርቅ ዕቃ ያላቸውን መንፈሳዊ ትርጉም መረዳት ይገባናል። በራእ.15፡2 ላይ እንደምናነበውም የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ የዘመሩት ድል ነሺዎች በታላቁ መከራ ወቅት በጌታ የሚያምኑትን አይሁድ የሚያመለክቱ ሲሆን በዚህ ራእይ ውስጥ በገና ይዘው መታየታቸውም አይሁድነታቸውን ከማመልከት በቀር ክርስቲያኖች በሙዚቃ መሣሪያ እንዲያመልኩ የማስረዳት ዓላማ የለውም። ከዚህም ጋር አብሮ የታየው «የብርጭቆ ባሕር» እንዲሁም «አውሬው» ትርጉም የሚያስፈልገው እንደ ሆነ ሁሉ በገናውም የሚያመለክተው የራሱ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው ራእይን የሚያጠና ሁሉ ሊያሰምርበት ይገባል።

ሰይጣን ሰዎችን ወደ ዝሙትና ወደ ጣዖት አምልኮ የሚመሩ ዘፈኖችን የሚያዘፍነው የሙዚቃ መሣሪያን በመጠቀም ነው፤ ብዙውን ጊዜ የሰውን ሥጋዊ ስሜት የሚቆጣጠረውና ለመንፈስ ቅዱስ ስፍራ እንዳይኖር የሚያደርገውም በዚሁ በሙዚቃ መሣሪያ ነው። ሆኖም የሙዚቃ መሣሪያ ከሰይጣን ውድቀትና ከሰው ልጆችም ውድቀት በኋላ ሳይሆን ከሰይጣን ውድቀት በፊት እንደነበረ በኢሳ.14፡11 ላይ የተጻፈው «ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ» የሚለው ቃል እና በሕዝ.28፡13 ላይ የምናነበው «...የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህ ቀን ተዘጋጅተው ነበር» የሚለው ቃል አያስረዳምን? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል። የቅዱሳት መጻሕፍትን አጻጻፍ ባሕርይ በማስተዋል ስናጠና የጥያቄውን ምላሽ ለማግኘት አስቸጋሪ አይሆንም። «አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ» ተብሎ በኢሳ.14፡12 ላይ የተነገረው ቃል እና «አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ» ተብሎ በሕዝ.28፡14 ላይ የተነገረው ቃል በንባቡ ውስጥ ቀድሞ በክብር ስለነበረውና በኋላ ስለወደቀው መልአክ ማለትም ስለ ሰይጣን እንድናስብ ያደርገናል፤ በእርግጥ ኢሳይያስ እየተናገረ ያለው ስለ ባቢሎን ንጉሥ ውድቀት ነው (ኢሳ.14፡4)፤ ሕዝቅኤል ደግሞ የተናገረው ስለጢሮስ ንጉሥ ነው (ሕዝ.28፡12)፤ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ነቢያት የእነዚህን ሁለት ነገሥታት ውድቀት ልክ እንደ ወደቀው መልአክ ውድቀት አድርገው ያቀርቡታል፤ ይህም ማለት የወደቀውን መልአክ አወዳደቅ ለባቢሎን ንጉሥና ለጢሮስ ንጉሥ አወዳደቅ ምሳሌ አድርገው በማቅረብ ገልጸውታል። ስለዚህ በምሳሌያዊ አቀራረብ ውስጥ ዋናው ታሪክ እና ምሳሌው የተመሳሰሉበትን ነገር መለየት ያስፈልጋል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ነገሥታቱና ሰይጣን የተነጻጸሩት (የተመሳሰሉት) በውድቀታቸው ነው፤ ስለዚህ በሁሉም ዝርዝር ገለጻ ውስጥ የተነገሩትን ነገሮች የነገሥታቱን ለምሳሌው ማለትም ለወደቀው መልአክ መስጠት አንችልም። ለምሳሌ በኢሳ.14 ውስጥ ከቊ.9 ብንጀምር «... ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም የምድር ታላላቆች ሁሉ ለአንተ አንቀሳቀሰች፣ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ በዙፋኖቻቸው አስነሣች። እነዚህ ሁሉ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በታችህም ብል ተነጥፏል፤ ትልም መደረቢያህ ሆኗል» የሚለው ቃል ሰይጣንን ሊመለከት አይችልም፤ ምክንያቱም እዚህ ላይ ወደ ሲኦል የወረደውን የሚያናገሩት ቀደም ሲል የሞቱት የአሕዛብ ነገሥታት ናቸው፤ ከሰይጣን በፊት ግን የወደቁ መላእክት የሉም። «ወደ ሲኦል ወረደ» የተባለውም «የበገናው ድምፅ» ብቻ ሳይሆን «ጌጡም» ነው። ሰይጣን ደግሞ ከውድቀቱ በፊት በባሕርዩ የከበረ መልአክ ስለነበረ እንደ ሰው ጌጣጌጥ ሊኖረው አይችልም፤ እንዲሁም ሰይጣን መንፈስ ስለሆነ «ብልና ትል» የሚበሉት አይደለም፤ ደግሞም ሊሞት የሚችል አይደለም። ስለዚህ አባባሉ በቀጥታ የሚመለከተው ምሳሌውን ሳይሆን ውድቀቱ እየተነገረለት ያለውን የባቢሎን ንጉሥን ነው። የባቢሎን ንጉሥ ወደ ሲኦል ሲወርድ ወይም ሲሞት «ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል ትልም መደረቢያህ ሆኖአል»፣ ተብሎ ሊነገርለት የሚችል ነው (ቊ.11)፤ «ሰው» ነውና (ቊ.17)። ስለዚህ በቊ.11 ላይ «የበገናህ ድምፅ» የሚለው የባቢሎን ንጉሥ ከመውደቁ በፊት የነበረውን የበገና ድምፅ ያሳያል እንጂ (ዳን.3፡7) ሰይጣን ከመውደቁ በፊት የበገና ድምፅ እንደነበረ አያስረዳም።

በሕዝ.28፡13 «የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ» የሚለውም ቀጥታ የጢሮስን ንጉሥ የሚመለከት ነው እንጂ ሰይጣንን የሚመለከት አይደለም፤ ምክንያቱም ወደ ኋላ በቊ.4 ላይ «በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጥግናን ለራስህ አግኝተሃል፤ ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል» የሚል ቃል ስናነብ ወደፊት በቊ.16 ላይ «በንግድህም ብዛት ግፍ በውስጥህ ሞላ»፣ በቊ.8 ላይ ደግሞ «በበደልህም ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከስህ» ይላል።በእነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ የተገለጡት «የወርቅና የብር በግምጃ ቤት ውስጥ መሰብሰብ»፣ «የንግድ ብዛትም መኖር» የወደቀው መልአክ ባሕርያት አይደሉም። እንደዚሁም «የከበሮና የእንቢልታ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ» የሚለው የወደቀውን መልአክ የሚገልጽ አይደለም። የጢሮስ ንጉሥ ከመውደቁ በፊት በከበሮና በእንቢልታ የነበረውን ክብርና ደስታ ለማስታወስና በኋላም እንዴት እንደሚወድቅ የሚገልጽ ነው።

በመሠረቱ በገና በእንጨትና በክር የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። ከበሮና እንቢልታም ከእንጨትና ከቆዳ የሚሠሩ ናቸው። በመሆኑም ሰይጣን ከመውደቁ በፊት መናፍስት በሆኑ መላእክት መካከል ይህ ቊሳዊ መሣሪያ እንዴት ሊኖር ይችላል? ከምድር ከሚገኙ ነገሮች የሚሠራ ዕቃ ሊኖር የሚችለው በምድር ላይ በሰው መካከል ነው እንጂ በሰማይ ባሉ መላእክት መካከል አይደለም። ቀደም ሲል እንደተገለጠው የሙዚቃ መሣሪያን መሥራት የጀመረው ከቃየል ትውልድ መካከል የሆነው የዩባል ዘር ነው (ዘፍ.4፡21)። ይህ በእግዚአብሔር ላይ ያመፀ ትውልድ የሠራቸውን እነዚህን የዜማ ዕቃዎች ሰይጣን የሰው ልጆችን የተለያየ ኃጢአት ለማሠራት ይጠቀምባቸዋል፤ በዘመናችን የተለያዩ የዘፈን ክለቦችን እና ዳንኪራ ቤቶችን ለፍጥረታዊ ሰው ማለትም እግዚአብሔርን ለማያመልከው ዓለም መስህብነት እንዲኖራቸው የሚያደርገው የሙዚቃ መሣሪያን በመጠቀም ነው፤ ሰይጣን የሰውን ልብና ስሜት ከሚሰልብባቸው መንገዶች ዋነኛው የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚያወጡት ድምፅ ነው።በተለይም በዘመናችን ካለው የቴክኖሎጂ ዕድገት አንፃር የሙዚቃ መሣሪያዎች እጅግ በተራቀቀ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ኃላፊና ጠፊ ረጋፊም የሆነውን የዚህችን ዓለም ደስታ የተጠናከረ ለማድረግ የሰው ልጅ ያለውን እውቀት ሁሉ በሙዚቃ መሣሪያዎች እድገትና መሻሻል ላይ አፍስሷል ማለት ይቻላል፤ ይህ የሙዚቃ እድገትም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን ዓመፀኝነትና የሚፈጽመውን ርኵሰት ከመግለጥ በቀር የተሟላና የሚያሳርፍ ዘላቂም የሆነ ደስታን ለዚህች ዓለም ሊያስገኝ አልቻለም፤ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ክፋቷን ከምትገልጠው ከዚህች ክፉ ዓለም የተጠሩ ሰዎች ደግሞ «የሙዚቃ መሣሪያን ለእግዚአብሔር ክብር እንጠቀምበት» በሚል ሰበብ ለሥጋዊነትና ለዓለማዊነት ያለውን የሰውን የሁል ጊዜም ዝንባሌ ሲገልጡ መታየቱ አስገራሚ ነው። «ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ» እያለ የሚናገር ሰው ለዓለማዊ ነገር ሕያው ሆኖ ሲኖር ከታየ ይህ ሰው ቀድሞውንም ቢሆን ለዓለም ነገር እንዳልሞተ መገንዘብ ይቻላል።

በእርግጥ አስቀድመን እንዳየነው ዘመኑም ሆነ ሥርዓተ አምልኮው ፊደላዊና ምድራዊ ጠባይ በነበረው በብሉይ ኪዳን ውስጥ እነዚህ የዜማ ዕቃዎች በዓለም የሰይጣን መሣሪያ ሆነው እያገለገሉም ቢሆን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአገልግሎት ላይ ውለዋል። በአዲስ ኪዳን ግን ፍጥረታዊና ቊሳዊ በሆነ ነገር እግዚአብሔር የሚመለክበት ዘመን አብቅቶ በመንፈስና በእውነት የሚመለክበት ዘመን በመምጣቱ የሙዚቃ መሣሪያዎች በአገልግሎት ላይ እንዲውሉ አልታዘዘም። አማኞች ያን የዓለም ነገር አምጥተው በጉባዔያቸው ላይ እንዲገለገሉበት፣ ምንም ዓይነት መመሪያ ካለመኖሩም ሌላ ይዘቱ መንፈሳዊ ብቻ ከሆነው የአምልኮአቸው ባሕርይ ጋርም ተቃራኒ ነው።

እግዚአብሔር የሚከብረው የመንፈስና የእውነት አምልኮ (ዮሐ.4፡23) ሲቀርብለት እንጂ በይዘቱ ሙሉ በሙሉ አፍአዊ(ውጫዊ) የሆነው የሙዚቃ አምልኮ ሲቀርብለት አይደለም። በሙዚቃ መሣሪያ ክብራቸው የሚገለጠው እንደ ባቢሎን ንጉሥና እንደ ጢሮስ ንጉሥ ያሉ የዚህ ዓለም ኃያላን ናቸው። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት እንደ ባቢሎንና እንደ ጢሮስ ነገሥታት የበገናቸው የከበሮአቸውና የእንቢልታቸው ድምፅ ወደ ሲኦል ይወርዳል። በሙዚቃ መሣሪያቸው ከፍ ያለ ድምፅ ታላቅነታቸውን ለማሳየት የሞከሩ ባቢሎናዊና ጢሮሳዊ ገጽታ ያላቸው የዚህ ዓለም ማኅበራት ሁሉ በታላቅ አወዳደቅ የሚወድቁበት የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን በቅርቡ ይመጣል። ሐሰተኛይቱንና ጋለሞታይቱን ቤተክርስቲያን የምትገልጠው የታላቂቱ ባቢሎን ፍርድ የተነገረበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል «... ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አትገኝም። በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እምቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቹ ውስጥ ከቶ አይገኝም ...» ይላል (ራእ.18፡21-22)።

የእግዚአብሔርን የልቡን መሻት ስንረዳና በዚያ መሠረት ልናመልከው ስንታዘዝ በሙዚቃ መሣሪያ የሚፈጸመውን አምልኮ ደጋግፈን ለማቆም የምናቀርባቸው ብቃት የሌላቸው ምክንያቶቻችን ሁሉ ሸሽተው ይጠፋሉ። የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው እንደ ድምፅ ማጉሊያ፣ ቴፕ ቪዲዮና ኦዲዮ ወዘተ ከተጠቀምን የሙዚቃ መሣሪያን ብንጠቀም ምን አለበት? የሚለው ምክንያትም በቀላሉ ሸሽተው ከሚሄዱት ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። ድምፅ ማጉሊያ የሚጠቅመው ወደ ሰው ለመናገር እንጂ ወደ እግዚአብሔር ለመናገር አይደለም። እግዚአብሔር «ድምፅዋ ሳይሰማ ከንፈርዋን ብቻ ታንቀሳቅስ የነበረችውን» የሐናን ጸሎት እንደሰማ «የልብን ዝማሬም» ቢሆን ይሰማል(ቈላ.3፡16)። ቴፕ፣ ቪዲዮ፣ ኦዲዮ አንድን ቃል ቀርፆ ለማቆየት የሚጠቅም እንጂ እግዚአብሔርን ለማምለክ ወይም ለማክበር የሚውል አይደለም፤ ከላይ ከተነሣው ጥያቄ አኳያ የሙዚቃ መሣሪያን መገልገል የተፈለገው ደግሞ በአምልኮ ላይ በመሆኑ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ሊነጻጸር የሚችል አይደለም፤ ስለዚህ በቀላሉ ሊፈርስ የሚችለውን ይህን ምክንያት በፍጥነት እናስወግድ፤ አንባብያን እዚህ ላይ ሊያስተውሉት የሚገባው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ቊሳዊ የሆነው የሙዚቃ መሣሪያ በመንፈስ አምልኮ ላይ ስፍራ እንደሌለው ለመግለፅ እንጂ በዓለም ያለውን ማናኛቸውንም የቴክኖሎጂ ዕድገት ለመቃወም እንዳልሆነ ነው።

በአምልኮ ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያን ለመጠቀም ያለንን ዝንባሌ በትንሹም ቢሆን ጠብቀን ለማቆየት የምናቀርበው የመጨረሻው አስተያየታችን ደግሞ «የሙዚቃ መሣሪያ እኮ የጉባዔ መዝሙርን ለማስማማት፣ ለማድመቅና አለማውያንን ለመሳብ ይጠቅማል» የሚል ነው። ይህ ምናልባት ከወንጌል ሥርጭት አገልግሎት አንጻር እንደ አንድ ጥሩ ሐሳብ ሊታይ ቢችልም በአምልኮ ጉባኤ ላይ የሙዚቃ መሣሪያን ለመጠቀም ግን መነሻ ሊሆን የሚችል አይደለም። ስለሆነም የአምልኮ ጉባኤና የወንጌል ስርጭት ጉባኤ ያላቸውን ልዩነት ምን ጊዜም ቢሆን መረዳት ያስፈልጋል፤ የአምልኮ ጉባኤ አማኞች በአጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚያካሂዱት መደበኛ ጉባኤ ሲሆን የወንጌል ስርጭት ጉባኤ ግን በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄድና ወንጌላውያን ለማያምኑ ሰዎች የመዳንን ወንጌል የሚሰብኩበት ጉባኤ ነው፤ በዚህ የወንጌል ስርጭት ጉባኤ ጊዜ ወንጌልን ለመስማት ለተሰበሰቡ ኢአማንያን የመዳን መልእክትን እና የንስሐ ጥሪን በዜማ ማስተላለፍ በሚፈለግበት ጊዜ አግባብነት እና ሥርዓት ባለው የሙዚቃ ስልት መጠቀም ነውር የለበትም። ንስሐና የኃጢአት ስርየትን የሚናገሩ መዝሙሮች በተስማማ የሙዚቃ ቅንብር ቃሉ እንዲሰማ ሆኖ ለማያምኑ ሰዎች ቢቀርቡላቸው ይህ ቢያንስ ቢያንስ ወንጌልን ሰምተው ለማያውቁ ኢአማንያን ወይም ዓለማውያን ሰዎች ወንጌል እንዲሰሙ መልካም አጋጣሚን ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ አኳያ በአምልኮ ጉባኤ ሳይሆን በወንጌል ስርጭት ጉባኤ ላይ በሙዚቃ መሣሪያ መዘመር የሚኰነን አይደለም። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ሰዎችን ወደ ጌታ ኢየሱስ የሚስበው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑ ምን ጊዜም ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባም። ጌታ ኢየሱስ ሲናገር «የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም» ብሏልና (ዮሐ.6፡44)።

ስለዚህ በአምልኮ ጉባኤ ጊዜ እግዚአብሔርን እንደልቡ መሻት እናምልክ፤ እኛ ደስ የሚያሰኘንን ሳይሆን እርሱ ደስ የሚለውን ለማድረግ እንታዘዝ። ለእኛ ደምቆ የሚታየንን ሳይሆን ለእግዚአብሔር የሚያረካውን ለማቅረብ እንፍቀድ፤ ፍጥረታዊና ቊሳዊ ከሆነ ነገር ተላቅቀን መንፈሳዊ በሆነ መንገድ ብቻ ወደ እግዚአብሔር በአምልኮ እንቅረብ። እግዚአብሔር ስሜታችን ሳይሆን ፈቃዱንና የልቡን ሐሳብ ብቻ እንድንከተል ይርዳን።

  1. በአምልኮ ላይ የሚታይ ያልሆነ እንቅስቃሴ

«መንፈሳዊ ሰው» ተብሎ በ1ቆሮ.2፡15 ላይ የተገለጠው አማኝ በቶሎ ሊረዳው እንደሚችለው መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔርን ልናመልክ በኢየሱስ ስም ተሰብስበን ወደፊቱ በምንቀርብ ጊዜ ሥጋችን ሙሉ በሙሉ በመንፈሳዊ ማንነታችን ቊጥጥር ሥር ሊሆን ይገባዋል። በሌላ ጊዜ እንደማንኛውም ሰው በዚህ ዓለም ስንኖር የቤተሰብ አስተዳደርን፣ ጤንነትን፣ ሥራን ... የሚመለከቱ ኃጢአት ባይሆኑም በባሕርያቸው ሥጋዊ (ምድራዊ) የሆኑ ነገሮችን ልናስብና በተገቢው መንገድ ተግባር ላይ ልናውላቸው እንችል ይሆናል፤ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ስንሰበሰብ ግን በሥጋ ፈቃድ ልንሆን አይገባም። ራሱን ለሥጋዊ ስሜቱ አሳልፎ የሰጠ ክርስቲያን ግን ይህን ስለማያስተውል በአምልኮ ጉባዔያት በተገኘ ቊጥር በውስጡ ታምቆ የነበረውን ሥጋዊ ስሜት ተገቢ ባልሆነ እንቅስቃሴ ሲገልጥ ይታያል በዚህም ያልሞቱት የአሮጌው ሰው ጠባዮች በመንፈሳዊ ጉባዔያት ላይ በመገለጥ የአዲሱን ሰው ትክክለኛ ገጽታ ለማበላሸት ሁል ጊዜም ይጥራሉ።

በየአምልኮ ጉባዔው በአብዛኛው እየታየ ያለውና «ይህም ያንስበታል» በሚል፣ መልካም በሚመስል ንግግር ተሸፍኖ እየተስፋፋ የሚገኘው ዳንኪራና ጭፈራ ቆም ተብሎ በእርጋታ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው። አንዳንድ ጊዜ በእልከኝነት እና በምን አለበት የሚቀርቡትን ክርክሮች ወደ ጐን ትተን ዝላዩንና ጭፈራውን በተመለከተ በቅንነትና በየዋህነት ወይም ባለማወቅ የሚቀርቡ አንዳንድ ምክንያቶችን በማንሣት እንደ እግዚአብሔር ቃል መመርመርና ትክክለኛውን እውነት ማቅረቡ ብዙዎችን ቆም ብለው እንዲያስቡበትና እንደ እግዚአብሔር ሰው ራሳቸውን እንዲመለከቱ ይረዳቸዋል ተብሎ ይታሰባል፤ ስለሆነም ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹን በመመርመርና እውነቱን በመግለጥ ቀጥሎ እንተነትናለን፡-

1ኛ. በአምልኮ ጊዜ መዝለልና መጨፈር ተገቢ እንደሆነ ያስረዳል ተብሎ በአብዛኛው የሚጠቀሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት እየዘለለ መዝፈኑ ነው። ይህ ታሪክ የሚገኘው በ2ሳሙ.6፡12-23 እና በ1ዜና.15፡25-29 ላይ ነው። በዚህ ክፍል ዳዊትና የእስራኤል ቤት ሁሉ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ክብር እንዳመጡ እናነባለን። ለዳዊት ያ ቀን ትልቅ የደስታ ቀን ነበር። ከዚህም የተነሣ ዳዊት የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር (2ሳሙ.6፡14)፤ ሚስቱ ሜልኮልም በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አይታ በልብዋ ናቀችው (2ሳሙ.6፡16)፤ «ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው!´ ለሚለው የንቀት ንግግሯም ዳዊት የሰጠው ምላሽ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን ዝቅ ከሚያደርግና ራሱን ከተወ ሰው የሚወጣ መልስ ነበር። «በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ። አሁንም ከሆንኩት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ በዓይንሽም ፊት እዋረዳለሁ፤ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ» የሚል ድንቅ መልስን ሰጣት (ቊ.22-23)። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሳለ ከተናቁ ሰዎች ጋር ክብሩን ትቶ እየዘለለ ለእግዚአብሔር መዝፈኑ ምን ያህል በአምላኩ ደስተኛ እንደሆነ እና ክብርንም ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሰጠ ያሳያል። በዚያ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰው እግዚአብሔርን የሚያከብርባቸው መንገዶች ሁሉ በዐይን የሚታዩ ሥነ ሥርዓቶች በመሆናቸው ያደረገው ሁሉ ከዘመኑ የእግዚአብሔር ሐሳብ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ነበር። ይህም ሆኖ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን የታየው ታቦቱን ከአሚናዳብ ቤት እስከ አቢዳራ ቤት፣ ከአቢዳራ ቤት እስከ ጽዮን ድረስ በሚያመጣበት ጊዜ ብቻ ነበር፤ በመንገድ ላይ ሲጓዙ በሕዝብ መካከል እግዚአብሔርን ያከበረበት ሁኔታ ነበር እንጂ በብሉይ ኪዳን የአምልኮ ስፍራ ማለትም በመገናኛው ድንኳን የተፈጸመ አልነበረም። ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በማደሪያው ድንኳንና በኋላ በተሠራው ቤተመቅደስ ውስጥ የተለያዩ መሥዋዕቶች እየቀረቡ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲከናወን ዝላይ እና ጭፈራ አልነበረም፤ ስለሆነም በብሉይ ኪዳንም ቢሆን በአምልኮ ላይ የእግዚአብሔር መዝሙር በተዘመረ ቊጥር ዳዊትም ሆነ ሌሎች እስራኤላውያን እንደመደበኛ ልምምድ ሁል ጊዜም ይዘልሉ እና ይጨፍሩ ነበር ማለት አይቻልም፤ ከዚህም የተነሣ በዚህ ዘመን እሑድ እሑድ ለአምልኮ በተሰበሰቡ የክርስቲያኖች ጉባዔያት እና በየቦታው በሚደረጉት የተለያዩ መንፈሳዊ ስብሰባዎች በዘመናዊ የሙዚቃ ስልት ታጅቦ ሲከናወን የምናየው ዝላይና ጭፈራ የሁል ጊዜም መደበኛ ልምምድ መኾኑ ልምምዱ እንኳን ከአዲስ ኪዳን አምልኮ ጋር ቀርቶ ከብሉይ ኪዳኑ አምልኮ ጋርም ፈጽሞ እንደማይገናኝ በግልጽ ያስረዳል፤ ስለሆነም የዳዊትን መዝለል ሽፋን ለማድረግ ቢሞከርም ዝላይና ጭፈራ ወደ አማኞች መካከል የአሮጌውን ሰው ጠባዮች ተከትሎ የገባው በዙሪያችን ካለው ክፉ ዓለም እንደሆነ ከአስተዋዮች አይሰወርም።

ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት የዘለለው የእግዚአብሔርን ታቦት በራሱ ከተማ ወዳዘጋጀለት ድንኳን ባመጣበት ዕለት ነበር። ደስታው ከታቦቱ መምጣት ጋር የተያያዘ ነው፤ ምክንያቱም ታቦት በብሉይ ኪዳን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የሚጠራና (2ሳሙ.6፡2) የእግዚአብሔርን በሕዝቡ መካከል መገኘት የሚያመለክት ነበር። በአቢዳራ ቤት ለ3 ወር ያህል ታቦቱ በተቀመጠ ጊዜም እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤት ባርኮ ነበር (ቊ.11)። ታዲያ ዳዊት ይህን ታቦት በታላቅ ክብር ከእስራኤል ቤት ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ራሱ ከተማ ሲያመጣ ዘለለ፤ በአዲስ ኪዳን ግን ከእንጨት ወይም ከድንጋይ ወይም ከሌላ ቊሳዊ ነገር የተሠራ «ታቦት» የለም፤ ሆኖም «ታቦት በአዲስ ኪዳን ቀርቷል» ብለው በሚያምኑ ሰዎች ዘንድ እንኳ ለአንድ ቀን ብቻ ታቦት አጅቦ የዘለለውን የዳዊትን ታሪክ በመጥቀስ በየእሑዱና በየጊዜው በቋሚነት የሚደረግ ዝላይና ጭፈራ በመካከላቸው መታየቱ አስገራሚ ነው። ዝላዩ ከዳዊት ከተወሰደ ታቦቱም ሆነ ዳዊት የተከለው ድንኳን፣ የተሠዋው የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት፣ ባጠቃላይ ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ባመጣበት በዚያን ቀን የተፈጸሙት ሌሎች ክንውኖች እንዳይፈጸሙስ ምን የሚያግድ ነገር ይኖራል? ለዝላዩና ለጭፈራው ሲሆን «ዳዊት ዘሏል» የሚለውን ጠቅሶ ታቦቱን ግን መተውም ሆነ ቀርቷል ማለት እርስ በእርስ የሚፋለስ ሐሳብ መኾኑ ሊታወቅ ይገባል። በእውነት የሚሰግዱ (የሚያመልኩ) አማኞች ግን ዘመኑ ካለፈበት ከብሉይ ኪዳን አምልኮ ምንም ነገር አይወስዱም፤ መምህራቸው ኢየሱስ እንደነገራቸው ያለምንም ቊሳዊና ሥጋዊ ሥርዓት በመንፈስና በእውነት ብቻ እግዚአብሔርን ያመልኩታል። ለእነርሱ ታቦቱም ሆነ የዳዊት መዝለል በዚያው ፊደላዊ ይዘት በነበረው በብሉይ ኪዳን ዘመን ብቻ እንዳገለገለ የሚታወቅ ነው።

እውነተኛ አማኞች ዳዊት ከምናምንቴዎች ጋር ሆኖ ሚስቱ ሜልኮል እስክትንቀው ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በሕዝብ መካከል እየዘለለ ከመዝፈኑ ታሪክ የሚማሩት ነገር አለ፤ ይኸውም ዳዊት ንጉሥ ሆኖ እያለ ከተራው ሕዝብ ጋር ራሱን ቈጥሮ በሙሉ ኃይሉ እየዘፈነና እየዘለለ ደስታውን መግለጡ እግዚአብሔርን ለማክበር ንጉሥነቱን አለማሰቡን ያሳያል፤ ክርስቲያንም በዚህ ዓለም ሲኖር ዓለም የምትሰጠውን የከበረ ስፍራና ሌሎች ስለእርሱ ያላቸውን አመለካከት ከግምት ሳያስገባ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ራሱን መቊጠር ይኖርበታል፤ ይህንንም የሚገልጠው በአምልኮ ሰዓት በመዝለል ሳይሆን ዕለት በዕለት በሚገጥመው ሁሉ በንግግርም ሆነ በተግባር እርሱ የጌታ ኢየሱስ መሆኑን ባለማወላወል በመግለጥ ነው። ከዚህ የዳዊት ታሪክ የምንማረው ይህንን መንፈሳዊ መልእክት ነው እንጂ በአምልኮ ላይ ፊደል በፊደል የሚታየውን ጭፈራና ዝላይ አይደለም። መዝለል ከመጠን በላይ መደሰትን የሚያሳይ የሰዎች ልማድ ነው። ዳዊትም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት የዘለለው በውስጡ የተሰማውን ታላቅ ደስታ ለመግለጥ ነው። ከዚህ ታሪክ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር መገኘት እጅግ ደስ ሊላቸው እንደሚገባ የሚያሳይ መልእክትንም ማግኘት ይቻላል። ታቦቱ በሕዝቡ መካከል መሆኑ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መገኘቱን እንደሚያሳይ ሁሉ ክርስቲያኖችም በኢየሱስ ስም ሲሰበሰቡ በመካከላቸው የእግዚአብሔር መገኘት ይኖራል። በዓይን የሚታይ ምንም ዓይነት ቊሳዊ ነገር በመካከላቸው ሳይኖር በኢየሱስ ስም ስለተሰበሰቡ ብቻ እግዚአብሔር በመካከላችን ነው ብለው በማመን በእጅጉ ደስ ይሰኛሉ፤ ሆኖም ይህንን ደስታቸውን የሚገልጡት በሚታይ የሥጋ ዝላይ አይደለም።

2ኛ. በብሉይ ኪዳኑ የዳዊት ዝላይ ላይ ተደግፎ መዝሙሮች በተዘመሩ ቊጥር ሲዘልና ሲጨፍር የኖረ ሰው ለአዲስ ኪዳኑ የመንፈስ አምልኮ ዳዊት በዝላይ መዝፈኑ በመረጃነት ሊጠቀስ እንደማይችል ሲገባው ከአዲስ ኪዳን ጥቅስ ማፈላለጉ አይቀርም፤ የንባቡ ይዘት ምንም ቢሆንም «መዝለል» የሚል ቃል በሚያገኝበት ሁሉ ላይ ዓይኑን በማሳረፍ ጭፈራውን የሚደግፍለት ጥቅስ ያፈላልጋል፤ ብዙ ስህተት የሚፈጠረው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ ዓይነት በማጥናት ነው። በፊት የግል መረዳትንና ፍላጐትን አስቀድሞ ለዚያ መረዳት ጥቅስ በማፈላለግ ማጥናት ቃልን ወደ ማጣመም ይመራል፤ በዚህ ዓይነት ዝላይና ጭፈራን ሊደግፉ ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱት የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች መካከል አንዱ ሉቃ.6፡23 ነው። ከቊ.22 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት «ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም። አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና» ይላል፤ ልብ ብሎ የሚያነብ ማንኛውም ሰው በዚህ ንባብ ውስጥ «ዝለሉ» የተባለው በአምልኮ ጊዜ እንዳልሆነ ይረዳል። ንባቡ አማኝ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በተጠላ፣ በተለየና በተነቀፈ ጊዜ በሰማይ ያለውን ታላቅ ዋጋ እያሰበ ደስ ሊሰኝ እንደሚገባው የሚያስረዳ ንባብ ነው። «ዝለሉም» የሚለው ቃል የተነገረው «ደስ ይበላችሁ» የሚለውን ቃል ተከትሎ ነው፤ በመሆኑም መዝለል እጅግ ታላቅ የሆነ ደስታን የሚገልጥ ነው፤ ከዚህ ተነሥተን ግን በየጊዜው በተጠላንና በተነቀፍን ቊጥር በየመንገዱና በየስፍራው ሁሉ በእግራችን ወደላይ እንዘላለን ማለት አይደለም። ቃሉም የተነገረው በጉባዔም ይሁን በየትኛውም ስፍራ ክርስቲያኖች እየዘመሩ የሚዘልሉበትና የሚጨፍሩበት መርህ እንዲሆን አይደለም። ስለሆነም ጥቅሱ ከአምልኮ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በስደት ጊዜም ቢሆን ዋጋችንን እያሰብን የምንገልጸውን ደስታ በመንፈሳዊ ዝላይ (ማለትም በሐሴት) እንጂ ፊደላዊ በሆነ የሥጋ ዝላይ የምናሳየው አለመሆኑን ማስተዋል ይገባል።

3ኛ. አካላዊ ውዝዋዜ በአምልኮ ላይ መታየቱ እግዚአብሔርን ሊያከብር ይችላል ከሚል የአመለካከት ቀንበር መላቀቅ ጥቂትም ቢሆን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ «ሥጋ እስከለበስን ድረስ በሥጋ የምናደርገው ዝላይና ጭፈራ መኖሩ ለእግዚአብሔር ክብር ከሆነ ምን ችግር አለው?» ሲባል እንሰማለን። ለዚህ አባባልም «በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ» የሚለው ቃል እንደማስረጃ የሚጠቀስበት ወቅት አለ (1ቆሮ.6፡2ዐ)፤ ይህም ከኋላ ያለውን ንባብ አያይዞ በማጥናት ካለመረዳት የተነሣ የሚጠቀስ እንደሆነ ማየት ይቻላል። ከቊ.18 ጀምሮ እንኳ ያለውን ስናነብ ሰው በገዛ ሥጋው ላይ ስለሚሠራው የዝሙት ኃጢአት የሚናገር ነው። የአማኞች ሥጋ ግን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነው፤ አማኞች የክርስቶስ ክቡር ደም ዋጋ ሆኖ የተከፈለባቸው ስለሆኑ የራሳቸው እንኳ አይደሉም፤ ስለሆነም በዚህ ለእግዚአብሔር ብቻ መኖሪያ በሆነው ሥጋቸው እግዚአብሔርን ሊያከብሩ ይገባል። ዝሙትን ቢፈጽሙ ግን የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሥጋቸውን ያረክሳሉ ያዋርዳሉ፤ ስለዚህ አማኞች በሥጋቸው እግዚአብሔርን የሚያከብሩት ራሳቸውን ከዝሙት በመጠበቅ ባጠቃላይ ሰውነትን ከሚያረክሱ የሥጋ ሥራዎች ተለይተው በቅድስና በመኖር ነው፤ ጥቅሱ የሚናገረው ይህንን ሆኖ እያለ «በዝላይና በጭፈራ እንዲሁም በማናቸውም ዓይነት ውዝዋዜ እግዚአብሔርን ማክበር ይቻላል» ለሚል የሰው ሐሳብ መጥቀሱ መጻሕፍትን ማጣመም እንደሆነ መረዳት ይገባል።

4ኛ. በጉባዔ አምልኮ ጊዜ ሥጋ በዓለም ሳለ የለመደውንና አሁን ያጣውን ዝላይና ጭፈራ (ዳንኪራ) እግዚአብሔርን በማክበር እያሳበበ እንደገና ለማግኘት ያስችለው ዘንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊና መንፈሳዊ ለማስመሰል የማያደርገው ጥረት የለም፤ በክርስትና ትምህርት ውስጥ ስለ መንፈሳዊው ነጻነት (አርነት) የተነገረውን እውነታ የሥጋ ነጻነትን ለማወጅ እንዲያስችል ተደርጎ ሲቀርብ ብዙ ጊዜ እናያለን፤ ከብሉይ ኪዳን «በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርህን ከአንገትህ እሰብራለሁ፤ እስራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም...» (ኤር.3ዐ፡8)፣ ከአዲስ ኪዳን ደግሞ «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ» (ገላ5፡1) የሚሉትና የመሳሰሉት ጥቅሶች «ሥጋ በነጻነት እንደሚፈልገው ሆኖ ማምለክ አለበት» የሚል ሐሳብን ለማስረዳት የሚጠቀሱበት መድረኮች መኖራቸው አስገራሚ ነው፤ እነዚህ ጥቅሶች በአምልኮ ጊዜ ሥጋ እንደፈለገው እንዲጨፍር ምንም ዓይነት ጭላንጭል ቀዳዳ የሚከፍቱ አይደሉም፤ በኤር.3ዐ፡8 ያለው በአሕዛብ ነገሥታት ይገዙ ለነበሩትና የባርነት ቀንበር ተጭኖአቸው ለነበሩ እስራኤላውያን የተነገረ የተስፋ ቃል ሲሆን በዚሁ ክፍል «ቀንበርህን ከአንገትህ እሰብራለሁ እስራትህን እበጥሳለሁ» የሚለው ቃልም «ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም» በሚለው ቃል በቀላሉ ሊብራራ ይችላል፤ በመሆኑም ቃሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ እስራኤል ከአሕዛብ የአገዛዝ ቀንበር ነጻ የሚወጡበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚያስረዳ ቃል ነው እንጂ በአምልኮ ላይ ሥጋ በነጻነት እንዲዘል የሚያስተምር አይደለም። በገላ.5፡1 ላይ ያለው ደግሞ ክርስቲያን ከሕግና ከኃጢአት ባርነት በክርስቶስ ነጻ መውጣቱን ይናገራል እንጂ በአምልኮ ላይ ሥጋ በነጻነት እንዲወራጭና እንዲዘል በር የሚከፍት ቃል አይደለም፤ ሥጋ በአምልኮ ላይ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ስፍራ በክርስትና የተገኘውን አርነት (ነጻነት) ተጠቅሞ (ምክንያት አድርጎ) ራሱን ሊገልጥ አይችልም። በዚሁ በገላ5፡13 ላይ «እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ» ተብሎ ተጽፏል። ስለሆነም የእግዚአብሔር ቃል ስለመንፈሳዊ አርነት የሚያስተምረንን እውነት ምክንያት አድርጎ የሥጋ አርነትን ማወጅ ትልቅ ስህተት ነው፤ በየአምልኮ ጉባዔው «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን ተብሎ እንደተጻፈ በነጻነት ሆነንና ተፈትተን ማምለክ ስለሚገባን ነቃ ነቃ በሉ»፣ «በእልልታ፣ በሆታ፣ ደስ እያለን እየዘለልን ሳንቆጥብ ጌታን እናከብረዋለን፤ ሃሌ ሉያ!» በሚሉ የማነቃቂያ ቃላት ከመድረክ የሚተላለፉ ቅስቀሳዎችና «ተነሡ፣ ተቀመጡ፣ አጠገብህ ያለውን እንዲህ ... በለው፤ እቀፈው፣ ጨብጠው፣...» የሚሉ አግባብ ያልሆኑ ማሳሰቢያዎች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ከሥጋ ስሜት የመነጩ የአሮጌው ሰው ባሕርያት እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን አርነትና መፈታት ከኃጢአት እና ከሕግ እንዲሁም የጌታ ከመሆናችን በፊት ከነበርንበት የተለያየ እስራት ስለመፈታትና፣ ነጻ ስለመውጣት ነው እንጂ በአምልኮ ላይ የሚታይ የሥጋ መወራጨትን ወይም ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴን አይደለም፤ እንዲያውም የአምልኮ ዝማሬዎች በሚዘመሩበት ወቅት መወዛወዝ፣ መዝለልና መጨፈር፣ እንዲሁም ወዲያና ወዲህ እየተሽከረከሩ የተለያዩ የዳንስ ትርዒቶችን ማሳየት ለአንድ አማኝ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን በዓለም እያለ በነበረበት በቀደመው እስራት ተመልሶ መታሠር ነው እንጂ መፈታት አይደለም።

በእርግጥ በአምልኮ ጊዜ ከተለየዩ ምድራዊ ሐሳቦች፣ ከሚያስቆዝሙና ልብን ከሚከፋፍሉ ዕለታዊ ጉዳዮች ነጻ መሆን ያስፈልጋል፤ በዚያ ክፍለ ጊዜ በልብ ላይ ፍጹም የሆነ ነጻነት ሊሰማንና በምንዘምርበት ጊዜም ሆነ በቃላት በምናመሰግንበት ጊዜ ድምፃችንን ለማውጣት የሚይዘንና የሚተናነቀን ስሜት ሊኖርብን አይገባም፤ ስለሆነም እንደእውነቱ ከሆነ ሊበጠስ የሚገባው እስራት የከበረውን የመንፈስና የእውነት አምልኮ አንቆ በመያዝ በውስጣችን የሚገኝ የሥጋ ስሜትና የተከፋፈለ ሐሳብ እንዲሁም በሥጋ ድካም የተፈጸመ የኃጢአት እስራት ነው፤ ይህ ደግሞ ሥጋን ወደ ጭፈራ የሚመራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ወደማለት የሚመራ ነው፤ አርነቱም በልባችን ላይ ሲፈስ ይሰማናል እንጂ ኢአማንያን እንደሚያደርጉት በውዝዋዜ አይገለጥም፤ ደስታቸውን እና ነጻነታቸውን እስኪያልባቸው ድረስ በመጨፈር እያዜሙ፣ በተለያየ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በማጀብ ሲገልጡ የሚታዩት ዓለማውያንና ጣዖት አምላኪዎች ናቸው፤ ይህም በአምልኮተ ሰይጣን ውስጥ የሚታየው ሥጋን እያስጨፈሩ፣ እያዘለሉና፣ እስኪደክመው ድረስ እያወዛወዙ የሚቀርበው የአምልኮ ልማድ አማኝ ነን በሚሉት መካከል መታየቱ ከዚህ እስራት ለዳኑት ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ በመሆኑም ካለማወቅ የተነሣ ከመድረክ ተዋንያን በሚነገራቸው የማሟሟቂያ ቃላት ብቻ ተታልለው በአሕዛብ የአምልኮ ጠባይ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ የዋሃን አማኞች አሁን ቆም ብለውና ልባቸውን አስፍተው አምልኮአቸውን ሊመረምሩ ይገባል፤ ምናልባትም ባልበረደና፣ በተደጋጋሚ እየገነፈለ በሚያስቸግረው የወጣትነት ስሜት በመገፋፋት የሚፈጸም የስሜት አምልኮ ከሆነም በዚህ ስሜት ላይ ሊፈርዱበትና አምልኮአቸውን እንደ እግዚአብሔር ቃል ሊያደርጉ ይገባቸዋል።

5ኛ. አንዳንድ ጊዜ ደግሞ «ሰው ስሜት ስላለው ልቡ ሲነካ ስሜቱ ፈንቅሎት ሳያስበው ሊዘልልና ሊጨፍር ይችላል» በሚል ደካማ ምክንያት ጉዳዩ በቸልታ ሲታለፍ ይታያል። በመሠረቱ ሰው ስሜት እንዲኖረው ተደርጎ የተፈጠረ ፍጡር እንደሆነ የታወቀ ነው። ስሜቱም እንደየሁኔታው የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ የኀዘን ሌላ ጊዜ የደስታ ስሜት በሰው ላይ ይታያል። ምድራዊና ሥጋዊ የሆነ ኀዘንና ደስታ በዚያው ምድራዊና ሥጋዊ በሆነ መንገድ ይገለጣል፤ የኀዘን ስሜት በመራራ ልቅሶ ፊትንና ጸጉርን በመንጨት ደረት በመምታት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በራስ ላይ የከፋ ጉዳት በማድረስ ሊገለጥ ይችል ይሆናል፤ እንዲሁም የደስታ ስሜት በዘፈንና በዝላይ ወይም በዳንኪራ ይገለጥ ይሆናል፤ ይህ በክፉው በተያዘው በኃጢአተኛው ዓለም የሚከናወን ሲሆን መንፈሳዊ ሰው ግን ስሜቱን የሚገልጠው ከእነዚህ በተለየ መንገድ ነው፤ በኀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ የክርስቲያን ስሜት በመንፈስ ቅዱስ ቊጥጥር ሥር መሆን ይገባዋል። እንደዚሁም «የእግዚአብሔር ቃል ራስን ስለመግዛት» የሚያስተምረውን ሁሉ ክርስቲያን ተግባር ላይ ሊያውለው ያስፈልጋል፤ በገላ.5፡22-23 ከተዘረዘሩት የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ «ራስን መግዛት» ነው። በ2ጢሞ1፡7 ላይ ደግሞ «እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና ተብሎ ተጽፏል፤ ስለሆነም ክርስቲያን ሁል ጊዜ ራስን የመግዛት መንፈስ ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር፣ በልጁ ሞት የፈጸመው የማዳን ሥራ፣ እንዲሁም በመግቦቱ የሚያደርጋቸው ነገሮች ልቡን ቢነካውና ከፍ ያለ ደስታ ቢፈጥርበት ይህንን ክቡር የሆነ መንፈሳዊ ስሜት ልቅ በሆነ የሥጋ ጭፈራ ሊገልጠው አይገባም፤ ልቅ ባይሆንም በሥጋ የሚደረግ ዝላይ ለእግዚአብሔር ያለንን ስሜት መግለጥ አይችልም፤ አንዳንድ ጊዜ ራስን መቈጣጠር እስከተቻለና ከልክ ያለፈ እስካልሆነ ድረስ ዝላዩ ምን ችግር ይኖረዋል? የሚል ለሥጋዊ ስሜት በር የሚከፍት ሐሳብ ሲሠነዘር ይደመጣል፤ ሆኖም ራስን መግዛት ማለት ጭፈራውንና ዝላዩን በመጠኑ ማድረግ ከልክ እንዳያልፍና ከቊጥጥር ውጪ እንዳይሆን ወይም ልቅ እንዳይሆን ማድረግ ማለት አይደለም፤ ቀድሞውኑ ሥጋ የእግዚአብሔርን መዝሙር ተጠቅሞ ሊዘልል እና ሊጨፍር ሲፈልግ የሥጋ ውዝዋዜ እግዚአብሔርን ለማምለክ ምንም ድርሻ እንደሌለው በማስተዋል ለመዝለል የተነሣሣውን የሥጋ ስሜት ገዝቶ በዜማ እና በከንፈር ፍሬ ብቻ ለማምለክ መቻል ነው፤ ክርስቲያን ደስታውን የሚገልጠው በመዝሙር ነው፤ «ደስ የሚለው ማንም ቢሆን እርሱ ይዘምር» ተብሏል (ያዕ.5፡13)። ስለሆነም ደስ ተሰኝተን እግዚአብሔርን ስናመልክ ልንዘምር እንጂ ልንዘልልና ልንጨፍር አይገባንም፤ የሥጋ ውዝዋዜ መንፈስ ለሆነው አምላካችን አይስማማውምና።

የጉባኤ አምልኮ አፈጻጸም

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት የዳኑ ሰዎች ከውኃና ከመንፈስ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ። በአዲስ ኪዳን ሕያው እግዚአብሔርን ሊያመልኩ የሚችሉትም በዚህ ዓይነት ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ደም የነጻና ሕያው እግዚአብሔርን ሊያመልክ የሚችል ኅሊና አላቸው። ጌታችን ስለአምልኮ ባስተማረው መሠረታዊ ትምህርት ውስጥ ስግደቱ ወይም አምልኮው የሚቀርበው “ለአብ” እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግሯል። “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” (ዮሐ.4፡21)፣ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል” (ዮሐ.4:23)፤ እንዲሁም “አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” (ዮሐ4፡23) በሚሉት የጌታ ቃላት ውስጥ የሚመለከው አምላክ “አብ” ተብሎ ተጠርቷል። ይህም እኛ በአምልኮ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ በእግዚአብሔር ልጅነታችን ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳል። በኢየሱስ አምነን የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንንም እግዚአብሔር «አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ» በልባችን ውስጥ ልኮአል (ገላ.4፡6)። ስለሆነም የክርስቲያኖች አምልኮ በልጅ እና በአባት መካከል ያለ የፍቅር ኀብረት የሚገለጥበት ነው። ልጅ ለአባቱ የሚገዛው ፈቅዶና ወድዶ ማለትም ከፍቅር በሚነሣ መታዘዝ እንደ ሆነ ሁሉ እኛም እግዚአብሔር አባታችንን የምናመልከው በገዛ ፈቃዳችን፣ ለእርሱ ካለን ፍቅር የተነሣ ሊሆን ይገባል።

ለአባታችን ካለን ፍቅር የሚነሣውን አምልኮ በጉባዔ ስናቀርብ ተግባራዊ አፈጻጸሙ ምን ሊመስል ይችላል? ባለፉት ክፍሎች የአዲስ ኪዳን አምልኮ አንድ የአምልኮ መሪም ሆነ የተወሰኑ የመዘምራን ቡድን እንዲሁም ያማረ የሙዚቃ ቅንብር የሚመሩት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ሊቀካህናቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በመካከላችን በሚያድረው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚመራው አምልኮ እንደሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት ተምረናል። ታዲያ ይህ አምልኮ በተግባር ሲፈጸም ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል ማወቅ የብዙዎች መሻት ነው። መደበኛ የሆነ ይዘትና ቅደም ተከተል ያለው፣ ለዓመታት ቋሚ ሆኖ የሚኖር የአምልኮ አፈጻጸም ምን ጊዜም ቢሆን በመንፈስና በእውነት በሚቀርብ አምልኮ ውስጥ ሊኖር አይችልም፤ ሆኖም በአምልኮ ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ፣ የሚያደንቁና የሚያወድሱ የከንፈር ፍሬዎች መንፈስ ቅዱስ ባቀናበራቸው መሠረት እንደሚቀርቡ መረዳት ይቻላል።

በጌታ በኢየሱስ ስም ተሰብስበን እግዚአብሔርን የምናመልከው ወደ እግዚአብሔር የምንናገረው የተለያዩ የአምልኮ መዝሙሮችን በመዘመርና እርሱ በባሕርዩ የሚመለክባቸውን ቃላት በመንፈሱ ተገዝተን ወደ እርሱ በመናገር ነው። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚከብርባቸውንና የሚደነቅባቸውን ቃላት በወንድሞች ልብ ውስጥ ከሞላ በኋላ በዜማም ይሁን ንግግር መልክ እንዲገለጡ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም በጊዜ በአምልኮው ላይ የተነሣውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚመለከቱ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦችንም መንፈስ ቅዱስ በወንድሞች በኩል ሊያመጣ ይችላል፤ እነዚህን ሁሉ በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረንን ቀጥሎ እንመለከታለን።

  1. መዝሙሮችን መዘመር

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከነበረበት ጊዜ አንሥቶ በአዲስ ኪዳን አማኞች ዘንድ መዝሙር እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳለን። በዕብ.2፡13 ላይ ከመዝሙረ ዳዊት ተጠቅሶ ስለመሢሑ ስለኢየሱስ የተጻፈው ቃል “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ” ይላል (መዝ.21(22)፡22)። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ በስቅለቱ ዋዜማ ወደፊት የቤተክርስቲያኑ አባላት በሚሆኑት ወንድሞቼ በሚላቸው በደቀመዛሙርቱ መካከል ሆኖ አብሮ መዝሙርን ዘምሯል (ማቴ.26፡3ዐ፤ ማር.14፡26)። እርሱ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ካረገ በኋላም በምድር ላይ በስሙ በሚሰበሰቡት መካከል እንደሚገኝ ቃል ስለገባ በማኅበር መካከል አብሮን በዜማ እንደሚያመሰግን ልናምን እንችላለን።

በሐ.ሥ.16፡25 ጳውሎስና ሲላስ በእስር ቤት ሆነው በመንፈቀ ሌሊት እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ እንደነበር ተጽፏል፤ እንዲሁም በያዕ.5፡14 «ደስ የሚለው ማንም እርሱ ይዘምር» ይላል። ሆኖም ይህ ሁሉ በማናቸውም ጊዜ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን በየግል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበትን አምልኮ ያሳያል። የቤተክርስቲያን የአምልኮ መዝሙሮችን በተመለከተ በይበልጥ የሚያስረዳው ግን በ1ቆሮ.14፡15 እና በ1ቆሮ.14፡26 ላይ ስለመዝሙር የተጻፈው ነው። በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት ከም.12 እስከ ምዕ.14 ድረስ ባለው ክፍል አማኞች ወደ ማኅበር ሲሰበሰቡ ስለሚያደርጓቸው ነገሮች የተጻፈ መለኮታዊ ሥርዓትን እናገኛለን። ስለሆነም በዚህ ክፍል ስለመዝሙር የተጻፈውም የጉባዔ (የማኅበር) መዝሙርን ያመለክታል። በ1ቆሮ.14፡15-16 «እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ፤ እንዲያማ ካልሆነ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል?» በማለት ይናገራል። በዚህ ቃል የተገለጠው ጸሎትና መዝሙር በማኅበር መካከል የሚደረግ መሆኑን ሌሎች የሚባለውን ማወቅ እንደሚገባቸው ከተነገረው ሐሳብ እንረዳለን። እንደ ጸሎቱ ሁሉ መዝሙርም በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአእምሮም ደግሞ መዘመር አለበት። ይህም ማለት እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር በሰጠው የተፈጥሮ ማስተዋል የመዝሙርን ሐሳብ እየተረዳ ሊዘምር ይገባል ማለት ነው። ሁሉም በቋንቋቸው የሚሰሙትና የሚያውቁት መዝሙር እንዲሆን የተፈለገውም ለዚህ ነው። እንደዚሁም በ1ቆሮ.14፡26 ላይ «እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፣ ትምህርት አለው፣ መግለጥ አለው፣ በልሳን መናገር አለው፣ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን» የሚል ቃል ይገኛል። የቆሮንቶስ አማኞች በሚሰበሰቡበት ጊዜ ያደርጓቸው ከነበሩት ነገሮች መካከል 5ቱ በዚህ ቊጥር የተገለጡ ሲሆን ከ5ቱም አንዱ መዝሙር ነበር፤ እነዚህንም ነገሮች ተሰብስበው የሚያከናውኑት አስቀድሞ በተዘጋጀ ወይም በተደነገገ ሥርዓት ወይም አስቀድሞ በሚታወቅ ቅደም ተከተል ሳይሆን በሚሰበሰቡ ጊዜ እያንዳንዳቸው ያላቸውን ነገር ማለትም መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው የሞላውን ነገር መዝሙርም ይሁን ሌሎቹን ነገሮች ወደ ጉባዔው በማምጣት ነበር። ስለሆነም በመደበኛ ሁኔታ የምትሰበሰብ አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ይህንን መርህ ልትከተል ይገባታል።

“ሁሉ ለማነጽ ይሑን" ተብሎ የተጻፈው መመሪያ መዝሙርንም የሚመለከት ከመሆኑ አንጻር ስናየው ለጌታ የሚዘመሩ መዝሙሮች ሰዎች እያስተዋሉ ትርጉማቸውንም እየተረዱ ከዘመሯቸው፣ መዝሙሮቹን የማያውቁ ካሉና የመዝሙሮቹ ቃላት እየገቧቸው ከሰሟቸው ይታነጹባቸዋል። ይህ ማለት ለልባቸው የሚቀር መልእክትና አንዳች መንፈሳዊ በረከት ይኖራል ማለት ነው። በመንፈስም በአእምሮም የሚዘመር መዝሙር እግዚአብሔርን ከማምለካችን በተጨማሪ ለእኛም ሆነ ስንዘምር ለሚያዳምጡን እንግዶች መታነጽ ይሆናል። ከዚህም ሌላ ወደ ሰዎች ትምህርትንና መልእክትን ሊያስተላልፉ የሚችሉ መዝሙሮችን እየተቀኙ መዘመር ይቻላል። በተለይ ለትምህርትና ለወንጌል ሥርጭት አገልግሎት ሕዝብ በሚሰበሰብ ጊዜ የሚዘመሩት መዝሙሮች እንደዚህ ያሉ ሊሆኑ ይገባል። እንደዚሁም መዝሙሮች በየግልም ሆነ በየቤቱ ባሉ የቤተሰብ የመተናነጽ ክፍለ ጊዜያት ጌታን ለማክበርም ሆነ ሰዎችን ለማነጽ ያላቸው አገልግሎት ሊዘነጋ አይገባም። ይህንን ሁሉ በተመለከተ «መንፈስ ይሙላባችሁ» ለተባሉት የኤፌሶን አማኞች የተጻፈው ቃል እንዲህ ይላል፤ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” (ኤፌ5፡18-19)፤ እንደዚሁም “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ለተባሉት የቈላስይስ አማኞች “በጥበብ ሁሉ እርስ በእርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” ተብሎ ተጽፎአል (ቈላ.3፡16)።

መዝሙሮች በሚዘጋጁ ጊዜ ይህ ሁሉ ሊታሰብ ያስፈልጋል። ይህም ማለት በኤፌ5፡18 እንደተገለጠው በመንፈስ ተሞልተን፣ በቈላ.3፡16 እንደተገለጠው ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል ተሞልተን ልንገጥማቸው (ልንቀኛቸው) ይገባል ማለት ነው። ከእግዚአብሔር መንፈስና ከእግዚአብሔር ቃል ምስክርነት ያልተገኘ ባዕድ ነገር ልንዘምር አይገባም። መዝሙሮች በእግዚአብሔር ማንነትና በሥራው እንዲሁም በሐሳቡና በፈቃዱ የተሞሉ ሊሆኑ ይገባል። በእኔነት የተሞሉና ራስን የሚያሞካሹ እንዲሁም ለራስ ትኲ ረት የሚሰጡ ቃላት ወደ መዝሙሮቻችን እንደይገቡ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። በዚህ ፈንታ ግን የመዝሙሮቹ ይዘት በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ሆኖ በቅድሚያ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ እና ደግሞም የሚዘምሩትንም ሆነ የሚሰሙትን የሚያንጹ ሆነው ሊዘጋጁ ይገባል።

ዜማቸውንም በተመለከተ ቀላልና በእርጋታ የሚፈስ ዜማ ቢኖራቸው መልካም ነው። ምክንያቱም መዝሙር የሚዘመረው ነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር በአምልኮ እንድትነጋገር ለማስቻልና ሰዎችን ለማነጽ ነው እንጂ የተወሳሰበ የአርት ኪነጥበብ እንዲገለጥበት ለማድረግ አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ በዘፈን ዓለም የተለመዱትን ዘመናዊ የዜማ ስልቶችን ወደ መዝሙሮች ዜማ ውስጥ በማስገባት የሚታየው የተደበላለቀ አዘማመር የክፉውን ዓለም የተበከለ አየር በአማኞች መካከል የሚስብ ከመሆን ሌላ የሚጨምረው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ የመዝሙሮች ዜማ የምንዘምረውን ቃል ማስተዋል እንድንችል ዕድል የሚሰጥ ጥድፊያ ያልበዛበትና በሰከነ መንፈስ የሚዘመር እንዲሆን ተደርጎ ቢዘጋጅ ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ስሜት ተመራጭና ተስማሚ ይሆናል።

  1. የአምልኮ ምስጋናን ማቅረብ

በጉባኤ አምልኮ ጊዜ በዋናነነት እግዚአብሔርን የምናመልከው የእግዚአብሔርን ማንነት ማለትም የእርሱ ብቻ የሆነውን ባሕርይ የሚመለከቱ የአምልኮ ምስጋናዎችን ወደ እግዚአብሔር በመናገር ነው። በተለይም ለእግዚአብሔር የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለእኛ ራሱን የሰጠውን የክርስቶስ ኢየሱስን ባሕርያቶችና ሥራዎቹን ለእግዚአብሔር እያቀረብን ልናመልከው ያስፈልጋል (ኤፌ.5፡2) ጌታ ኢየሱስ እኛ ሁላችን እንደ ካህናት በአምልኮአችን ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር ልናቀርበው የሚገባን ጣፋጭ ሽታ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕታችን ነው። በመዝ.49(50)፡7-14 የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምስጋና መሥዋዕት ጋር ተነጻጽሮ መቅረቡን እናነባለን፤ በዕብ.13፡15 ላይ ደግሞ «እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቅርብለት» የሚል ቃል እናነባለን። ስለዚህ በጉባኤ መካከል ወደ እግዚአብሔር በመናገር የከንፈሮች ፍሬ በሆነ በምስጋና መሥዋዕት ልናመልክ ይገባል።

በጉባኤ መካከል መንፈስ ቅዱስ የአምልኮ ምስጋናዎችን በልባቸው የሞላላቸው ወንድሞች እየተነሡ እግዚአብሔርን በአምላካዊ ባሕርያቶቹና ሥራዎቹ ሊያደንቁትና ሊያከብሩት ይችላሉ። ለዚህ አስቀድሞ የሚዘጋጅ የተወሰነ መደበኛ ሥርዓት ሊኖር አይገባም፤ እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደ ማኅበር ከተሰበሰቡት ወገኖች መካከል እንዲያመሰግኑ ቀደም ብሎ የሚነገራቸው ወንድሞች መኖር የለባቸውም፤ የምስጋናውም ርእስ አስቀድሞ መወሰን የለበትም። ይህን ሁሉ በዚያው በአምልኮው ጊዜ ይወስን ዘንድ ዕድሉን ለመንፈስ ቅዱስ መተው ያስፈልጋል። በእኛ ዘንድ እንዳለ የምናምነው መንፈስ ቅዱስ ያለምንም መደነጋገር እና መፋለስ ሊመራን የሚቻለው የእውነት መንፈስ ነው። አልፎ አልፎ «አስቀድሞ የተዘጋጀ ሥርዓት ከሌለ በአምልኮው ጊዜ ሥርዓት ሊበላሽ አይችልምን?» እየተባለ የሚነሣው ጥያቄም በዚህ መልስ ያገኛል። መንፈስ ቅዱስ ለሚያምኑት ታማኝ ነው። በእርግጥ ማኅበሩ ሁሉ እርሱን ማዳመጥ በእርሱ መመራት ከቻለ እርሱ በሚወስነው ርእስ እርሱ የወሰናቸው ወንድሞች እርሱ በወሰነው ጊዜ እየተነሡ የምስጋና ቃላትን ያፈሳሉ፤ ሌሎችም ለምስጋናቸው አሜን ይላሉ። «አሜን» የሚለው ቃልም እንደመፈክር የሚባል የስሜት መግለጫ አይደለም፤ ነገር ግን ከመጣው የቃል ምስጋና ጋር የምንስማማ መሆናችንን ወይም ያ ምስጋና በአንድ ወንድም አንደበት ቢባልም የሁላችን ምስጋና መሆኑን ለመግለጥ አሜን እንላለን።

  1. የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦችን ማንበብ

ለአምልኮ በተሰበሰብን ጊዜ ከጅማሬው አንስቶ ከምንዘምረው ዝማሬ ወይም በቃል ከሚመሰገነው የአምልኮ ምስጋና ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችልና በጊዜው በአምልኮ ጉባዔው ላይ በትኲ ረት የተነሣውን ርእስ የሚመለከት የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ቢነበብ በልብ ላይ የተባረከ መንፈሳዊ ስሜትን ሊፈጥር ይችላል። በአምልኮው ላይ እየተባለ ያለውን ሁሉ በይበልጥ እንድናስተውል ይረዳናል፤ ለመታነጽም የሚሆን ቃል እንሰማለን። ሆኖም የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦቹም ሆኑ አንባቢው እንዲሁም የሚነበብበት ጊዜ ቀደም ብሎ በሰው አይቀናበርም። በዚያው በአምልኮው ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በየልባችን በሚያመጣቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ስንሞላ የሚነበብ ብቻ ይሆናል። የግድ በሁሉም የአምልኮ ቀን ቅዱሳት መጻሕፍት መነበብ አለባቸው የሚል ሐሳብም ሊኖር አይገባም። አንዳንድ ቀን የአምልኮ ጊዜው በሙሉ በዝማሬና በምስጋና ቃል ከተያዘ ሳይነበብ ሊቀር ይችላል። በሚነበብበት ጊዜም ቢሆን ከተያዘው የአምልኮ ርእስ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ወይም ልናመሰግን ከፈለግነውና ልንዘምር ካሰብነው ጋር በምንም የማይያያዝ በድንገት ትዝ ያለንን ጥቅስ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ገለጥ ስናደርግ ባጋጣሚ ያገኘንውን ጥቅስ ሁሉ ልናነብ አይገባም፤ በእርግጥ ራሳችንን ሳይሆን የእግዚአብሔርን መንፈስ እያደመጥን የምናመልክ ከሆነ ይህ ችግር ሊኖር አይችልም።

ማስገንዘቢያ፡-

በጉባዔ አምልኮ ጊዜ መዝሙሮችም ሆኑ በቃል የሚቀርቡ የአምልኮ ምስጋናዎች እንዲሁም በየጣልቃው የሚነበቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ሲቀርቡ በልባችን ላይ ግፊትና ተጽዕኖ የሚያደርገውን የእግዚአብሔርን መንፈስ የምናዳምጥበት ጥቂት ጊዜ ሊኖረን ይገባል። ይህም የጸጥታ ጊዜ መስፈኑ የሚያመልኩት አማኞች መንፈስቅዱስ በልባቸው የሚያደርገውን ተጽዕኖ የሚለዩበት ጊዜ ስለሆነ በአምልኮ ጉባኤ የሚገኝ አማኝ በዚያ ጊዜ በልቡ ውስጥ የሚሰማውን የመንፈስቅዱስ ድምፅ ማዳመጥና መለየት ይገባዋል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ከግብዝነትና መናገርን ከመውደድ የተነሣ ብቻ በልባችን መንፈስ ቅዱስን ሳናዳምጥ የምንናገር ሰዎች ልንሆን አይገባም። በዚያ ሰዓት የምናመልክበት ርእስ ወደልባችን ካልመጣ የእግዚአብሔርን ነገር እያሰላሰሉ መቆየት መልካም ነው። አንድ የአምልኮ ርእስን መንፈስ ቅዱስ በልባችን ላይ ሲያመጣ ደግሞ የምንናገረው ሁሉ ያንንው መስመር የተከተለ ሊሆን ይገባል። እንደዚሁም «እግዚአብሔር ሆይ» ብለን ከጀመርን መለኮታዊ ባሕርዩን የሚመለከቱ ሥራዎቹንና ለእኛ ያለውን ፈቃዱን እያወሳን አምልኮውን ልናቀርብ ይገባል። «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ» ብለን ከጀመርን ደግሞ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነቱ ለእኛ ያደረገልንን ነገሮች እያነሣን ልናመልከው ይገባናል። በተለይ እንጀራ በመቊረስ የክርስቶስን ሞት በምናስብበት ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በሰውነቱ ያደረገልንን ሁሉ የሚመለከት ምስጋና ሊቀርብ ይገባዋል፤ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ እያደነቅን በምናመልክበት ጊዜ ደግሞ መለኮታዊ ባሕርያቶቹንና መለኮታዊ ሥራዎቹን የሚያወድስ አምልኮን ርእስ በመጠበቅ ልናቀርብ ይገባል፤ በአጠቃላይ የአምልኮ አድራሻንም ሆነ የአምልኮ ይዘትን እንዲሁም የአምልኮ አርእስትን የመደበላለቅ ልማድ ሊኖር አይገባም። በእርግጥ ገና አዲስ የተወለዱ ጀማሪ አማኞች ይህን ሁሉ መለየት አይችሉ ይሆናል፤ እነዚህ አዳዲስ አማኞች የአምልኮ አድራሻንና የአምልኮ ይዘትን እንዲሁም የአምልኮ አርእስትን ጠብቀው ማምለክ ባይችሉም አንደበታቸው ለአምልኮ በመከፈቱና እግዚአብሔርን «አባ አባ» ብለው ለመጥራት በመቻላቸው ብቻ ሊበረታቱ ይገባቸዋል፤ ከተደበላለቀና ከተዘበራረቀ የአምልኮ ልማድም ቀስ በቀስ እንዲወጡና በአእምሮ የበሰሉ እንዲሆኑ ወንድማዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል፤ በዚህ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋላቸውን እያሳደገው የአምልኮን አጠቃላይ መስመር በአግባቡ እየለዩ ይመጣሉ።

ማጠቃለያ

ስለ አዲስ ኪዳን አምልኮ በዚህ ጽሑፍ የቀረበው እውነታ በብዙ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት የተለመዱ ሥርዓተ አምልኮዎችን የተከተለ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ በመንፈስና በእውነት ስለማምለክ ያስተማረውን ትምህርት የተከተለ ነው። ጌታ እንደተናገረው በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱ (ሊያመልኩ) የሚችሉት “በእውነት የሚሰግዱ” (ዮሐ.4፡23) ብቻ ናቸው። ሰዎች «በእውነት የሚሰግዱ (የሚያመልኩ)» ካልሆኑ፣ እንኳን በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩ ቀርቶ ስለእንደዚህ ዓይነት የከበረ አምልኮ የሚነገረው እውነትም አይገባቸውም፤ ቢገባቸውም ሊቀበሉትና በተግባር ሊተረጉሙትም አይፈልጉም፤ በእውነት የሚሰግዱ ግን ለአብ በመንፈስና በእውነት ይሰግዳሉ (ዮሐ.4፡23)።

“በመንፈስና በእውነት” ከሆነው የአዲስ ኪዳን አምልኮ ጋር አብረው የማይሄዱ በፍጥረታዊው ሰው አማካኝነት ጣልቃ የገቡ ሥርዓቶችን እያነሣን አማኞች ለእግዚአብሔር ማቅረብ ያለባቸው አምልኮ ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖረው እንደሚገባ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረን እውነት በግልጽነት በዚህ ጽሑፍ ቀርቧል፤ በእውነት የሚሰግዱ (እውነተኛ አምላኪዎች) ቀደም ሲልም መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ሲያበራላቸው የነበረውን ይህን እውነት ለመቀበልና ለመታዘዝ ጊዜ አይወስድባቸውም። ጉዳዩን በመንፈሳዊ አእምሮ ለማሰላሰል ለተቸገረ ሰው ግን የአምልኮ መሪ መኖር፣ በአምልኮ ጊዜ የመዘምራን አገልግሎት መኖር፣ በአምልኮ ጊዜ የተለዩ አልባሳት ለብሶ መታየት፣ ቊሳዊ የሆነውን የሙዚቃ መሣሪያ ወይም የዜማ ዕቃ ለአምልኮ መጠቀም የአዲስ ኪዳኑ የመንፈስና የእውነት አምልኮ ባሕርያት አለመሆናቸው ሲነገር መስማት አዲስ ሊሆንበት ይችላል። የመንፈስና የእውነት አምልኮን ምንነትና የመለያ ባሕርያቱን ትኲረት ሰጥቶ ካለማጥናት የተነሣ ቅን ኅሊና ባላቸው አንዳንድ አማኞች ዘንድም እንኳ ይህ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም፤ ሆኖም ለጊዜው አዲስ ቢሆንባቸውም ወደፊት በጌታ ጸጋ እየታገዙ ስለ አዲስ ኪዳን አምልኮ በግልጽነት ወደተነገረው ወደዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአዲስ ኪዳን አምልኮን በሚመለከት በዚህ ጽሑፍ የተገለጠው እውነታ አማኞች በአምልኮ ጉባዔ ጊዜ ብቻ የምናደርገውን የሚገልጽ መሆኑን ማስተዋል ከመደነጋገርና ግራ ከመጋባት ይጠብቃል። አጥቢያ ቤተክርስቲያን ማንነቷን የሚገልጡ የራስዋ ወይም የብቻዋ የሆኑ የተለያዩ ጉባዔያት (ስብሰባዎች) አሏት፤ እነርሱም፡- የ አምልኮ ጉባኤ፣ የቃል አገልግሎት ጉባኤ፤ የጸሎት ጉባኤ ናቸው፤ እነዚህ ጉባዔያት የየራሳቸው የተለየ ባሕርይ ያላቸው ሲሆን ቤተክርስቲያን በውጭ ካለው ዓለም ተለይታ የምታካሂዳቸው የራሷ ጉባዔያት ናቸው። ከነዚህም ጉባዔያት መካከል “የአምልኮ ጉባኤ” አማኞች በኢየሱስ ስም ተሰብስበው እግዚአብሔርን በአምላካዊ ማንነቱ እያመሰገኑና እያወደሱ የሚያመልኩበት ጉባዔ ነው፤ ይህም የአምልኮ ጉባዔ «በመንፈስና በእውነት» ብቻ የሚቀርበውን የአዲስ ኪዳን አምልኮ ባህርይ የተከተለ መሆን እንዳለበት በስፋት ተገልጧል።

ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ እየተባለ ያለውን ነገር ይበልጥ ግልጥ ለማድረግ ከአምልኮም ሆነ ከሌሎቹ የቤተክርስቲያን ጉባዔያት ውጪ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ በውጭ ካለው ዓለም ጋር የሚያደርጉአቸውን ስብሰባዎች መመልከቱ ጠቃሚ ነው፤ ለምሳሌ በሰርግ፣ በሽኝት እና በመሳሰሉት አማኞች በዚህ ዓለም ሲኖሩ ኢአማንያንን በሚጠሩባቸው መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ ምንም እንኳ መድረኩን የሚመሩት አማኞች ቢሆኑም ፍጥረታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ሊከናወኑ እንደሚችሉ የሚካድ አይደለም፤ ለምሳሌ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች በመድረክ መሪ ቢመሩ፣ በሰርግ ጊዜ ሙሽሮችና ሚዜዎች የተለየ ልብስ ቢለብሱ፣ እንዲሁም በእንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች ለኢአማንያን መልእክት ማስተላለፍ የሚችሉ የምስክርነት መዝሙሮች በሙዚቃ ታጅበው ቢቀርቡ ስለ አምልኮ ከጌታችን የተማርነውን መርህ የሚጥሱ አይሆኑም፤ ምክንያቱም እነዚያ ስብሰባዎች በሁኔታዎችና በክስተቶች ወይም በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሚካሄዱ ስብሰባዎች ናቸው እንጂ መደበኛ የቤተክርስቲያን ስብሰባዎች አይደሉም፤ እንዲሁም ወንጌላውያን ወደ አደባባይ ወጥተው በዓለማውያን መካከል ወንጌልን በሚሰብኩበት ጊዜ የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መርህ የግድ ሥራ ላይ ማዋል አይጠበቅባቸውም፤ ምክንያቱም ይህ የወንጌል ሥርጭት ጉባዔ ነው እንጂ የአምልኮ ጉባዔ አይደለምና።

አማኞች መዝሙሮችን በካሤት ለማሳተም ሲፈልጉም የመዝሙሩን ቃል የማይሸፍን ለስለስ ያለ ሙዚቃ ቢጠቀሙና በየቤትም ቢሆን ክርስቲያኖች በዕረፍት ሰዓታቸው መዝሙሮችን በሙዚቃ በመቃኘት ቢዘምሩ ወይም መዝሙርን ቢያጠኑ ይህ ሁሉ የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መመሪያ የሚያፈርስ አይደለም።

በዮሐ4 ላይ የምናነበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስና በእውነት ስለማምለክ ያስተማረን ትምህርት አማኞች በስሙ ተሰብስበው ለአምልኮ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርቡበት ጊዜ መሆኑን በትኲረት ማስተዋል ይገባል። በዚያ ክፍል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ በመረጠው ስፍራ ማለትም በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ይደረግ በነበረው አምልኮ ምትክ ስለሚደረገው የአዲስ ኪዳን አምልኮ መነገሩን ስንረዳ በኢየሱስ ስም ተሰብስቦ ስለሚደረግ የጉባኤ አምልኮ እናስባለን። በእንዲህ ዓይነቱ የአምልኮ ጉባዔ በብሉይ ኪዳን ይታዩ የነበሩት ፍጥረታዊና ቊሳዊ ነገሮች አገልግሎት ላይ አይውሉም። በአምልኮ ጊዜ የምንናገረውም ሆነ የምንዘምረው ወደ እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በመንፈስና በእውነት ብቻ ሊሆን ይገባል፤ እርሱ እግዚአብሔር መንፈስ ነውና። «በሥጋ የሆነ» ክርስቲያን ግን (1ቆሮ.3፡1) ምን ጊዜም የሚስማማው በሰው ዓይን ፊት አሸብርቆና ደምቆ የሚታይ ሥርዓተ አምልኮ መሆኑ ከብዙ ተሞክሮ የምናየው ነገር ነው። አንድ የሃይማኖት ሰፈር ከሌላው የሃይማኖት ሰፈር የሚበልጥና የሚሻል እንደሆነ ለማሳየት ራሱን ከሚገልጥባቸው መንገዶች አንዱ ባሸበረቁና ባጌጡ አልባሳት እና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተቀነባበረ በሰዎች ዘንድ ድንቅ ሊባል የሚችል አምልኮን ማቅረብ ነው፤ ይህ ዓይነት አምልኮ በሰዎች ፊት መደነቅን ቢያገኝና ፍጥረታዊ የሆነውን የሰው ስሜት ለማርካት ቢችልም መንፈስ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ግን የተናቀ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

እግዚአብሔር በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን እንዴት መመለክ እንደሚገባው ማወቁ ወሳኝ ነገር የመሆኑን ያህል እርሱን በማምለክ መትጋትም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በመንፈሳዊነት ባላደጉ አማኞች ዘንድ ለአምልኮ የሚሰጠው ትኲረት እጅግ አነስተኛ ሆኖ ይታያል። ብዙውን ጊዜ በትምህርትና በቃል አገልግሎት እየተካፈሉ በአምልኮ ጉባኤ ከመሳተፍ መዘግየት የዚህ ውጤት ነው፤ ብዙ ጊዜ ስለ አምልኮ እየተማሩ ለአምልኮ የሚሆን ጊዜ አለመስጠት ደግሞ አባታችን እግዚአብሔር በእኛ በልጆቹ ላይ ማግኘት የሚፈልገውን የአምልኮ ፍሬ አለማፍራት ነው። ከንቱ ለሆኑ ለዚህ ዓለም ነገሮች ውድ ጊዜያችንን እያባከንን በመንፈስና በእውነት መመለክ ለሚፈልገው አምላክ ጊዜ አለመስጠታችን ታላቅ ስንፍና መሆኑ ለታወቅ ይገባል። ከዚህም ስንፍና ተለይተን «አባ አባ» ብሎ በሚጮኽ በልጅነት መንፈስ እርሱን በማምለክ ልንተጋ ይገባናል።

በሌላ በኩል ደግሞ በግል የምንኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወት በቤተክርስቲያን ለሚኖረን የኅብረት ሕይወት መሠረት ነው፤ በግሉ የአምልኮ ጊዜ ያለው አማኝ በጉባኤ አምልኮም ሊተጋ ይችላል፤ በግል ጌታን የሚያመልክበት ጊዜ የሌለው አማኝ ግን በጉባኤ አምልኮም ላይተጋ ይችላል። አልፎ አልፎ ቢሳተፍም እንኳ የእርሱ አምልኮ አፍኣዊ ይሆናል፤ «ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው» እንደተባለው ነው (ማቴ.15፡7-9)። ስለዚህ በግልም ጌታን በእውነት የሚያመልኩ አማኞች ልንሆን ይገባናል። እንዲህ ከሆነም በቤተክርስቲያን አምልኮም በእውነት ጌታን የሚያመልኩ እንሆናለን።